ቀጥታ, እስራኤል የትራምፕን ባለ 15 ነጥብ የጋዛ ሰላም ዕቅድ ውድቅ ማድረጓን ኔታንያሁ ተናገሩ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የአሜሪካውፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡትን ባለ 15 ነጥብ የጋዛ ሰላም ዕቅድ ውድቅ ማድረጋቸውን ገለጹ። ኔታንያሁ የሰላም ዕቅዱን ውድቅ ለማድረግ የሰጡት ምክንያት በቅድሚያ ሐማስ ትጥቅ መፍታት አለበት የሚል ነው።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዩክሬን በሩሲያ ላይ በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 13 ሰዎች ተገደሉ

    ዩክሬን በሩሲያዋ ግዛት ታታርስታን ሪፐብሊክ ውስጥ በፈጸመችው የድሮን ጥቃት አንድ ሕጻንን ጨምሮ 13 ሰዎች መገደላቸውን የሞስኮ ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    ከትናንት እሁድ ምሽት ጀምሮ የተፈጸመው ድብደባ ሞስኮ ዩክሬን ላይ ሙሉ ጦርነት ከከፈተች ወዲህ ሩሲያ ላይ ተሰንዝረው በርካታ ሰዎችን ከገደሉ ጥቃቶች አንዱ ሆኗል።

    ዩክሬን ከድንበሯ ከ1,100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ኒዝኔካምስክ ከተማ ላይ ፈጽማዋለች ስለተባለው ጥቃት እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።

    የዩክሬን ጦር ኒዝኔካምስክ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ‘ታኔቮ’ የነዳጅ ማጣሪያን መምታቱን ገልጿል። የዩክሬኑ የመከላከያ ቴክኖሎጂ አምራች ‘ፋየርፖይንት’ በበኩሉ ጥቃቱ የተፈጸመው በኩባንያው የተመረቱ ‘ኤፍፒ-1’ ድሮኖች መሆኑን አስታውቋል።

    ጥቃቱ ከሌሊት እስከ ጠዋት ድረስ ለሰዓታት የቆየ እንደነበር የአካባቢው ምንጮች ተናግረዋል።

    ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቁ እና ትክክለኛነታቸው የተረጋገጠ ቪዲዮዎች ጭስ እና እሳት ወደ ሰማይ ሲወጣ አሳይተዋል። የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደውል ድምፅም ቪዲዮው ላይ ይሰማል።

    ሩሲያ የኢንዱስትሩ ተቋማት እና የመኖሪያ አካባቢዎች ዒላማ መደረጋቸውን አረጋግጣለች። የሩሲያ የምርመራ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ፤ “በማንኛውም ወታደራዊ ኦፕሬሽን ውስጥ ተሳትፎ የሌላቸው ሰላማዊ ሰዎች ቦታው ላይ ነበሩ” ብሏል። ቢቢሲ ይህንን መረጃ በራሱ አላረጋገጠም።

    ትናንት ሌሊት ከዩክሬን የተላኩ 450 ድሮኖች በሩሲያ አየር መከላከያዎች ተመትተው መውደቃቸው ተገልጿል።

    ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ዩክሬን ከድንበሯ ረጅም ርቀት ላይ የሚገኙ የሩሲያ ዒላማዎች ላይ የተሳኩ ጥቃቶችን ማድረስ ጀምራለች።

    እነዚህ ጥቃቶች ብዙውን ጊዜ ዒላማ የሚያደርጉት መጋዘኖች እና የኃይል መሠረተ ልማቶችን ሲሆን፣ በዚህ ምክንያት የሚገደሉ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥርም ጨምሯል።

    ዩክሬን እነዚህ መሠረተ ልማቶች ሩሲያ ለምታካሂደው ጦርነት የገቢ እና የሎጂስቲክ አስተዋጾ ያደርጋሉ የሚል ክስ ታቀርባለች።

  2. በኃይለኛ አውሎ ንፋስ ምክንያት ቻይና አንድ ሚሊዮን ሰዎች ቤታቸውን ለቅቀው እንዲወጡ አደረገች

    በቻይና የተከሰተው ‘ዶልፊን' የተባለ ከባድ አውሎንፋስ መሬት መድረሱን ተከትሎ፣ ባለሥልጣናት የፋይናንስ ማዕከል የሆነችውን ሻንጋይን ጨምሮ ከአገሪቱ ምሥራቃዊ አካባቢዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቤታቸውን ለቅቀው እንዲወጡ አደረጉ።

    አውሎ ንፋሱ ከፍተኛ ዝናብ ያስከተለ ሲሆን በተከሰተበት ክልል በሙሉ የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎችን አቋርጧል። ሰኞ ዕለት ብቻ በሻንጋይ ውስጥ ወደ 1,000 የሚጠጉ በረራዎች ተሰርዘዋል።

    ባለሥልጣናቱ ‘ዶልፊን’ የተባለው አውሎ ንፋስ ወደ ‘ትሮፒካል’ አውሎ ንፋስ ዝቅ ስለማለቱ የገለፁ ቢሆንም፣ ወደ ሰሜን አቅጣጫ እየተጓዘ ያለው አውሎ ንፋሱ እስከ ረቡዕ ድረስ ኃይለኛ ዝናብ፣ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ማስጠንቀቃቸውን ቀጥለዋል።

    ቻይናን ከመቱት አውሎ ንፋሶች ሁሉ የጎላው ስለሆነው ‘ዶልፊን’ አውሎ ንፋስ፥ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ቀደም ሲል ከፍተኛ የጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፈው ነበር።

    እሁድ ዕለት ከሰዓት በኋላ በዤጂያንግ ግዛት ዩሁዋን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲከሰት የንፋሱ ፍጥነት በሰዓት 150 ኪሎ ሜትር እንደነበረ የሜትሮሎጂ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

    ሰኞ ዕለት ደግሞ በሻንዶንግ፣ ሄናን፣ ሁቤይ፣ አንሁይ፣ ጂያንግሱ፣ ዤጂያንግ ግዛቶች እና በሻንጋይ ከተማ ከፍተኛ ዝናብ እንደሚዘንብ ተተንብዮ ነበር። መንግሥት፣ ህዝቡ ከቤት ውጭ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲቆጠብ ሲያሳስቡ በርካታ የቱሪስት መስህቦች ዝግ ሆነው እንዲቆዩ መወሰኑ ታውቋል።

  3. ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የምትፈጽማቸው ጥቃቶች መቀጠላቸው ተገለፀ

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚፈፅማቸው ጥቃቶች መቀጠላቸውን የብሪታንያ የባህር ላይ ንግድ ስራዎች ድርጅት አስታወቀ።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦች ላይ የሚደረጉ ጥቃቶች በመቀጠላቸው፥ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው የስጋት መጠን "ከባድ" እንደሆነ መቀጠሉን ድርጅቱ አስታውቋል።

    ድርጅቱ እንደገለፀው፣ ባለፈው ቅዳሜ አንድ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የነዳጅ መርከብ በውሃ መተላለፊያው ላይ ዒላማ የተደረገ ሲሆን፥ በወሽመጡ በኩል የሚደረገው የንግድ እንቅስቃሴ በጥቂት መርከቦች ብቻ ተወስኖ በ"ዝቅተኛ" ደረጃ ላይ ይገኛል።

    “ለልየታ የሚረዱ የራዲዮ ግንኙነቶችን ማድረግ፣ ድሮኖችን ማብረር እና የንግድ መርከቦችን ዒላማ ያደረገ ክትትልን ጨምሮ የአብዮታዊ ዘቡ ጥቃቶች እና የትንኮሳ እርምጃዎች ቀጥለዋል” ሲል ድርጅቱ ባወጣው የቅርብ ጊዜ ወርሃዊ ሪፖርቱ ገልጿል።

    ሪፖርቱ አክሎም “እነዚህ ድርጊቶች ኢራን ቁልፍ በሆኑ የባህር ላይ ማጓጓዣ መስመሮች ላይ ያላትን ተጽዕኖ የማጠናከር እና በመስመሮቹ በሚያልፉ መርከቦች ላይ ግፊት የማድረግ ፍላጎት እንዳላት የሚያመለክቱ ሆነው ቀጥለዋል” ብሏል። በመርከቦች አቅራቢያ የሚደረጉ የሚሳዔል ጥቃቶች እና ፍንዳታዎችን ጨምሮ ቀጥተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችም ወደ ኦማን በሚወስዱት ደቡባዊ መስመሮች (በሊማ-ኻሳብ-ኩምዛር አካባቢ) መቀጠላቸው ተጠቅሷል።

    የብሪታንያ የባህር ላይ ንግድ ስራዎች ድርጅት፣ ያልተመዘገቡ እና ያልፈነዱ ፈንጂዎች የሚያደርሷቸው አደጋዎችም በሆርሙዝ ወሽመጥ ሊቀጥሉ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።

  4. በሆርሙዝ መከፈት ላይ ስምምነት ባለመደረሱ የነዳጅ ዋጋ መልሶ ጨመረ

    ወሳኙ የሆርሙዝ ወሽመጥ ስለመከፈቱ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ስምምነት ለመድረስ የሚያስችል ሁኔታ ባለመኖሩ የነዳጅ ዋጋ ቅዳሜ እና እሁድ ከነበረበት ጭማሪ አሳየ።

    አሜሪካ የባሕር ላይ መተላለፊያ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲከፈት ብትፈልግም ኢራን ግን ከዚያ በፊት መሟላት ያለባቸው ስድስት ጉዳዮችን አቅርባለች።

    ሮይተርስ እንደዘገበው ዛሬ ሰኞ ማለዳ በእስያ ገበያ ላይ የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል ወደ አንድ ዶላር የሚጠጋ ጭማሪ አሳይቶ 84.46 ዶላር ሲሆን፣ የአሜሪካ ዌስት ቴክሳስ ድፍድፍ ነዳጅ በበርሜል 61 ሳንቲም ጨምሮ 78.79 ሆኗል።

    ኢራን እና ኦማን የሆርሙዝ ወሽመጥን መልሶ ለመክፈት ከስምምነት ይደርሳሉ በሚል ተስፋ ባለፈው ሳምንት የነዳጅ ዋጋ ከሰባት ፐርሰንት በላይ ቅናሽ አሳይቶ ነበር።

    አሜሪካ በኢራን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ተከትሎ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ቁጥጥር በማድረግ ጥቃቶችን በመፈጸሟ የመርከቦች እንቅስቃሴ ተገትቶ ቆይቷል። በዚህም የነዳጅ ዋጋ ላይ ተጽእኖ ተፈጥሮ ቆይቷል።

  5. እስራኤል የትራምፕን ባለ 15 ነጥብ የጋዛ ሰላም ዕቅድ ውድቅ ማድረጓን ኔታንያሁ ተናገሩ

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የአሜሪካውፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡትን ባለ 15 ነጥብ የጋዛ ሰላም ዕቅድ ውድቅ ማድረጋቸውን ገለጹ።

    ኔታንያሁ የሰላም ዕቅዱን ውድቅ ለማድረግ የሰጡት ምክንያት በቅድሚያ ሐማስ ትጥቅ መፍታት አለበት የሚል ነው።

    የትራምፕ የሰላም ቦርድ ባለፈው ወር ሐማስ እና ሌሎች በጋዛ የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች “ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈቱ” ከስምምነት ላይ መደረሱን ተናግሮ ነበር።

    ነገር ግን ሐማስ ከባድ መሣሪያዎቹን የሚያስረክበው እስራኤል “ማንኛውም ጥቃትን” ስታቆም እና ወታደሮቿን ከጋዛ ስታስወጣ መሆኑን ተናግሯል።

    እስራኤል በጥቅምት ወር የመጀመርያው የተኩስ አቁም ከተደረሰ በኋላ በጋዛ ጥቃት መፈጸሟን ቀጥላለች።

    ኔታንያሁ እሁድ ዕለት ለተሰበሰበው ካቢኔያቸው “እስራኤል ባለ 15 ነጥብ ሰነዱን ውድቅ አድርጋለች” ተናግረዋል።

    የእስራኤል ጦር “ሐማስ በትክክል ትጥቅ እስኪፈታ ድረስ [ከጋዛ] አይወጣም፤ እንዲሁም በዜጎቻችን እና በወታደሮቻችን ላይ የሚቃጣን ማንኛውም ስጋት ይቀለብሳል” ሲሉ ተናግረዋል።

    እሁድ ዕለት የሐማስ ባለሥልጣን ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ ቡድኑ ለስምምነቱ ያለውን ቁርጠኝነት "እንደገና ያረጋግጣል"፤ እንዲሁም የ15 ነጥብ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ "በቁም ነገር እና በኃላፊነት ስሜት ለመሳተፍ" ዝግጁ ነው ብለዋል።

    በተጨማሪም አደራዳሪዎች “ስምምነቱን ሁሉም አካላት ተግባራዊ ማድረጋቸውን አንዲያረጋግጡ” ጥሪ አቅርበዋል።

    እስራኤል ዕቅዱን ውድቅ ማድረጓ መስከረም ወር ላይ ትራምፕ ያቀረቡት የጋዛ ዕቅድ ችግር እንደገጠመው ማሳያ ተደርጎ ተቆጥሯል።

    ዕቅዱ የሰላም ቦርድ መመስረትን፣ የሐማስ ትጥቅ መፍታትን፣ የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ መውጣትን እና የጋዛን መልሶ ግንባታ የያዘ ነው።

    የኔታንያሁ አቋም ብዙዎችን ያስገረመ አልነበረም። ግን ይህንን አቋማቸውን ለማሳወቅ ትንሽ ጊዜ ወስደዋል።

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር በትራምፕ ዕቅድ ደስተኛ አለመሆናቸው በግልጽ የሚታወቅ ነው። ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ የቅርብ አጋራቸውን ማስቆጣት አለመፈለጋቸው አቋማቸውን ለማዘግየታቸው እንደምክንያት ከተጠቀሱት ነገሮች መካከል አንዱ ነው።

    ትራምፕ "ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ለማምጣት ትልቅ እርምጃ" ብለው የጠሩትን ነገር ካሳወቁ ከአንድ ሳምንት በላይ ሆኖታል ።

    ሐማስ ትጥቅ ለመፍታት የተስማማው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠው ደግሞ እስራኤል ጦሯን ከጋዛ ማስወጣት እንዳለባት ነው።

    እሁድ ዕለት ኔታንያሁ እርሳቸው በሥልጣን ላይ እያሉ ይህ እንደማይሆን ለማሳየት ቆርጠው የተነሱ አስመስሏቸዋል።

    ሐማስ መጀመሪያ ትጥቅ መፍታት እንዳለበት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የይስሙላ ትጥቅ መፍታት” ሊሆን እንደማይችል ተናግረዋል።

    ኔታንያሁ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር ወደፊት እንዴት መቀጠል እንደሚቻል እየተወያዩ መሆኑን ተናግረዋል።

    “ሀሳቦች አሏቸው፤ አንዳንዶቹ ተቀባይነት ያላቸው ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ቅቡልነት የሌላቸው ናቸው፤ እናም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ እንዴት አቋም መያዝ እንዳለብን እናውቃለን” ብለዋል።