ቢቢሲ ለቀረበበት የ10 ቢሊዮን ዶላር ክስ የትራምፕ ቤተሰቦች በምስክርነት እንዲቀርቡ ጠየቀ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ቢቢሲ ዶናልድ ትራምፕ የመሰረቱበትን የ10 ቢሊዮን ዶላር የስም ማጥፋት ክስ ለመከላከል የትራምፕ ቤተሰብ አባላት ሰነዶችን እንዲያቀርቡ እና ምስክርነት እንዲሰጡ ፍርድ ቤቱ እንዲያዝ ጠየቀ።

የፍርድ ቤት ሰነዶች እንደሚያሳዩት የቢቢሲ ጠበቆች ባለፈው ግንቦት ወር ዶናልድ ትራምፕ ጁኒየርን፣ ኢቫንካ ትራምፕን እና ጃሬድ ኩሽነርን ሰነዶችን እንዲያቀርቡ እና ማስረጃ እንዲሰጡ ለማድረግ ሞክረው ነበር።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ የ2021ዱ የካፒቶል ሂል አመፅ ላይ የተሰራጨ ንግግራቸው የተለያየ ክፍልን ፓናሮማ ዘጋቢ ፊልም ወጥ አስመስሎ በማቅረቡ ቢቢሲን ከስሰዋል።

ቢቢሲ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ንግግር ለተቀናበረበት መንገድ ይቅርታ ጠይቆ የስም ማጥፋት ግን አይደለም ሲል አስተባብሏል።

በቅርቡ የቢቢሲ ጠበቆች ለፍርድ ቤት ባቀረቡት የአቤቱታ ማመልከቻ ላይ የትራምፕ የቤተሰብ አባላት ንግግሩን ለማቅረብ ስላሰቡበት ዓላማ "የግል እውቀት አላቸው" ሲሉ ተከራክረዋል።

ምስክርነታቸውን እና ሰነዶቻቸውን ከፕሬዚዳንቱ የስም ማጥፋት ክስ ጋር ተዛማጅነት እንዳላቸው ጨምረው አስረድተዋል።

ቀደም ሲል የአሜሪካ የኮንግረስ ኮሚቴ ባሰባሰበው ማስረጃ ላይ በመመስረት፣ ዶናልድ ትራምፕ ጁኒየር እና ኢቫንካ ትራምፕ አባታቸው ንግግራቸውን ሲያሻሽሉና ሲያቀርቡ በቦታው የነበሩ ሲሆን፣ ጃሬድ ኩሽነር ደግሞ የዓመፅ አጠቃቀምን የሚያወግዝ ሀሳብ አርቅቆላቸዋል።

ቢቢሲ በፍርድ ቤት የተሰጡ የትዕዛዝ ደብዳቤዎችን በአካል ለማድረስ የተደረጉ ሙከራዎች ስላልተሳኩ፣ በኢሜይል እና እውቅና ባለው የፖስታ አድራሻ እንዲላኩ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

በክስ መዝገቡ ላይ እንደሰፈረው ከሆነ የቢቢሲ የሕግ ቡድን ተወካይ በፍሎሪዳ በሚገኘው ቤታቸው ለኢቫንካ ትራምፕ እና ለጃሬድ ኩሽነር የጥሪ ወረቀት ለማቅረብ ሞክረው የነበረ ቢሆንም የፖሊስ የፍተሻ ኬላን አልፈው እንዳይገቡ ተከልክለዋል። በኋላም የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ የጥሪ ወረቀቶችን መቀበል እንደማይችል ተነግሯቸዋል።

በተመሳሳይ ሌላ የሕግ ተወካይ በኒውዮርክ በሚገኘው የትራምፕ ታወር ውስጥ ለዶናልድ ትራምፕ ጁኒየር መጥሪያ ለማቅረብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም እንደዚህ ዓይነት ሰነዶችን የሚረከበው የሕንጻው ሠራተኛ ምሳ ላይ መሆኑ እንደተነገራቸው በመዝገቡ ላይ ሰፍሯል።

ከሁለት ቀናት በኋላ በተደረገ ሌላ ሙከራ፣ ተወካዩ "የሕግ ክፍሉ" በዚያ ቀን አለመኖራቸው እንደተነገረው ለፍርድ ቤት በቀረበው የአቤቱታ ማመልከቻ ላይ ሰፍሯል።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ የሕግ ቡድን አስተያየት እንዲሰጥ ቢጠየቅም ፈቃደኛ አልሆነም።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በታኅሳስ ወር ቢቢሲ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2024 ያስተላለፈው ዘጋቢ ፊልም ላይ ከተደረገው አርትኦት ጋር በተያያዘ ክስ መስርተዋል።

ቢቢሲ ስሜን አጥፍቷል፣ የንግድ ሕግንም ጥሷል ሲሉ ትራምፕ ተቋሙን በፍሎሪዳ ፍርድ ቤት ከስሰዋል።

ፕሮግራሙ ከትራምፕ ንግግሮች መካከል ከ50 ደቂቃ በላይ ልዩነት ያላቸውን ሁለት ንግግሮች በአንድ ላይ በማጣመር የካፒቶሉን ግርግር እየቀሰቀሰ ነው የሚል ግምት ፈጥሯል።

ዘጋቢ ፊልሙ ትራምፕ ለደጋፊዎቻቸው ሰላማዊ ሰልፍ እንዲያደርጉ እፈልጋለሁ ያሉበትን ክፍልም አስወግዶ ነበር።

ቢቢሲ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ንግግር ለተቀናበረበት መንገድ ሊቀመንበሩ ሳሚር ሻህ ለዋይት ሐውስ በላኩት ደብዳቤ ይቅርታ ጠይቋል።

ቢቢሲ የቪድዮ ክሊፕ በተስተካከለበት መንገድ ከልቡ ቢፀፀትም፣ የስም ማጥፋት መባሉን እንደማይሳማማ በደብዳቤው ገልጿል።

ቢቢሲ ፕሮግራሙ የስም ማጥፋት ሕጋዊ መስፈርቶችን የማያሟላ እና በአሜሪካ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ያልተላለፈ መሆኑን በመግለጽ ክሱ ውድቅ እንዲደርግ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ባለፈው ወር የትራምፕ ጠበቆች ዘጋቢ ፊልሙ በአሜሪካ ውስጥ እንደሚገኝ የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ እንደሌላቸው አምነዋል።

ትራምፕ በቅርቡ ቢቢሲ "ዘጋቢ ፊልሙን በመስራት ወይም በማዘጋጀት ረገድ ምንም ዓይነት ሚና እንደሌለው" ከተከራከረ በኋላ የቢቢሲ የንግድ ክንፍ የሆነውን ቢቢሲ ስቱዲዮስን ከክሱ ለመሰረዝ ተስማምተዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ጉዳዩን የሚመለከቱት ዳኞች ትራምፕ የፋይናንስ ሰነዶችን ለቢቢሲ በማስረከብ ረገድ እንዲዘገዩ ያቀረቡትን ጥያቄ ተቀብለዋል።

ዶክመንተሪው በንግድ ሥራቸው ላይ ጉዳት አድርሷል የሚለውን የትራምፕን ንግግር ለመመርመር ቢቢሲ አንዳንድ የፋይናንስ መዝገቦቻቸው እንዲሰጡት ጠይቋል።

የትራምፕ ሕግ ቡድን ግን የፋይናንስ ሰነዶችን ይፋ ማድረግ "የማይቀለበስ ጉዳት ያደርሳል" ሲሉ ተከራክረዋል።

ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት እአአ ለየካቲት 2027 ቀጠሮ ሰጥቷል።