በጦርነት እየታመሰች ባለችው ሱዳን ረሃብ መከሰቱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በጦርነት እየታመሰች ባለችው ሱዳን “በሁሉም አካባቢ ሊባል በሚችል ሁኔታ” ረሃብ መከሰቱን የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ለቢቢሲ ቱደይ ፕሮግራም ተናገሩ።

ዋና ዳይሬክተሩ ቴድሮስ አድሃኖም ይህን ያሉት ሱዳንን ጎብኝተው ከተመለሱ በኋላ ነው።

“በሱዳን ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ነው። በገፍ የሚፈናቀለው ሰው ብዛት አሁን በዓለም ከፍተኛው ሆኗል። ረሃብም እንደዚያው” ብለዋል ዳይሬክተሩ።

ዶክተር ቴድሮስ በአገሪቱ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ 12 ሚሊዮን ሰዎች መፈናቀላቸውን እና ለሱዳን የተሰጠው ዓለም አቀፍ ትኩረት በጣም አነስተኛ መሆኑን ገልጸው፣ ለዚህም ምክንያቱ የዘር መድልዎ ነው ብለዋል።

በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 2023 በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) መካከል የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።

“ውድመት፣ መፈናቀል፣ እዚህም እዚያም በሽታ፣ አሁን ደግሞ ረሃብ . . እስኪ አስቡት” ብለዋል ዶ/ር ቴድሮስ ለቢቢሲ ሲናገሩ።

በቅርቡ በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች የተጠለሉበትን ካምፕ እና በሱዳን የሚገኝ ሆስፒታልን እንደጎበኙ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ እዚያም በረሃብ ቆዳቸው አጥንታቸው ላይ የተጣበቀ በርካታ ሕጻናትን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

የሱዳንን ሕዝብ ግማሽ የሚያክለው ወደ 25 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ድጋፍ እንደሚፈልጉም ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል።

“ሱዳን የሚገባትን ያህል ትኩረት እያገኘች አይደለም” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በቅርቡ በሌላ የአፍሪካ አገር በተከሰተ ግጭት ተመሳሳይ ችግር ታይቶ እንደነበርም አውስተዋል።

“እኔ እንደማስበው እዚህ ላይ ያለው ጉዳይ የዘር መድልዎ ነው። አሁን የሚሰማኝ ይህ ነው። አሁን አካሄዱን እያየነው ነው። በተለይ ለአፍሪካ የሚሰጠው ትኩረት በጣም በጣም ዝቅተኛ ነው” ብለዋል።

በሱዳን ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ይህንን ችግር መመልከታቸው እንደሚያሳዝን የገለጹት ዶ/ር ቴድሮስ፣ “የጦርነትን ሽታ፣ የጦርነትን ድምጽ፣ የጦርነትን ምሥል አውቃለሁ። በመሆኑም ጦርነቱ እንዴት ሌሎችን እንደሚጎዳ መረዳት እችላለሁ። ልጅ እያለሁ እናቴ እኔ እድተርፍላት ስትፀልይ ትዝ ይለኛል። በሕይወት መትረፍ ትልቁ ነገር ነበር ። በሱዳን እና በጋዛም ተመሳሳይ ነገር እያየሁ ነው” ብለዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2022 ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ መፈፀሟን ተከትሎ ዶ/ር ቴድሮስ “ዓለም ለጥቁሮች እና ለነጮች ሕይወት እኩል ትኩረት እየሰጠ አይደለም” ሲሉ ተናግረው ነበር።

ለዩክሬን ከሚጎርፈው እርዳታ በሌሎች አገራት ላሉ የሰብዓዊ ቀውሶች የተለገሰው ሽራፊው ብቻ እንደሆነ በመግለጽ በኢትዮጵያ- ትግራይ፣ በየመን፣ በአፍጋኒስታን እና በሶሪያ ውስጥ ላለው ሰብዓዊ ቀውስ ተመሳሳይ ድጋፍ እንዳልተደረገ በወቅቱ አስረድተዋል።

በሱዳን ያለውን ሁኔታም “አሳዛኝ ነው” በማለት መገናኛ ብዙኃን የበለጠ ትኩረት እንዲሰጧቸው አሳስበዋል።

ነሐሴ ላይ በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው የባለሙያዎች ኮሚቴ በጦርነቱ ክፉኛ በተጎዳው ዳርፉር ክልል በሚገኘው አል ፋሽር ከተማ 500 ሺህ ተፈናቃዮች ተጠልለው በሚገኙበት ካምፕ ረሃብ መከሰቱን አውጆ ነበር።

የሱዳን የጦር መሪ ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) አዛዥ ሞሐመድ ሃምዳን ደጋሎ ወደ የእርስ በርስ ጦርነት ከመግባታቸው በፊት በ2021 በጋራ በአል በሽር መንግሥት ላይ መፈንቅለ መንግሥት አካሂደው ነበር። ሆኖም ባለፈው ዓመት ሱዳንን ወደ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ አስገብተዋታል።

ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ አርኤስኤፍን በገንዘብ እና በጦር መሣሪያ በመደገፍ ትከሰሳለች። ኤምሬትስ ግን የሚቀርብባትን ወቀሳ አስተባብላለች።

በሌላ በኩል ደግሞ ሳዑዲ አረቢያ ከሱዳን መንግሥት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላት ይነገራል።

ግጭቱን ለማስቆም በሳዑዲ አረቢያ እና በአሜሪካ አሸማጋይነት በርካታ የድርድር ጥረቶች ቢደረጉም ሳይሳኩ ቀርተዋል።