ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አርሰናል ራይስን ለማስፈረም የቀደመ ይመስላለ፤ ዩናይትድ ለማውንት ስንት ይከፍላል? የማጓየርና ምባፔ ዕጣ ፈንታስ?
የዝውውር ጭምጭምታዎች እየተጧጧፉ ነው። የተጫዋቾች ዝውውርም ደርቷል።
ከእንግሊዝ ስንጀምር፤ የቼልሲው አማካይ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ የሚያቀና ይመስላል።
አርሰናል፤ የዌስትሃሙን ዴክለን ራይስ ለማስፈረም በሚደረገው ውድድር ቀዳሚ የሆነ ይመስላል።
ነገር ግን 90ሚን እንደሚለው መድፈኞቹ የዌስትሃም የጥሪ ዋጋ ላይቋቋሙት ይችላሉ።
የ24 ዓመቱ እንግሊዛዊ ሜሰን ማውንት በዩናይትድ ቅድሚያ እንደሚሰጠው ጊቭ ሚ ስፖርት ቢዘግብም ዋጋው የተወደደ ይመስላል።
ማንቸስተር ዩናይትድ ለተጫዋቹ ከ60 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ እንደማይከፍል ተሰምቷል።
ስፖርት ዊትነስ ደግሞ ኒውካስል ዩናይትድ ለአርቢ ሊፕዚግ አማካይ ከበድ ያለ ገንዘብ ሊያወጣ እንደሚችል ፅፏል።
የ22 ዓመቱ ሃንጋሪያዊ ዶሚኒክ ወደ ሴይንት ጄምስ ፓርክ ይመጣል አይመጣም በሚመጣው ክረምት የሚለይ ይሆናል።
እንግሊዛዊው ተከላካይ ሃሪ ማጓየር ኦልድ ትራፈርድን አልለቅም የሚል ከሆነ ማንቸስተር ዩናይትድ ኪምን የማምጣቱ ነገር ስጋት ላይ ሊወድቅ ይችላል።
የ26 ዓመቱ ደቡብ ኮሪያዊ ኪም ሚን-ጄ ከናፖሊ ወደ ማንቸስተር ሊሄድ እንደሚችል 90ሚን አስነብቧል።
ዌስትሃም፤ ዴክለን ራይስን ለአርሰናል አሊያም ለሌላ ክለብ የሚሸጠው ከሆነ የፉልሃሙን ፖርቹጋላዊ አማካይ ለማስፈረም እንዳቀዱ ቶክስፖርት ዘግቧል።
ዩናይትድ የፖርቶውን በረኛ ዲዮጎ ኮስታ ማስፈረም ይሻል። ቢሆንም ፖርቶ ለ23 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ 64 ሚሊዮን ፓውንድ ክፈሉኝ እያለ ነው።
በዘንድሮው የክረምት የዝውውር መስኮት ከበርካታ ተጫዋቾች ጋር ስሙ እየተነሳ ያለው ዩናይትድ ጀረሚ ፍሪምፖንግን ሊያስፈረም እንደሚችል ስካይ ስፖርት ይፋ አድርጓል።
የጀርመኑ ባየርን ሊቨርኩሰን የ22 ዓመቱን ኔዘርላንዳዊ ለመሸጥ 34 ሚሊዮን ፓውንድ ይፈልጋል።
30 ሚሊዮን ፓውንድ የወጣለት የቦሩሲያ ሞንቼንግላድባኽ ፈረንሳዊ አማካይ ማኑ ኮኔ በሊቨርፑል ቢፈለግም ተጫዋቹ ወደ እንግሊዝ የመምጣቱ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል።
አስተን ቪላና ቶተንሃም የ23 ዓመቱን ጣሊያናዊ አጥቂ ኒኮሎ ዛኒዮሎ ለማስፈረም ፉክክር ውስጥ ገብተዋል።
30 ሚሊዮን ፓውንድ የመልቀቂያ ገንዘብ የሚጠይቀው ዛኒዮሎ አሁን ለጋላታሳራይ እየተጫወተ ሲሆን በጁቬንቱስና በኤሲ ሚላንም ይፈለጋል።
የሪያል ማድሪድ ፕሬዝደንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ፈረንሳዊውን ኮከብ ለማስፈረም እንደሚሹ ይፋ አድርገዋል።
ነገር ግን የ24 ዓመቱን ኪሊያን ምባፔ “ዘንድሮ ማምጣት አንፈልግም” ብለዋል ሲል ማድሪድ ኤክስትራ ፅፏል።
ዘ አትሌቲክ እንደዘገበው አርሰናል የ22 ዓመቱን ፈረንሳዊ ተከላካይ ዊሊያም ሳሊባ ለአራት ተጨማሪ ዓመታት አስፈርሟል።