አርሰናል ራይስና ካይሴዶን በአንድ ክረምት ማስፈረም ይችል ይሆን?

ታትሟል

አርሰናል በ92 ሚሊዮን ፓውንድ እንግሊዛዊውን አማካይ ለማዘዋወር የማይፈነቅለው ድንጋይ ያለ አይመስልም።

የ24 ዓመቱ ዴክለን ራይስ ከዌስትሃም ወደ አርሰናል ከሰሞኑ ሊዘዋወር ይችላል ሲል ቴሌግራፍ ፅፏል።

ዌስትሃም፤ ራይስን ለአርሰናል የሚሸጥ ከሆነ የፉልሃሙን ፖርቹጋላዊ የተከላካይ አማካይ ጃዎ ፓሊንሃን ሊያስፈርም ይችላል።

የማንቸስተር ሲቲው ካልቪን ፊሊፕስ አሊያም ከፕሪሚዬር ሊግ የወረደው ሳውዝአምፕተን አማካይ ጄምስ ዋርድ-ፕራውስም ወደ ዌስትሃም ሊመጡ ይችላሉ።

ቼልሲ፤ በራይስና በካይሴዶ ጉዳይ የአርሰናል ተቀናቃኝ ሆኖ ሊመጣ እንደሚችል 90ሚን ዘግቧል።

የለንደኑ ክለብ ቼልሲ ከራይስ በተጨማሪ የ21 ዓመቱን ኢኳዶራዊ የብራይተን አማካይ ሞይሰስ ካይሴዶን ሊገዛ ይችላል።

የ22 ዓመቱ የኒስ እና ፈረንሳይ የአማካይ ሥፍራ ተጫዋቹ ኬፍረን ቱራም ከሊቨርፑል ጋር ስምምነት ጨርሷል የሚለው ደግሞ ፉትቦል ትራንስፈርስ ነው።

ሌላኛው የዝውውር ጭምጭምታ የሚያሰራጨው ፋብሪዚዮ ሮማኖ የቼልሲው ክሮኤሻዊ አማካይ ማቴዎ ኮቫቺች ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ከስምምነት ደርሷል ብሏል።

ሮማኖ ከዚህ በተጨማሪ ሊቨርፑል የ22 ዓመቱን ፈረንሳዊ ማኑ ኮኔን ለማስፈረም ደፋ ቀና እያለ መሆኑን ጠቁሟል።

የስፔኑ ማርካ ጋዜጣ እንደገለጠው ሪያል ማድሪድ እንግሊዛዊውን አጥቂ ሃሪ ኬን በ68 ሚሊዮን ፓውንድ ለማስመጣት አቅዷል።

የቶተንሃም ሆትስፐር ሥራ አስኪያጅ ዳኒኤል ሌቪ የ29 ዓመቱን እንግሊዛዊ ለማንቸስተር ዩናይትድ አልሸጥም ማለታቸው ተሰምቷል።

ኒውካስል፤ ከእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ከወረዱ ቡድኖች ተጫዋቾችን ለመግዛት እየተሯሯጡ ነው።

ቴለግራፍ እንደፃፈው ኒውካስል የሊድስ ዩናይትዱን አሜሪካዊ አማካይ ቴይለር አዳምስን እንዲሁም የሌይስተሩን እንግሊዛዊ የመሃል መስመር ተጫዋች ጄምስ ማዲሰንን ወደ ሴይንት ጄምስ ፓርክ ሊያስመጣ ይችላል።

ነገር ግን ቶተንሃም ሆትስፐርም ጄምስ ማዲሰን ላይ ዓይኑን ጥሏል። ቢሆንም ሌይስተር ተጫዋቹን ከ50 ሚሊዮን ፓውንድ በታች የሚሸጥ አይመስልም።

ወደ ሳዑዲ ሊያቀና ይችላል የተባለለት የማንቸስተር ሲቲው አምበል ኢካይ ጉንዶዋን በፈረንሳዩ ኃያል እየተፈለገ ነው።

ፒኤስጂ የ32 ዓመቱን ጀርመናዊው አማካይ ለማስፈረም እንደሚሻ የፃፈው ለኤኪፕ ነው።

ከስፔን የሚወጡ ሪፖርቶች ደግሞ ጀርመናዊው አማካይ ከባርሴሎና ጋር የሶስት ዓመት ውል ገብቷል፤ ስምምነቱ ከአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ በኋላ ይፋ ይሆናል እያሉ መሆኑን ሙንዶ ዲፖርቲቮ አስነብቧል።

የሳዑዲው ክለብ አል አህሊ የአልጄሪያውን የ32 ዓመት የክንፍ መስመር ተጫዋች ሪያድ ማሕሬዝ ሊያስፈርም እንደሚሻ ሮማኖ ገልጧል።

ሜይል እንዳስነበበው ደግሞ ማንቸስተር ዩናይትድ የ21 ዓመቱን ሜሰን ግሪንውድ ለአውሮፓ ክለብ በውሰት መስጠት ይሻል።