የታሊባን መሪ የሸሪዓ ሕግ ቅጣቶች በአፍጋኒስታን እንዲተገበሩ አዘዙ

ታትሟል

የታሊባን መሪ ሀይባቱላህ አክሁንዛዳ በድንጋይ መውገርና የሰውነት ክፍልን በአደባባይ መቁረጥን ጨምሮ ሌሎችም ቅጣቶች በአፍጋኒስታን ውስጥ እንዲተገበሩ አዘዙ።

እንደ ዝርፊያ፣ እገታ እና አመጽ አነሳሽ ንግግር ወይም ጽሑፍ ጥፋተኛ የሆኑ ሰዎች በሸሪዓ ሕግ መሠረት እንዲቀጡ መሪው ማዘዛቸውን ቃል አቀባያቸው ተናግረዋል።

ታሊባን እአአ በ1990ዎቹ ሥልጣን ላይ ሳለ በአደባባይ በስቅላት መቅጣትን ጨምሮ ከላይ የተጠቀሱትን ቅጣቶች በመተግበሩ ውግዘት ገጥሞታል።

ከአንድ ዓመት በፊት ታሊባን ወደ ሥልጣን ሲመለስ እነዚህን ቅጣቶች ለማቅለል ቃል ገብቶ ነበር።

ሆኖም ግን ቀስ በቀስ የሴቶች መብትን ጨምሮ ሌሎችም ነጻነቶችን የሚገድቡ መርሆች እየተገበረ ይገኛል።

የታሊባን መሪም የአፍጋኒስታን ዳኞች የሸሪዓ ሕግን ተመርኩዘው ቅጣት እንዲበይኑ ወስነዋል።

የታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢቡላህ ሙጃሂድ በትዊተር ገጻቸው እንዳሉት፣ ይህ ውሳኔ የተላለፈው መሪው ከዳኞች ጋር ከመከሩ በኋላ ነው።

“የቀማኞች፣ የአጋቾች እና የአመጽ ቀስቃሾች ጉዳይ በትኩረት ታይቷል” ብለዋል።

የትኞቹ ቅጣቶች በሸሪዓ ሕግ እንደሚያስቀጡ በዝርዝር ባይታወቅም፣ አንድ የአፍጋኒስታን የሃይማኖት መሪ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ቅጣቶቹ በአደባባይ የሰውነት አካልን መቁረጥ፣ መግረፍና በድንጋይ መውገርን ይጨምራሉ።

ይህ ውሳኔ ታሊባን መብት እና ነጻነትን የሚገድቡ መርሆች እያወጣ ስለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ ነው ተብሏል።

ባለፈው ሳምንት ሴቶች ካቡል ውስጥ የሚገኙ ፓርኮችን እንዳይጎበኙ መከልከላቸው ይታወሳል።

ሴቶችን ከአደባባይ ሕይወት ከሚያርቁ ሕጎች መካከል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያ እንዳይሄዱ የሚከለክለው ይገኝበታል።

ታሊባን እንደሚለው “የእስልምና መርሆች እየተተገበሩ አልነበረም።”

ለ20 ዓመታት የቆየውን የውጭ አገራት ኃይል መውጣት ተከትሎ ታሊባን ወደ ሥልጣን ከተመለሰ ወዲህ፣ በመላው አፍጋኒስታን የሚታየው ነውጥ ቢቀንስም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተበራክተዋል።

ተቃዋሚዎች፣ ጋዜጠኞች እና ሴቶች የዚህ ጥሰት ቀዳሚ ዒላማ ናቸው።

ታሊባን እአአ ከ1996 እስከ 2001 ሥልጣን ላይ ሳለ የነበረው ዓይነት የሴቶች ጭቆና እንደማይኖር ቃል ቢገባም፣ ግማሽ የአፍጋኒስታን ሕዝብ በጥብቅ ገደብ ሥር ወድቋል።

ሴቶች ያለ ወንድ አጃቢ ረዥም ርቀት መጓዝ ተከልክለዋል። ታዳጊ ሴቶች እስከአሁን ወደ ትምህርት ቤት አልተመለሱም።

በጤና እና ትምህርት ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች ሥራ እንዲያቆሙም ታሊባን አዟል።

ከወራት በፊት ሴቶች በአደባባይ ፀጉራቸውን እንዲሸፍኑ የታዘዙ ሲሆን፣ መብታቸውን ለማስከበር የሞከሩ ሴቶች ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል።

ታሊባን ከሰብአዊ መብት፣ ከደኅንነት እና ከአስተዳደር ጋር በተያያዘ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የገባውን ቃል እስከሚጠብቅ ድረስ በርካታ ቢሊዮን ዶላሮችን እንዳያንቀሳቅስ ገደብ ተጥሎበታል።