በሆንዱራስ የሴቶች እሥር ቤት በተነሳ አመፅ ቢያንስ 41 ሰዎች ሞቱ

ታትሟል

ማክሰኞ በሆንዱራስ የሴቶች እሥር ቤት በተነሳ አመፅ ቢያንስ 41 ታራሚዎች ተገደሉ።

በሁለት ተቀናቃኝ አመፀኛ ቡድኖች መካከል ፀብ ከተነሳ በኋላ አንደኛው ቡድን የሌላቸውን ክፍል በእሣት ማጋየቱ ተሰምቷል።

ባለሥልጣናት እንደሚሉት ምንም እንኳ እሣቱ ለበርካታ ታሳሪዎች መሞት ምክንያት ቢሆንም የተወሰኑት በጥይት ተመትተው ነው የተገደሉት።

የሃገሪቱ ደኅንነት ሚኒስትር ዴኤታ ጁሊሳ ቪላኑዌቫ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጅዋል። አክለውም አመፁን ለማብረድ ቃል ገብተዋል።

ሚኒስትሯ የእሣት አደጋ ሠራተኞች፣ ፖሊስና ወታደራዊው ኃይል ‘በፍጥነት እንዲገባ’ አዘዋል።

“የሰዎች ሕይወት መጥፋት የምንታገሰው አይደለም” ብለዋል።

በእሣት አደጋው የሞቱት ሁሉም ታራሚዎች መሆናቸው ግልጥ አይደለም።

እሥር ቤቱ ከዋና ከተማዋ ቴጉሲጋልፓ 20 ኪሎ ሜትር ያክል ርቆ የሚገኝ ሲሆን 900 ገደማ ታራሚዎችን ያስተናግዳል።

በርካታ ታራሚዎች በአደጋው ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

የታራሚዎችን ቤተሰቦች የምትወክለው ዴልማ ኦርዶኔዝ እሥር ቤቱ “ሙሉ በሙሉ ወድሟል” ስትል ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግራለች።

ባለፈው ዓመት አመፀኛ ቡድኖች ላይ ዘመቻ ለመክፈት ቃል የገቡት ፕሬዝደንት ዢያሞራ ካስትሮ በተፈጠረው ነገር “እጅጉን ደንግጫለሁ” ሲሉ በማሕበራዊ ሚድያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ፕሬዝደንቷ፤ በምላሹ “ከባድ እርምጃ” እንደሚወስዱ ገልጠዋል።

የደኅንነት ሚኒስትር ዴኤታዋ ቪላኑዌቫ ምርመራ መከፈቱን አሳውቀዋል።

“እሥር ቤት ውስጥ ከአደገኛ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ያላቸው ሁሉ” ለፍርድ ይቀርባሉም ብለዋል።

ሆንዱራስ እንዲሁም ጎረቤቶቿ አል ሳልቫዶር እና ጓቲማላ ከደቡብ አሜሪካ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለሚጓዝ ኮኬይን መንገድ ናቸው።

ሆንዱራስ ከአደገኛ ቡድኖች ጋር በተያያዘ እሥር ቤቶቿ ብዙዉን ጊዜ በአመፅ ይታመሳሉ።

በ2019 በሰሜናዊቷ ከተማ ቴላ እሥር ቤት ውስጥ በተነሳ አመፅ 18 ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።