በአዲስ አበባና አካባቢዋ በሐምሌ ብቻ ዘጠኝ ሰዎች ወንዝ ገብተው መሞታቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Mayor Office of Addis Ababa
በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም. ብቻ በአዲስ አበባ እና በአካባቢዋ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ዘጠኝ ሰዎች ወንዝ ውስጥ ገብተው ሕይወታቸው እንዳለፈ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ወንዝ ውስጥ ገብተው ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች በተደጋጋሚ እየተሰማ ነው።
ከሞቱት ሰዎች ሁለቱ አስክሬናቸው የተገኘው ሐምሌ 26፣ 2014 ዓ.ም. እንደሆነ ገልጸዋል።
ከእነዚህ ሰዎች መካከል ዋና ሳይችሉ ወንዝ ውስጥ ወይም ውሃ ያቆረ ጉድጓድ ውስጥ ገብተው ለመዋኘት ሲሞክሩ የሞቱ ሰዎች ይገኙበታል። የተቀሩትን ሰዎች ለሕልፈት የዳረጋቸው ምን እንደሆነ ፖሊስ እያጣራ እንደሚገኝም አክለዋል።
በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ወንዝ ውስጥ ገብተው ለሽያጭ የሚውል ቁሳቁስ ለመልቀም ሲሞክሩ ወይም ወንዝ ለመሻገር ሲሞክሩ የሚሞቱ ሰዎች እንዳሉም ተናግረዋል።
የሞቱት ሰዎች በአጠቃላይ ወንዶች እንደሆኑ እና አራቱ ወጣቶች መሆናቸውን አቶ ንጋቱ ገልጸዋል። ዕድሜያቸውም ከ18 እስከ 60 ይደርሳል።
“ወንዝ ውስጥ ከመግባት ጋር በተያያዘ በአንድ ወር ዘጠኝ ሰው ሲሞት ብዙ ቁጥር ነው” ያሉት አቶ ንጋቱ፤ በአጠቃላይ በ2014 ወደ 115 ሰዎች ከአደጋ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን እንዳጡ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከእነዚህ መካከል 14ቱ በእሳት አደጋ ሲሞቱ የተቀሩት ወንዝ ውስጥ ለመዋኘት ገብተው የሞቱ፣ በግንባታ ስፍራዎች በሚደርስ አደጋ የሞቱና በሌሎችም ምክንያቶች ሕይወታቸው ያለፉ እንደሆኑ አስረድተዋል።
ከጎርፍ ጋር በተያያዘ ሁለት ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው ተናግረዋል።
በተለይ ያለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ ከተማ፣ በለሚ ኩራ እና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ጎርፍ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።
ቅዳሜና እሑድ በጎርፍ የደረሰውን የንብረት ውድመት ሳይጨምር፣ ክረምት ከገባ ወዲህ ከጎርፍ አደጋ ጋር በተያያዘ ወደ 3 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ንብረት እንደወደመ አክለዋል።
የ2014 ዓ. ም. የክረምት ዝናብ ከፍተኛ እንደሚሆን አስቀድሞ መተንበዩ አይዘነጋም።
እነዚህ ወደ ኮሚሽኑ ሪፖርት የተደረጉ አደጋዎች ሲሆኑ ለእነሱ ሪፖርት ሳይደረጉ የደረሱ ጉዳቶች እንደሚኖሩም አስረድተዋል።
ዘንድሮ ዝናብ ከፍተኛ ሊሆን እንሚችል በመገመቱ በ61 አካባቢዎች 161 ተጋላጭ ቦታዎች ተለይተው የድጋፍ ግንብ መሥራት፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች ማስተካከል፣ ማኅበረሰቡን ማስተማር፣ አለፍ ሲልም ለጎርፍ አደጋው ተጋላጭ የሆኑ ወንዝ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን ወደተሻለ ቦታ እንዲዛወሩ መደረጉን አቶ ንጋቱ ተናግረዋል።
በጎርፍ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ጊዜያዊ መጠለያ እየተሰጠ እንደሆነም ሳይጠቅሱ አላለፉም።
አምና በጎርፍ አደጋ አስር ሰዎች ሲሞቱ ወደ 4.7 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረትም ወድሟል።
“ዘንድሮ የዝናቡ መጠን ጨምሯል። ጎርፉም በመጠን ከፍተኛ ነው። በተመሳሳይ ቦታ አደጋ እያጋጠመ ነው። ተጋላጭ ቦታዎች ተለይተው ምን መደረግ እንዳለበት አቅጣጫ ባይቀመጥ ከዚህ ከፍ ያለ ጉዳትም ሊደርስ ይችላል። ነገር ግን የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ ተሠርቷል። . . . አምና ያጋጠመን ነገር ዘንድሮ ይገጥመናል ብዬ አላስብም” ብለዋል።












