ረቡዕ ዕለት አዲስ አበባ ውስጥ በጎርፍ የተወሰደ ታዳጊ እየተፈለገ ነው

የፎቶው ባለመብት, sm
በአዲስ አበባ ከተማ ትናንት ረቡዕ ሰኔ 01/2014 ዓ.ም. በጎርፍ የተወሰደ ታዳጊ በአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እና በነዋሪ እየተፈለገ ነው ተባለ።
የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ረቡዕ ዕለት ጉለሌ ክፍለ ከተማ ላዛሪስ ትምህርት ቤት አካባቢ በጎርፍ የተወሰደ ታዳጊ እየተፈለገ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ከሰዓት በኋላ 9፡37 አካባቢ ይሆናል። . . . ከትምህርት ቤት ወደ መኖሪያ ቤቱ እየሄደ የነበረ እድሜው ከ4 እስከ 6 ዓመት የሚገመት ታዳጊ በጎርፍ ተወስዷል የሚል መረጃ ደርሶናል” ብለዋል።
ይህ መረጃ ለከተማዋ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከደረሰ በኋላ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ጨምሮ ነዋሪዎች ተሰማርተው ታዳጊውን ለማግኘት ፍለጋ እያደረጉ ነው።
አቶ ንጋቱ ታዳጊው በጎርፍ ተወስዷል የተባለበት አካባቢ ወንዝ አለመኖሩን ተናግረው ከአካባቢው ሰዎች ታዳጊው የተወሰደው በፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ በመጣ ጎርፍ ነው መሆኑን ጥቆማ እንደደረሳቸው ተናግረዋል።
“ቱቦዎችን ከፋፍተን አይተናል እስካሁን ምንም ነገር የለም። ወደ ዋና ወንዝ ተቀላቅሎ ከሆነ በሚል እስከ አፍንጮ በር ድረስ ሄደን ፈልገናል። . . . አቃቂ አባ ሳሙኤል ተብሎ ወደሚጠራው ወንዝ ድረስ ሄደን እንፈልጋለን” ብለዋል።
አቶ ንጋቱ ጨምረውም “በሙሉ አቅማችን እየፈለግን ነው። የአካባቢው ወጣቶች እና የፖሊስ አባላት ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ነው። አነፍናፊ ውሾችም እንዲሳተፉ ተደርጓል እስካሁን ግን አልተገኘም” በማለት ታዳጊውን ለማግኘት እየተደረገ ያለውን ጥረት አስረድተዋል።
አደጋው ረቡዕ ዕለት ማጋጠሙንና የታዳጊውን እድሜ ከግምት በማስገባት በጎርፍ ተወስዷል የተባለውን ልጅ በሕይወት የማግኘት እድሉ ጠባብ መሆኑን አቶ ንጋቱ አመልክተዋል።
በአዲስ አበባ በአንድ አካባቢ ዝናብ ሲጥል በሌላ አካባቢ ጎርፍ የመከሰት አጋጣሚ እንዳለ የሚናገሩት አቶ ንጋቱ፤ ጉለሌ አካባቢ ለከፍተኛ ጎርፍ የሚዳርግ ዝናብ ባይዘንብም ጉለሌ ለእንጦጦ ባለው ቅርበትና ተዳፋት በመሆኑ ለጎርፍ ተጋላጭ ያደርገዋል ብለዋል።
የክረምት ወቅት መጀመሩን ተከትሎ በሚኖረው ከፍተኛ የዝናብ ስርጭት የጎርፍ አደጋ ሊከሰት ስለሚችል ነዋሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ባለሙያዎች ይመከራሉ ነው።
በየዓመቱ በክረምት ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች በተለያዩ ምክንያቶች በመዘጋታቸው የተነሳ ለመንገዶች መዘጋት እንዲሁም ለንብረት ውድመት ምክንያት ሲሆኑ ቆይተዋል።
በተጨማሪም ከፍተኛ ዝናብ በሚጥልበት ጊዜ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ወንዞች በመሙላት የሚያስከትሉት ጎርፍ በዳርቻዎቻቸው ያሉ መንደሮችን በማጥለቅለቅ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማጋጣሙ የሚታወስ ነው።













