ሩሲያ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ 'ስሜታዊነት' ይታይባቸዋል አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ክሬምሊን ዶናልድ ትራምፕ 'ስሜታዊነት' እየታየባቸው ነው አለ።
ሩሲያ ይህን ያለችው ትራምፕ ፕሬዝደንት ፑቲን "ፍፁም ቀውስ ናቸው" ማለታቸውን ተከትሎ ነው።
ሩሲያ ከቀናት በፊት ዩክሬን ላይ በ367 ድሮን እና ሚሳዔል ታግዛ ከባድ ጥቃት የፈፀመች ሲሆን 13 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
ትራምፕ እሑድ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ሚድያቸው ፑቲን "አንድ ነገር ሆነዋል" ብለዋል።
"ፍፁም አብደዋል" ያሉት ትራምፕ "ያለ አንዳች ምክንያት ሰዎችን እየገደሉ ነው" ሲሉ ፑቲንን ወቅሰዋል።
የፑቲን ቃል አቀባይ የሆኑት ድሚትሪ ፔስኮቭ ትራምፕ ያሰሙት ንግግር "በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች የሚያንፀባርቁት ስሜታዊ ጫና ነው" ብለዋል።
የጀመርኑ መራሔ መንግሥት ፍሬድሪክ ሜርዝ በበኩላቸው የዩክሬን አጋሮች ለኪየቭ የሚሰጠው የጦር መሣሪያ ድጋፍ ገደብ እንዳይኖረው አድርገዋል ብለዋል።
ጀርመን ታውረስ የተሰኙትን ሚሳዔሎች ለዩክሬን ሰጥታለች የሚሉ ዘገባዎች መሰማት ጀምረዋል።
ሩሲያ ቅዳሜ ምሽት በዩክሬን ያደረሰችው የአየር ድብደባ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ከባዱ የአየር ጥቃት ነው ተብሏል። የዩክሬን አየር ኃይል ትልቁ የድሮን ጥቃት ነው ብሏል።
ፔስኮቭ የአየር ድብደባው ዩክሬን የሩሲያ "ማኅበራዊ መሠረተ-ልማት" ላይ ላደረሰችው ጥቃት ምላሽ ነው ብለዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የአየር መቋቋሚያው በተለያዩ የሀገሪቱ ግዛቶች 20 የዩክሬን ድሮኖችን መመከት ችሏል።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ እሑድ ሩሲያ የወሰደችው የአየር ድብደባ "ምንም ዓይነት ወታደራዊ ትንታኔ የሚያስፈልገው አይደለም" ብለው "ፑቲን እና ሩሲያ መርጠው. . . ጦርነቱን ለመቀጠል እና ነብስ ለማጥፋት የሚያደርጉት ነው" ሲሉ ኮንነዋል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ዜሌንስኪ ረቡዕ ወደ ጀርመን ያቀናሉ። ነገር ግን ይህ ጉዟቸው እስካሁን ተጨባጭነት አላገኘም።
ከዚህ ቀደም የነበሩ የጀርመን መራሔ መንግሥታት ታውረስ ሚሳዔል ለዩክሬን በድጋፍ እንደማይሰጡ በግልፅ አስታውቀው ነበር።
ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ሌሎች ምዕራባዊያን የዩክሬን አጋሮች ለኪየቭ የመሣሪያ ድጋፍ ቢያደርጉም እንዴት ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት የሚደነግጉ ሕግጋት ያወጣሉ።
ታውረስ ሚሳዔል 500 ኪሎ ሜትር መምዘግዘግ የሚችል ሲሆን ሩሲያ ይህ መሣሪያ ለዩክሬን የሚቀርብ ከሆነ "እንደ አደገኛ እርምጃ ይወሰዳል" ብላለች።
ትራምፕ፤ ፑቲንን "ለረዥም ጊዜ አውቀዋለሁ። እንስማማለን። ነገር ግን ከተማዎች ላይ ሮኬቶች እያስወነጨፈ ሰዎችን እየገደለ ነው። ይህንን ነገር አልወደድኩትም" ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት አክለው ሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል ዝተዋል። ነገር ግን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ማዕቀብ እንደሚጥሉ ዛቻ ማሰማታቸው ይታወሳል።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገፃቸው በለቀቁት መልዕክት ትራምፕን ብቻ ሳይሆን የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዜሌንስኪንም ወርፈዋል።
ሩሲያ በአሁኑ ወቅት 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት በቁጥጥሯ ሥር አድርጋለች። ይህ ግዛት በአውሮፓውያኑ 2014 በሩሲያ የተያዘችው ክሬሚያን ያካትታል።















