በዩክሬን የተኩስ አቁም እንዲደረግ ቫቲካን የምታደራድር ከሆነ ጣሊያን ለመደገፍ ዝግጁ ነኝ አለች

የፎቶው ባለመብት, Ukrainian presidency handout
በዩክሬን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቫቲካን እንድታደራድር ያቀረቡትን ሀሳብ ጣሊያን እንደምትደግፈው አስታወቀች።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ቢሮ እንዳስታወቀው ጣሊያን በዩክሬን እና ሩሲያ መካከል "ግንኙነቶችን ለማመቻቸት እና ወደ ሰላም ለመራመድ" ዝግጁ መሆኗን ገልጾ፤ አዲሱ ሊቃነ ጳጳስ በቫቲካን ንግግር እንዲደረግ ያሳዩትን ፈቃድ በአዎንታዊ መልኩ እንቀበለዋለን ብሏል።
ይኹን እንጂ እስካሁን በቫቲካን ውይይት እንደሚደረግ ስምምነት ላይ አልተደረሰም።
ባለፈው አርብ በዩክሬን እና ሩሲያ ባለሥልጣናት መካከል በኢስታንቡል የነበረው ንግግር ሞስኮ ተጨማሪ ፍላጎት ከማንፀባረቅ ውጭ አንድ እርምጃ መሻገር አልቻለም።
ሊቃነ ጳጳስ ሊዮ ባለፈው ሳምንት ቫቲካን ባላንጣዎችን ለማቀራረብ "ሁሌም ዝግጁ" መሆናቸውን ገልፀው፣ ሰላም እንዲያሸነፍ "ሁሉንም ጥረት" እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
ሊቃነ ጳጳሱ ንግግሩን ማሰናዳት አሊያም ማደራደሩን ተስፋቸው እንጂ መሬት የረገጠ እቅድ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።
ቀጥተኛ ንግግር የሚቀጥል ከሆነ ዩክሬን ቫቲካን የንግግር አዘጋጅ መሆኗን ትቀበላለች።
ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ማክሰኞ ዕለት "ከሩሲያ ጋር ለመነጋገር መድረክ መፍጠርን" ጨምሮ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ጋር መነጋገራቸውን በኤክስ ገፃቸው ገልፀዋል።
በመሪዎቹ ንግግር ዜሌንስኪ ስዊዘርላንድን እና ቱርክን እንደ አማራጭ የንግግር ስፍራዎች ማቅረባቸውንም ጠቁመዋል።
ነገር ግን ክሬምሊን ለንግግር ቱርክን ልትመርጥ እንደምትችል ይጠበቃል። በኢስታንቡል የተጀመሩ ንግግሮች ተከታታይ እንዲሆኑ በተለይም ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በቱርክ ንግግር የተደረገበት ስምምነት እንዲቀጥል ይሻል።
ዩክሬን ወታደራዊ ኃይሏን መቀነስን ያካተተው ስምምነት አሁን ላይ ለኪየቭ የሚዋጥ አይደለም።
ሩሲያ ተጨማሪ ፍላጎቷን ያሳወቀች ሲሆን፤ ክሬሚያን ጨምሮ በሩሲያ በከፊል ለተያዙ አራት ግዛቶች ዩክሬን እውቅና እንድትሰጥ ጠይቃለች።
ለክሬምሊን ንግግሩ የሚደረግበት አገር ያን ያህል የሚያሳስበው ሳይሆን፤ ንግግሩ በቭላድሚር ፑቲን ፍላጎት ላይ እንዲሆን ግን ይሻል።
ትርጉም ያለው ንግግር ማድረግ እድሉ ዝቅተኛ እንደሆነም ይታመናል።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ግጭቶችን በማሸማገል ታሪክ ያላት ስትሆን፤ በሩሲያ የተወሰዱ የዩክሬን ህፃናትን ለማስመለስ እና እስረኞችን ለማስለቀቅ በነበሩ ንግግሮች ላይ ተሳትፋለች።
የአዲሱ ጳጳስ ተሳትፎም ለንግግሩ የተለየ አካሄድ ሊያመጣ እንደሚችል ይጠበቃል።












