ዲሞክራቷ ሕግ አውጭ የትራምፕ ስም ከኬኔዲ ማዕከል ይነሳ ሲሉ ከሰሱ

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Hulton Archive via Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተወካይዋ ጆይስ ቤቲ የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ስም ከጆን ኤፍ ኬኔዲ ማዕከል ይነሳ ሲሉ ክስ አቀረቡ።

ባለፈው ሳምንት በትራምፕ ደጋፊዎች የተሞላው የኬኔዲ ማዕከል ቦርድ በኬኔዲ ማዕከል የፐርፎርሚንግ አርትስ የተሰኘው ማዕከል ትራምፕ-ኬኔዲ ማዕከል ተብሎ እንዲሰየም ወስነዋል።

ቤቲ እና ሌሎች በርካታ ዲሞክራት ሕግ አውጭዎች በአሜሪካ ሕግ መሠረት የቦርዱ አባላት ተደርገው ይቆጠራሉ።

ዲሞክራቷ ፖለቲከኛ በክሳቸው ስያሜውን ለመቀየር "የኮንግረስ ይሁንታ" ያስፈልጋል ይላሉ።

የክስ መዝገቡ እንደሚለው ቦርዱ ስያሜውን ለመቀየር የተገኙት ቤቲ ተቃውሟቸውን ሊያሰሙ ሲሉ ድምፃቸውን እንዳይሰማ ተደርገዋል።

ቤቲ እንደሚሉት ኮንግረሱ ማዕከሉ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ኬኔዲ "ቋሚ መታሰቢያ" እንዲሆን ይፈልጋል።

"አምባገነን ገዥዎችን በሚያስንቅ መልኩ የወቅቱ ፕሬዝደንት እና ታማኝ ባለሟሎቹ ይህን ታሪካዊ ማዕከል ፕሬዝደንት ትራምፕ ብለው ሰይመውታል" ይላል የክስ መዝገቡ።

ዋይት ሐውስ ለቢቢሲ በላከው መግለጫ ፕሬዝደንት ትራምፕ የኬኔዲ ማዕከልን "ፋይናንሱን በማጠናከር፣ ሕንፃዎቹን በማዘመን እና ከፋፋይ የሆነው ግራ ዘመም አስተሳሰብ በማፍረስ" ታድገውታል ብሏል።

"በዚህ ምክንያት ነው የኬኔዲ ማዕከል በሙሉ ድምፅ ትራምፕ-ኬኔዲ ማዕከል ሲል ታሪካዊ ውሳኔ የወሰነው። ይህ ከአሜሪካ ታላላቅ የባሕል ማዕከላት አንዱ የሆነው ተቋም አዲስ የስኬት እና የኩራት ምዕራፍ ነው" ሲሉ የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ሊዝ ሂዩስተን ተናግረዋል።

ባለፈው አርብ የትራምፕ ስም በማዕከሉ ሕንፃ ላይ የተለጠፈ ሲሆን የማዕከሉ ድረ-ገፅ ላይ የሚታየው አዲሱ ስያሜ "የትራምፕ-ኬኔዲ ማዕከል" ይላል።

በስያሜው ቅር የተሰኘው ቻክ ሬድ የተሰኘው ሙዚቀኛ ላለፉት 20 ዓመታት በማዕከሉ ለገና በዓል ያቀርብ የነበረውን የጃዝ ኮንሰርት ሰርዟል።

ማዕከል የተገነባው በ1950ዎቹ ሲሆን ፕሬዝደንት ኬኔዲ በ1963 ከተገደሉ በኋላ የአሜሪካ ኮንግረሱ ማዕከሉን በስማቸው እንዲጠራ ወስኗል።

ትራምፕ ስልጣን በያዙ ማግስት ነው የማዕከሉን ቦርድ አባላት አሰናብተው በወዳጆቻቸው የተኩት። አዲስ የተሾሙት የቦርድ አባላት ትራምፕን የቦርዱ ሊቀ-መንበር አድርገው መርጠዋል። የትራምፕ የቅርብ አማካሪ የሆኑት ሪቻርድ ግሪኔል ደግሞ የቦርዱ ፕሬዝደንት ሆነው ተሹመዋል።

የማዕከሉ ድረ-ገፅ እንደሚለው ቦርዱ 34 በትራምፕ የተሾሙ እና 23 በአሜሪካ ሕግ መሠረት የተሰየሙ አባላት አሉት።

ትራምፕ ለማዕከሉ መልሶ ጥገና በሚል 257 ሚሊዮን ዶላር በጀት በኮንግረስ በኩል እንዲፀድቅ አድርገዋል።

በርካታ የፕሬዝደንት ኬኔዲ ቤተሰብ አባላት የማዕከሉን ስያሜ ተከትሎ በማኅበራዊ ሚድያ ገፆቻቸው የተሰማቸውን ቅሬታ ገልፀዋል።

የጆን ኤፍ ኬኔዲ ወንድም ልጅ የሆኑት እና የቀድሞው የሕዝብ እንደራሴዎች ምክርት ቤት አባል ጆ ኬኔዲ ሶስተኛ ስያሜውን ከተቃወሙ ሰዎች መካከል ናቸው።