የባለቤቱን አስክሬን ቆራርጦ በቦርሳ ይዞ ሲጓዝ የነበረው ግለሰብ በፖሊስ ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, DCI Kenya
የኬንያ ፖሊስ የተቆራረጠ አስክሬን በቦርሳ ይዞ ሲጓዝ የነበረን ግለሰብ በቁጥጥር ሥር አዋለ።
የ29 ዓመቱ ጆን ኪያማ ዋምቡያ አስክሬኑ የ19 ዓመት ሚስቱ እንደሆነ ተናግሯል። ፖሊስ በናይሮቢ ሁሩማ ግዛት ቅኝት ሲያደርግ ነው ግለሰቡን የያዘው።
ግለሰቡ ሕገ ወጥ ነገር እንደያዘ በመጠርጠር ፖሊስ አስቁሞት ቦርሳውን ሲፈትሽ የተቆራረጠ አስክሬን አግኝቷል።
የኬንያ ወንጀል ምርመራ "በጣም አስደንጋጭ ነበር" ሲል የገጠመውን ገልጿል።
ሴቶች ላይ የሚፈጸም ግድያ ከፍተኛ ከሆነባቸው አገሮች መካከል ኬንያ አንዷ ናት።
ግለሰቡ ላይ ፖሊስ ባደረገው ምርመራ ነው አስክሬኑ የባለቤቱ ጆይ ፍሪዳ ሙናኒ እንደሆነ የደረሰበት።
ፖሊስ የአስክሬኑን ቁርጥራጭ ሲያገኝ ግለሰቡ "እምብዛም እንዳልተደናገጠ" ተገልጿል።
ፖሊሶች ቤቱ ሲሄዱ ቢላ፣ ደም የተነከረ ልብስና ተጨማሪ የሰውነት ክፍሎች አግኝተዋል።
የኬንያ ወንጀል ምርመራ ድርጊቱን "አሰቃቂ" ሲል ገልጾታል። ተጠርጣሪው በቅርቡ በግድያ ክስ ፍርድ ቤት የሚቀርብ ይሆናል።
እአአ በ2024 ከነሐሴ እስከ ጥቅምት 97 ሴቶች መገደላቸውን የኬንያ ብሔራዊ ፖሊስ ገልጿል።
ባለፈው ወር በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች በሴቶች ላይ የሚደርስ ግድያና ጥቃትን በመቃወም በናይሮቢ ሰልፍ አካሂደዋል። ፖሊስ በአስለቃሽ ጭስ ሴቶቹን በትኗቸዋል።
ከዚህ ቀደም የኦሊምፒክ አትሌቷ ሬቤካ ቼፕቴጌ በፍቅረኛዋ መገደል ከፍተኛ ቁጣ አስነስቶ ነበር።
ሐምሌ ላይ ፖሊስ ሴቶችን አከታትሎ የሚገድል ግለሰብ በቁጥጥር ሥር አውሏል። ኮሊንስ ጁማሲ ካሉሻ የተባለው ግለሰብ ዘጠኝ ሴቶችን ገድሎ አስክሬናቸውን ቆራርጧል።
ከማረሚያ ቤት አምልጦ እስካሁን አልተያዘም።
ሪታ ዌይኒ የተባለችው ወጣት ተገድላ አስክሬኗ ተቆራርጦ መገኘቱም አይዘነጋም።












