አሜሪካን መስቀለኛ መንገድ ላይ ያስቀመጣት ስጋት የፈጠረው የቻርሊ ከርክ ግድያ

አሜሪካ ከባድ ቀናትን እያሳለፈች ነው። አገሪቱ ከዚህ የጥላቻ እና የአመጽ አዙሪት መውጣት ትችል ይሆን? በማለት የሚጠይቁ ጥቂቶች አይደሉም።
በአሜሪካ ታሪክ እጅግ አስደንጋጭ ነው የተባለለትን ግድያ ተከትሎ የዩታ ገዢ አሜሪካውያን የፖለቲካውን ውጥረት እንዲያረግቡ ተማጽነዋል። ከቻርሊ ከርክ ሞት በኋላ ሃሳባቸውን የሰጡ ሰዎች አገሪቱ በምትፈልገው መንገድ ላይ ትሆናለች ብለው አያስቡም።
ቢያንስ በቅርቡ አይሳካም። የቅርብ ጊዜ ታሪክ እንደሚያሳየው ከከባድ አደጋ በኋላ አሜሪካ ወደ አንድ ላለመምጣት የመረጠችባቸው ምሳሌዎች ብዙ ናቸው።
ከ14 ዓመታት በፊት የዲሞክራቲክ ኮንግረስ አባል አሪዞና ውስጥ በጥይት ከተመቱ በኋላ ይህ አልሆነም። ከስምንት ዓመታት በፊትም አንድ የሪፐብሊካን ኮንግረስ አባል በቤዝቦል ልምምድ ወቅት መገደላቸውም ምንም የፈጠረው ነገር የለም።
አሜሪካውያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው ወረርሽኝ ጊዜም አንድ ላይ ሊቆሙ አልቻሉም። እንዲያውም ኮቪድ ክፍፍሎቹን አባብሷል።

የፎቶው ባለመብት, OLIVIER TOURON/AFP via Getty Images
ምክንያቱ ቀላል ነው። ለመለወጥ ግን አስቸጋሪ። የአሜሪካን የፖለቲካ የሚያራግቡት ሰዎች እና መድረኮች ከዚህ የሚጠቀሙ ሲሆን ውጥረቱን የሚቀንሱት ግን ምንም አያገኙም።
በአገሪቱ የመሃሉን ፖለቲካ የሚያራምዱት ሳይሆን የፖለቲካ መሠረትን ባማከለ መልኩ ፖሊሲዎችን እና ንግግሮችን የሚሰብኩት ለፖለቲካ ሹመት የመመረጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው።
በተመሳሳይ በመገናኛ ብዙኃን ዘንድም ፖለቲካዊ አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች የበለጠ ጽንፈኛ በመሆናቸው እና ቁጣን በማነሳሳታቸው ይሸለማሉ። ብዙ ተመልካች ያገኛሉ፤ ይህም ተጨማሪ የማስታወቂያ ዶላር ለማግኘት መንገድ ይጠርግላቸዋል።
ይህ የማበረታቻ መዋቅር የዩታውን ገዢ ስፔንሰር ኮክስን የተለየ ያደርጋቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, REUTERS/Cheney Orr
ቻርሊ ከርክ ከተገደለ በኋላ አሜሪካውያን "መገናኛ ብዙሃንን ዘግተው፣ ስልክ አጥፍተው፣ ወጥተው እንዲዝናኑ፣ ቤተሰቦቻቸውን እንዲያገኙ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ መልካም ነገር እንዲሠሩ" አሳስበዋል።
ክፍፍሉ ጫፍ በደረሰበት ሜዳ ጤናማ የእርቅ ሃሳብ አቅርበዋል።
1960ዎቹ እና 70ዎቹ እና ዛሬ
ክፍፍል እና የፖለቲካ ጥቃቶች በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ አዲስ ክስተቶች አይደሉም። የዛሬ 160 ዓመት ገደማ አገሪቱ ከራሷ ጋር ጦርነት ውስጥ ገብታ ነበር።
በ1960ዎቹ አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ አንድ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ተገድለዋል። ወንድማቸውም ፕሬዝዳንት ለመሆን በዘመቻ ላይ እያለ ተገደለ። በዚያው ወቅት በአገሪቱ ታዋቂ የሆኑ ሁለት የሲቪል መብቶች መሪዎችም ተገድለዋል።
በ1970ዎቹ ደግሞ ፕሬዝዳንት ጀራልድ ፎርድ በሁለት የተለያዩ አጋጣሚዎች በጥይት ተመቱ። በ1980ዎቹ ሮናልድ ሬገን ወደ ሊሙዚናቸው ሲያቀኑ በጥይት ተመቱ።

የፎቶው ባለመብት, Heritage Space/Heritage Images via Getty Images
ባለፈው ዓመት ፔንስልቬኒያ ውስጥ ትራምፕ የመግደል ሙከራ ተደረገባቸው። ፍሎሪዳ ውስጥም አንድ ተመሳሳይ ሃሳብ የነበረው ታጣቂ ተያዘ። የታጣቂው ክስ የተጀመረው ከርክ በተገደለበት ሳምንት ነው።
ይህን ዘመን ከ1960ዎቹ እና 70ዎቹ ልዩ የሚያደርገው ነገር ገዥው ኮክስ ያሳስባቸዋል።
አሜሪካውያንን የበለጠ የሚከፋፍሉ ነገሮችን ቢቆጠቡም ይህንን እያፋፋሙ ነው ያሏቸውን የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎችን ከመክሰስ ግን ወደ ኋላ አላሉም።
"ባለፉት አምስት እና ስድስት ዓመታት ውስጥ ባየናቸው ግድያ እና የግድያ ሙከራዎች ውስጥ ማኅበራዊ ሚዲያ ቀጥተኛ ሚና ተጫውቷል ብዬ አምናለሁ" ሲሉ ኮክስ ተናግረዋል።
ምናልባት "ካንሰር" በአሜሪካ ማኅበረሰብ ላይ ያደረሰው ነገር በጣም ደካማ ሊሆን ይችላል ሲሉም አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Anna Moneymaker/Getty Images
አብዛኛዎቹ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በይፋ የተናገሩት ነገር የለም። ቢሊየነሩ የኤክስ አለቃ ኤለን መስክ "አክራሪ ግራ ዘመሞች የቻርሊ ከርክን ግድያ አወድሰዋል" ከማለት ባለፈ "ግድያን ከሚያወድሱ የክፋት ናፋቂዎች ጋር አንድ መሆን የማይቻል ነው" በማለት ገልጿል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ዙሪያ ስጋቶቹን "አንዳንድ ጊዜ በኤክስ ላይ የሚደረገው ውይይት አሉታዊ ሊሆን ቢችልም፣ አሁንም ቢሆን ውይይት መደረጉ ግን ጥሩ ነው" በማለት ስጋቱን ገልጿል።
"ይህ እንደ መጥፎ ጋብቻ ነው የሚቆጠረው"
ማኅበራዊ ሚዲያን ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር ለማዛመድበት ፍላጎት ያላቸውን ጭምር የሚያሳስብ ነው።
በዩታ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የቻርሊ ከርክ ድርጅት የሆነው የ'ተርንቲንግ ፖይንት ዩኤስኤ' ፕሬዝዳንት የሆነችው የ19 ዓመቷ ካትሊን ግሪፊትስ "በእርግጠኝነት ማኅበራዊ ሚዲያ ለሕብረተሰባችን በጣም ከባድ ነገር ነው" ስትል ተናግራለች።
"ካላችሁ የፖለቲካ አመለካከት ጋር ከማይስማማ ሰው ጋር እንኳን ውይይት ማድረግ አይቻልም። በእውነቱ ይህ አሳዛኝ ይመስለኛል።"
አሳዛኙ እና አስገራሚው ነገር ከርክ እራሱን የንግግር ነጻነትን የሚደግፍ አድርጎ ቢመለከትም፣ ተቺዎቹ ግን ብዙውን ጊዜ በዚህ ሃሳብ አይስማሙም። የእሱ ሞት አገሪቱን ከሰለጠኑ ንግግሮች የበለጠ ሊገፋት ይችላል።

የከርክን ሞተ ተከትሎ ግን የአሜሪካ የፖለቲካ ሰዎች ወደ የራሳቸው ምሽጎች አፈግፍገዋል።
አብዛኞቹ ግራ ዘመሞች ገዳዩ በበይነ መረብ እና በቡድን ውይይቶች ስር ነቀል የአመለካከት ለውጥ ሊያመጣባቸው የቻለባቸውን መንገዶች ለመመርመር ጓጉተዋል።
ብዙዎቹ በቀኝ በኩል ያሉት ደግሞ ተጠርጣሪው የግራ ክንፍ ሴራ አካል ስለመሆኑ ማወቅን ይመርጣሉ።
ሁለቱም ወገኖች ለእርቅ ወይም ለስምምነት ቅድሚያ ለመስጠት የሚፈልጉ አይመስልም።
እውነታው ግን አክራሪነትን የሚያጠኑ ሰዎች የአሁኑን ክፍፍል ለመመልከት ግራ-ቀኝ ብሎ መመልከት ተገቢ ላይሆን ይችላል ብለው ያምናሉ።

የፎቶው ባለመብት, Samuel Corum/Getty Images
ጽንፍ በያዘ ዴሞክራሲ ላይ የሚሠሩት እና የካርኔጊ ኢንዶውመንት ፎር ኢንተርናሽናል ፒስ ከፍተኛ ባልደረባ የሆኑት ራቼል ክላይንፌልድ "ሰዎች መገዛት የማይችሉበትን ምክንያት መመልከቱ የተሻለ ነው" ብለዋል።
"የሙቀት መጠኑን የመቀነስ ፍላጎትን ይጠይቃል…ለዚህ ደግሞ ሰዎች የበለጠ ድፍረት እንዲኖራቸው ይፈልጋል።"
"እንደማስበው ከሆነ እንደ ማኅበረሰብ ገጽ ገልብጠን አዲስ ምዕራፍ የምንከፍትበት መንገድ ላይ ማተኮር የበለጠ ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም ይህ እንደ መጥፎ ጋብቻ ነው። እንደ መጥፎ ጋብቻ ጣትን በመቀሰር መሸነፍ ብቻ ነው የሚችሉት።"
ምን ዓይነት እርቅ ይከናወን
አሜሪካ ክፍፍሎቹን የሚቀሰቅሱትን ስልተ ቀመሮችን ማፍረስ ትችል ይሆን? የሚለው ጥያቄን በተመለከተ፤ ለእርቅ ትልቅ ቁርጠኝነት ያለው ጠንካራ መሪ ያስፈልጋል።
የፖለቲካ ፀሐፊው ዴቪድ ድሬከር "ከዚህ እንዴት እንደምንወጣ እርግጠኛ አይደለሁም" ይላሉ። "ሁለቱም ወገኖች ወንጀሎቹን ለማስቆም 'በቃ' ቢሉ ይጠቅማል" ብለዋል።
"ብዙውን ጊዜ ፕሬዝዳንት ብቻ ነው ያንን ማመቻቸት የሚቻለው። ሁለቱም ወገኖች ማለፍ የማይገባቸው የተወሰኑ መስመሮች እንዳሉ ካልተስማሙ ወይም ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ይህን ካላደረጉ፣ እንዴት እዚህ ደረጃ እንደምንደርስ እርግጠኛ አይደለሁም።"

የፎቶው ባለመብት, SAUL LOEB/AFP via Getty Images
ትራምፕ እንደዚህ ዓይነት ፕሬዝዳንት አይደሉም።
ትራምፕ ግራ ዘመሞች የማጋ (አሜሪካን ዳግም ታላቅ እናደርጋለን የሚለውን) እንቅስቃሴያቸውን ለማጥፋት ይፈልጋሉ ብለው ያምናሉ። ከከርክ ግድያ በኋላም ከዩታው ገዢ የተለየ መንገድን መርጠዋል።
"ችግር ውስጥ የሚያስገባኝን አንድ ነገር እናገራለሁ። ነገር ግን ብዙም ግድ አይሰጠኝም። በቀኝ በኩል ያሉት አክራሪዎች ብዙውን ጊዜ አክራሪ የመሆናቸው ምክንያቱ ወንጀል ማየት ስለማይፈልጉ ነው…በግራ በኩል ያሉት ጽንፈኞች ችግር ናቸው" ብለዋል።
የከርክን ግድያ ተከትሎ ከኦቫል ኦፊስ በሰጡት አስተያየት "አክራሪ የግራ ዘመም ፖለቲካዊ አመጽ ብዙ ንፁሃንን ጎድቷል፣ ብዙ ሕይወት አጥፍቷል" ሲሉ ተናግረዋል።
የፕሬዝዳንቱ ሃሳብ በሌሎች የዋይት ሐውስ ባለሥልጣናት እየተስተጋቡ ነው።
የትራምፕ ቺፍ ኦፍ ስታፍ የሆኑት ስቴፈን ሚለር "ፈጣሪ ምስክሬ ነው፤ ያለንን ሃብት ሁሉ…እነዚህን ሰንሰለቶች ለመለየት፣ ለማደናቀፍ፣ ለመበታተን እና ለማጥፋት እንጠቀማለን" ብለዋል።
"ይሆናል። በቻርሊ ስም እናሳካዋለን።"
ከበርካታ አስርት ዓመታት በላይ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በፖለቲካ-ተኮር ግድያዎች እና ብጥብጦች ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ብዙ ግድያዎች የተፈጸሙት "ከግራ ክንፍ" ይልቅ "የቀኝ ክንፍ" ርዕዮተ ዓለም ባላቸው ሰዎች ነው። ይህንን ሙሉ ለሙሉ ለመደምደም ግን በብዙ መረጃዎች ያስፈልጋሉ።
ታሪክ ራሱን ይደግማል - ግን አይደለም
አንዳንድ ሰዎች በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ መጥፎ ጊዜያትን እንደ መጽናኛ ምንጭ አድርገው ይጠቁማሉ።
"አሜሪካ ውስጥ (በ1960ዎቹ እና በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ) ከነበረው ፖለቲካው ለውጥ ይልቅ እንደ ቬትናም ጦርነት እና የዋተርጌት ቅሌት ያሉት ክስተቶች ፖለቲካውን ቀርጸውታል" ሲሉ የቀድሞ የሪፐብሊካን ኮንግረስ አባል እና የቴሌቪዥን አዘጋጁ ጆ ስካርቦሮ ተናግረዋል።
"ነገር ግን አገሪቱ ወደ ፊት ተጓዘች። ሁለት መቶ ዓመቷን አከበረች። እናም ከአመጽ ክፍፍሏን አልፋለች። እንደገናም ታደርገዋለች።"

የፎቶው ባለመብት, CHARLY TRIBALLEAU/AFP via Getty Image
ተስፋ ከሚያታያቸው መካከል ከአገሪቱ ከፍተኛ ጥቁር ባለሥልጣናት አንዱ የሆኑት የጆርጂያው ዲሞክራት ሴናተር ራፋኤል ዋርኖክ ይገኙበታል።
የፖለቲካ ጥቃትን ከምንም በላይ "ፀረ-ዲሞክራሲያዊ" ሲል አውግዘው፣ አሜሪካ እንደ ዘር ባሉ ጉዳዮች ላይ ያደረገችውን ለውጦች ገልጸዋል።
"በቤተሰብ ስብሰባ ላይ ለራሳችን ከምንነግራቸው ታሪኮች በሚበልጥ ደረጃ የማንኛውም ቤተሰብ ታሪክ ሁልጊዜም የተወሳሰበ ነው" ብለዋል።
"አባቴ የወታደር ዩኒፎርሙን ለብሶ ለአንድ ታዳጊ ልጅ መቀመጫውን (አውቶቡስ ላይ) መልቀቅ የነበረበት ቢሆንም እኔ ግን አሁን በሴኔት ውስጥ ወንበር አለኝ።"
ተስፋቸው ልብ የሚያሞቅ ቢሆንም ግን አሁንም ግልጽ የሆነ መውጫ መንገድ አይታይም።
አሜሪካ የተመሠረተችበትን 250ኛ ዓመት ለማክበር በምትዘጋጀበት በአሁኑ ወቅት የታሪክ ምሁር እና ፊልም ሠሪ ከሆኑ ኬን በርንስ ጋር ቢቢሲ ቆይታ አድርጓል።
"ሰዎች ታሪክ እራሱን ይደግማል ይላሉ። በፍፁም አይደገምም" ብለዋል በርንስ።
ይልቁንም በርንስ ብዙዎች ፀሐፊው የማርክ ትዌይንን ሃሳብ በመዋስ የሚናገሩትን ጥቅስ ይመርጣሉ፡ "ታሪክ ራሱን አይደግምም፣ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ይመሳሰላል።"
በሌላ አነጋገር ምንም እንኳን አሁን ያለው ነገር ያለፈውን ቢመስልም ነገሮች ሁለት ጊዜ በተመሳሳይ መንገድ አይፈጸሙም።
በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ይህ የውጥረት ጊዜ ከሌሎች በርካታ ወቅቶች ጋር ቢመሳሰልም ግን ታሪክ ራሱን እየደገመ አይደለም።
አዎ የአሜሪካ ታሪክ በቁጣ እና በግጭት የተሞላ ነው። ነገ ግን የአገሪቱ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ሥርዓቶች እነዚያን ስሜቶች የሚያነቃቁ ኩባንያዎችን እና ሰዎችን ለመሸለም በጣም ፈጣን ነበሩ።
ዩናይትድ ስቴትስ ትዳክማለች እንጂ አትጠነክርም።
የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር ቦብ ጌትስ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት ከሆነ ሦስቱ ታላላቅ የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋቶች የሚሆኑት የእየጎለበተች ያለችው ቻይና፣ እያሽቆለቆለች ያለችው ሩሲያ እና የአሜሪካ የውስጥ ክፍፍሎች ናቸው።
የአሜሪካ ባላንጣዎች ክፍፍሏ ይህቺን ልዕለ ኃያል ምን ያህል እንደሚጎዳት በእርግጠኝነት ያውቃሉ። ሰዎችን የበለጠ ለመለያየት በበይነ መረብ ላይ ጠንክረው ይሠራሉ። አሜሪካውያን ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ ቀላል ያደርጉላቸዋል።















