ሳዲዮ ማኔ የአፍሪካ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሴኔጋላዊው ሳዲዮ ማኔ ዳግም የአፍሪካ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ በአፍሪካ እግር ኳስ ማህበር (ካፍ) ተመረጠ።
ማኔ በዘንድሮው አፍሪካ ዋንጫ ፍጻሜ ግብጽን አሸንፈው ዋንጫውን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያነሳ ከፍጹም ቅጣት ምት ጎል ማስቆጠሩ ይታወሳል።
በኮቪድ-19 ስርጭት ምክንያት ለሦስት ዓመታት የተስተጓጎለው ሽልማት በሞሮካ መዲና ራባት ተከናውኗል።
የናይጄሪያዋ አሲሳት ኦሾኦላ እአአ በ2019 ያነሳችውን ሽልማት በድጋሚ ተቀዳጅታለች።
ማኔ “ይህንን ሽልማት ስቀበል በጣም በጣም ተደስቻለሁ” ብሏል ።
ማኔ ለዚህ ክብር የበቃው የብሔራዊ ቡድን አጋሩን እና የቼልሲውን ግብ ጠባቂ ኤዱዋርድ ሜንዲን እና ቀድሞ በሊቨርፑል የቡድን አጋሩ የነበረውን ሞሐመድ ሳላህን በመብለጥ ነው።
“የሴኔጋል ዜጎችን አመሰግናለሁ። ይህን ሽልማት ለሃገሬ ወጣቶች ማስታወሻ ማድረግ እፈልጋለሁ” ብሏል።
ማኔ ብሔራዊ ቡድኑን ለዓለም ዋንጫ ከማድረስ ባለፈ ከቀድሞ ቡድኑ ሊቨርፑል ጋር ሁለት ዋንጫዎችን በማንሳት የውድድር ዓመቱን አጠናቋል።
በወንዶች ዘርፍ ከነበሩ ሰባት ሽልማቶች አምስቱን ሴኔጋላዊያን በማንሳት የበላይነታቸውን አስመስክረው አምሽተዋል።
የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አሊዩ ሲሴ የዓመቱ ኮከብ አሰልጣኝነትን ክብር ተጎናጽፈዋል። ቡድኑ ደግሞ የዓመቱ ምርጥ ወንዶች ቡድን ተብሏል። ፓፕ ሳር ደግሞ የዓመቱ ወጣት ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተሰይሟል። ሌላኛው ሴኔጋላዊ ፓፕ ኡስማን ሳኮ የታንዛኒያው ሲምባ ላይ ባስቆጠራት ጎል የዓመቱ ምርጥ ጎል አሸናፊ ለመሆን በቅቷል።
“ይህንን ዋንጫ ለማንሳት ረዥም ጊዜ ጠብቀናል” ያሉት የሴኔጋል እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አውገስቲን ሴንጎር ናቸው። “ዋንጫውን እስካሁን ላላነሱ ቡድኖች ጥሩ ምሳሌ እንሆናለን“ ሲሉም አክለዋል።
በውድድሩ አንድ ጨዋታ ላይ ብቻ የተሰለፈው ሳር ሽልማቱን ለማግኘት ከሬድቡል ሳልዘቡርጉ አይቮሪኮስታዊው ካሪም ኮናቴ እና ከቱኒዚያው የማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋች ሃኒባል መጅብሪ ጋር ተፎካክሯል።
በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ እንደ ዳንኤል አሞካቺ፣ ሉካስ ራዴቤ፣ ጄይ ጄይ ኦኮቻ፣ ዠርሚ ንጂታፕ፣ ኤል ሃጂ ዲዩፍ እና ካሊሉ ፋዲጋ ያሉ የቀድሞ ኮከቦች ተገኝተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በስፔን የሴቶች ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን የፒቺቺ ሽልማትን ያገኘችው አሲሳት ኦሾኦላ አምስት ሽልማቶችን በማግኘት የመጀመሪያዋ ሴት ተጫዋች ሆናለች።
ኦሾኦላ ሽልማቱን የተቀዳጀችው ከኢንተር ሚላኗ አጃራ ንቹት እና ከዛምቢያዊቷ ግሬስ ቻንዳ በመቅደም ነው።
“ይህ ምሽት ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ክብረ ወሰን የተሰበረበት ነው። ዛሬ አምስት ሽለማት አግኝቻለሁ። አምስት!” ብላለች።
“2021-22 የውድድር ዓመት ለእኔ በጣም ፈታኝ ነበር። ከጎኔ የቆሙትን በሙሉ ለማመስገን እወዳለሁ” ብላለች።
ደቡብ አፍሪካዊቷ ዲዛየር ኤሊስ ለሦስተኛ ተከታታይ ዓመት የዓመቱ የሴቶች ምርጥ አሰልጣኝ ሆነዋል።
ኤሊስ የሽልማቱን ማስታወሻነት ለሴት አሰልጣኞች አድርገዋል።
እሑድ የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታ በደቡብ አፍሪካ እና በአዘጋጇ ሞሮኮ መካከል ይከናወናል።
የአፍሪካ ምርጥ የሴቶች ቡድንም ከዚህ ጨዋታ በኋላ ይታወቃል።
የ2022 የካፍ ሽልማት አሸናፊዎች
- የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች (ወንዶች): ሳዲዮ ማኔ (ሴኔጋል እና ባየር ሙኒክ)
- የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች (ሴቶች)፡ አሲስት ኦሾኦላ (ናይጄሪያ እና ባርሴሎና)
- የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ (ወንዶች): አሊዩ ሲሴ (ሴኔጋል)
- የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ (ሴቶች)፡ ዲዛየር ኤሊስ (ደቡብ አፍሪካ)
- የዓመቱ ምርጥ ብሔራዊ ቡድን (ወንዶች): ሴኔጋል
- የዓመቱ ምርጥ ወጣት ተጫዋች (ሴቶች)፡ ኤቭሊን ባዱ (ጋና እና ሴኮንዲ ሃሳካስ ሌዲስ/አልቫልድስነስ)
- የዓመቱ ምርጥ ወጣት ተጫዋች (ወንዶች): ፓፕ ማታር ሳር (ሴኔጋል እና ቶተንሃም ሆትስፐር)
- የዓመቱ ምርጥ ክለብ (ሴቶች)፡ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ)
- የዓመቱ ምርጥ ክለብ (ወንዶች): ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ (ሞሮኮ)
- የኢንተር ክለብ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች (ሴቶች)፡ ኤቭሊን ባዱ (ጋና እና ሴኮንዲ ሃሳካስ ሌዲስ/አልቫልድስነስ)
- የኢንተር ክለብ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች (ወንዶች)፡ መሐመድ ኤል ሼናው (ግብጽ እና አል አህሊ)
- የዓመቱ ምርጥ ግብ፡ ፓፔ ኦስማን ሳኮ (ሴኔጋል እና ሲምባ)












