የሳዑዲ አረቢያው አል-ሂላል ቡድን ብራዚላዊውን ኔይማር ለመግዛት ከፒኤስጂ ጋር ተስማማ

ኔይማር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኔይማር
ታትሟል

የፈረንሳዩ ፓሪስ ሳን ዠርሜይን (ፒኤስጂ) ብራዚላዊውን ኔይማርን በ90 ሚሊዮን ዩሮ ለሳዑዲ አረቢያው አል-ሂላል የእግር ኳስ ቡድን ለመሸጥ ተስማማ።

የ31 ዓመቱ ኔይማር ዝውውር እውን የሚሆነው አስፈላጊውን የጤና ምርመራ አጠናቆ በሰነድ ሲቀርብ ነው ተብሏል።

ኔይማር ፒኤስጂን የተቀላቀለው ከስድስት ዓመታት በፊት የዓለም ክብረ ወሰን በተባለ ክፍያ በ222 ሚሊዮን ዩሮ ነበር።

ተጫዋቹ ከፈረንሳዩ ክለብ ጋር በነበረው ቆይታ በዓመት 26 ሚሊዮን ዩሮ ገቢን ያገኝ እንደነበር ተነግሯል።

ወደ ሳዑዲ አረቢያው ክለብ ሲዘዋወር ደግሞ ከዚህ ስድስት እጥፍ የሆነውን 150 ሚሊዮን ዩሮ ዓመታዊ ክፍያን ያገኛል ተብሏል።

ኔይማር በፒኤስጂ በነበረው ቆይታ በ173 ጨዋታዎች የተሰለፈ ሲሆን፣ ክለቡ አምስት የሊጉን ዋንጫ ጨምሮ 13 ዋንጫዎችን እንዲያነሳ አድርጓል። በተጨማሪም ከሦስት ዓመት በፊት ቡድኑ ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ እንዲደርስ ረድቷል።

ነገር ግን ኔይማር በፈረንሳዩ ክለብ ውስጥ የነበረው ቆይታ ተደጋጋሚ ጉዳቶች ደርሰውበት ከጨዋታ ውጪ ሆኖ የቆየባቸው ጊዜያት ነበሩ።

በተጨሪም ኔይማር በጉዳት ምክንያት ለአገሩ ብራዚል ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ እና በአህጉራዊው የኮፓ አሜሪካ ውድድር ላይ ሳይሳተፍ ቀርቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኔይማር ሽያጭ ስምምነት ይፋ የሆነው፣ የቡድኑ ባልደረባ ኪሊያን ምባፔ ከፒኤስጂ ጋር ለመቆየት ከስምምነት መድረሱ ከተነገረ በኋላ ነው።

የ24 ዓመቱ ምባፔ ከቡድኑ ጋር ባለው ኮንትራት ምክንያት ውዝግብ ውስጥ የነበረ ሲሆን፣ ወደ ሪያል ማድሪድም የመግባት ፍላጎት ነበረው።

ባለፈው ሐምሌ ወር ፒኤስጂ የሳዑዲው አል-ሂላል ክለብ ከምባፔ ጋር የዝውውር ንግግር እንዲያደርግ ፈቅዶ፣ ቡድኑ የዓለም ክብረ ወሰን የተባለውን 259 ሚሊዮን ፓወንድ ክፍያን አቅርቦ ነበር።

ሳዑዲ አረቢያ በዓለም ላይ ያሉ ኮከብ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን በከፍተኛ ክፍያ በማዘዋወር በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት የአገሯን የእግር ኳስ ሊግ በዓለም ከሚጠቀሱ ሊጎች መካከል አንዱ ለማድረግ እየጣረች ነው።

እንደሚታወቀው ካሪም ቤንዜማ፣ ንጎሎ ካንቴ፣ ጆርዳን ሄንደርሰን፣ ሩበን ኔቪስ፣ ሳዲዮ ማኔ እና ሮቤርቶ ፊርሚኖ ወደ ሳዑዲ ከተዘዋወሩ ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳሉ።

እንዲሁም ፖርቹጋላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከማንችስተር ዩናይትድ ወደ ሳዑዲው አል-ናስር የተዘዋወረው ባለፈው ጥር ወር ላይ ነበር።

የማንችስተር ሲቲው ሪያድ ማህሬዝ ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ወደ ሳዑዲው አል-ሂላል መዘዋወሩን ተከትሎ፣ የሲቲ አሠልጣኝ ፔፕ ጎዋርዲዮላ የሳዑዲ ሊግ ፈርጣማ የገንዘብ አቅም “ገበያው ላይ ተጽእኖ እያሳደረ ነው” ብሎ ነበር።

“ከወራት በፊት ክርስቲያኖ ሮናልዶ ወደ ሳዑዲ ሲያቀና፣ ይህን ያህል በርካታ ኮከብ ተጫዋቾች ወደ ሳዑዲ ሊግ በመሄድ ይጫወታሉ ብሎ ማንም አላሳበም ነበር” ብሏል የሲቲው አሠልጣኝ።

ይህ ሁኔታም ወደፊት የበለጠ እንደሚቀጥል እና ክለቦችም ምን እየተካሄደ እንደሆነ ማወቅ ይገባቸዋል ሲል ፔፕ ጎዋርዲዮላ አስጠንቅቋል።