ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማንቸስተር ሲቲ ከቶተንሃም፣ አርሴናል ከኤቨርትን. . . የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ግምት
ባለፈው ሳምንት ዌስት ሃም እና ኒውካስል በአወዛጋቢው በቪዲዮ በታገዘ ዳኝነት (ቫር) መጎዳታቸውን የቢቢሲው እግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱቶን ይገልጻል።
እንደሱቶን ከሆነ ዌስትሃም ከቼልሲ ጋር አቻ መለያየት ይችል ነበር። ከፓላስ ጋር በነበረው ጨዋታ ኒውካስልም ሦስት ነጥባ ማሳካት ይችል ነበር።
“ያለፈው ሳምንት ለእኔ ጥሩ አይደለም። ያለፈው ሳምንት ግምቴ በቫር ውሳኔ ሳይሳካ ቀርቷል” ብሏል።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ፣ እሑድ እና ሰኞ ይከናወናሉ።
ለዚህ ሳምንትም ሱቶን የሊጉን ጨዋታዎች ግምት አስቀምጧል።
ቅዳሜ
ፉልሃም ከ ቼልሲ
ቼልሲ በዚህ ውድድር ዓመት ወጥ አቋም ማሳየት አልቻለም። ከአሰልጣኝ ቶማስ ቱህል መሰናበት በኋላስ ቡድኑ ምን ዓይነት አቋም ያሳያል?
አዲሱ አሰልጣኝ ግርሃም ፖተር ቡድኑን ለማዘጋጀት በቂ ጊዜ ያላቸው አይመስልም።
ቼልሲ ከፉልሃም የተሻሉ ተጫዋቾችን ይዟል።
ቢሆንም ፉልሃም በሜዳው ማግኘት ከነበረበት ዘጠኝ ነጥብ ሰባቱን ማሳካት ችሏል።
ግምት፡ 1 – 1
በርንማውዝ ከብራይተን
የግራም ፖተርን መልቀቅ ተከትሎ ብራይተን ወዴት ያመራ ይሆን?
ብርንማውዝም አሰልጣኙ ስኮት ፓርከርን ካሳበተ በኋላ በጊዜያዊው አሰልጣኝ ጋሪ ኦኔል ይመራል። ኖቲንግሃም ፎረስትን ካሸነፉ በኋላ ሥራውን በቋሚነት ለመያዝ ማለሙ ጥፋት አይደለም።
ፓርከር አንዳንድ ተጫዋቾቹ ለሊጉ ይመጥናሉ ብሎ የሚያስብ አይመስለኝም። ኦኔል ግን በተቃራኒው የሚያስብ ይመስለኛል። ይህ ነው ልዩነቱም።
የፖተር መልቀቅም የተጫዋቾችን እምነት በመሸርሸር ለበርንማውዝ የሚጠቅም ይመስለኛል።
ከፖተር ውጭም በራይተን ይህን ጨዋታ በበላይነት የሚያጠናቅቅ ይመስለኛል።
ግምት፡ 1 – 2
ሌስተር ከ አስቶን ቪላ
ይህ ጨዋታ በመሰናበት አጣብቂኝ ውስጥ የሚገኙ ሁለት አሰልጣኞች የሚገናኙበት ነው።
በብራይተን ከተሸነፉ በኋላ ብሬንዳን ሮጀርስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ከቡድኑ ጋር መቀጠል የሚፈልጉ አይመሰልም።
ስቴቨን ዤራርድም ጫና ውስጥ ቢወድቅም ከማንቸስተር ሲቲ ጋር አቻ መውጣቱ ቡድን እየገነባ ለመሆኑ ምልክት ሊሆን ይችላል።
ሮጀርስ አሰልጣኝ ሆነው ዤራርድ ተጫዋች ሆነው በሊቨርፑል ይተዋወቃሉ። ሁለቱም አሰልጣኞች የተለያዩ ቡድኖችን ይዘውም በስኮትላንድ ሊግ ተገናኝተዋል።
ይህን ሁሉ ከግምት በማስገባት ቡድኖቹ ለመፋለም ብዙ ምክንያት እንዳላቸው አምናለሁ። ሆኖም ቪላ የሚያሽነፍ ይሰምለኛል።
ግምት፡ 1 – 2
ሊቨርፑል ከ ዎልቭስ
የሊቨርፑል ተከላካይ መስመር እንደቀድሞው አይደለም። ረቡዕ ምሽት በናፖሊ በተደጋጋሚ ሲፈተን አምሽቷል።
ከዚህ ቀደም ሊቨርፑል ከመጥፎ ውጤቱ እንደሚያገግም በተደጋጋሚ እገምት ነበር።
አሁን ግን በተቃራኒው እቆማለሁ።
ሊቨርፑል ጎል እንደሚያስቆጥር ባምንም ዎልቭስ ጫና ያሳድርባቸዋል።
ዎልቭሶች ችግራቸው ጎል ማስቆጠር ነው። ዲዬጎ ኮስታ ለዚህ መፍትሔ ስለመሆኑ ብጠራጠርም አንፊልድ ላይ የተወሰኑ ዕድሎችን እንደሚፈጥሩ አምናለሁ።
ግምት፡ 1 – 2
ሳውዝሃምፕተን ከ ብሬንትፎርድ
ይህንን ጨዋታ ለመገመት ከባድ ነው። ባለፈው ዓመት ሴንት ሜሪ ላይ ሳውዝሃምፕት 4-1 ሲያሸንፍ በመልሱ ጨዋታ ብሬንትፎርድ 3-0 አሸንፏል።
ጫና ያለው በአሰልጣኝ ራልፍ ሃሰንሃልት ላይ ቢሆን ጨዋታዎችን አሸንፈው በሊጉ እንደሚቆዩ አምናለሁ።
ብሬንትፎርድ ጎል የማስቆጠር ችግር እንደሌለበት በሊድስ ጨዋታ አሳይቷል።
አቻ ብዬ መገመት ባልወድም ከዚህ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች አንድ አንድ ነጥብ ያገኛሉ።
ግምት፡ 2 – 2
ማንቸስተር ሲቲ ከ ቶተንሃም
በሊጉ ምርጡ የመልሶ ማጥቃት ቡድን ቶተንሃም ነው። የሲቲ አጨዋወት ለቶተንሃም እንደሚመች ባለፈው የካቲት ኢትሃድ ላይ ተመልክተናል።
የቅዳሜው ጨዋታ ክፍት እንደሚሆን እጠበቃለሁ።
ሶን በዚህ ጨዋታ ጎል ያስቆጥራል ብዬ አስባለሁ። ሃላንድም ኳስና መረብን ያገናኛል።
ግምት፡ 3 – 3
እሑድ
አርሴናል ከ ኤቨርትን
አርሴናል ባለፈው ሳምንት በማንቸስተር ዩናይትድ ከደረሰበት ሽንፈት አንድ ነገር ማግኘት ነበረበት።
አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በአንድ ጊዜ ሦስት ተጫዋቾችን በቀየረበት አጋጣሚ ሲተች ተመልክቻለሁ። ለእኔ ግን ተገቢ ውሳኔ ነበር።
ይህ ጨዋታ ለአርሴናል ቀላል አይሆንም። ኤቨርተን በጥሩ መንፈስ ላይ ይገኛል። ይህ የላምፓርድ ቡድን ነጥብ እንዲያገኝ በቂው ነው?
ቡድኑ ጥሩ ኳስ ፈጣሪ ተጫዋቾች ያሉት ሲሆን ጋብርኤል ጄሱስን ካሰለፈ የእሑዱን ጨዋታ በድል ያጠናቅቃል።
ግምት፡ 2 - 1
ዌስት ሃም ከ ኒውካስል
ዌስት ሃም በቼልሲ ሜዳ ባጋጠመው ነገር አዝኛለሁ። ማክስዌል ኮርኔት ያስቆጠረው ኳስ መሻሩ ከመጥፎ ውሳኔዎች አንዱ ነው።
ኒውካስልም በተመሳሳይ መጥፎ ውሳኔ ተላልፎበታል።
ሁለቱም ቡድኖች ማስመስከር የሚፈልጉት ጉዳይ ስላለ ጥሩ ጨዋታ ይሆናል።
ኒውካስል ማጥቃትን የሚመርጥ ሲሆን ይህ አጨዋወት ለዌስት ሃም መልሶ ማጥቃት የተመቸ ነው።
ግምት፡ 2 – 1
ክሪስታል ፓላስ ከ ማንቸስተር ዩናይትድ
በሦስት ሳምንታት ውስጥ ማንቸስተር ዩናይትድ ለብዙዎች ከዓለማችን መጥፎው ቡድን ወደ ሃገሪቱ ድንቅ ቡድንነት ተቀይሯል።
እውነታውን ካየበደረጃ ሰንጠረዡ መሐል ላይ ነው የሚገኙት። ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ሲያሸንፉ ጥሩ ቢሆኑም በመሐል መሰናክል ያጋጥማቸዋል።
ባለፈው ዓመት ዩናይትድን በሜዳው ያሸነፈው ክሪስታል ፓላስ በዚህም ጨዋታ ጥሩ ውጤት የሚያመጡለት ድንቅ ተጫዋቾች አሉት።
የዩናይትድ ተከላካይ ክፍል ጫናን የሚቋቋምበት መንገድ የተመቸኝ ሲሆን በዚህ ጨዋታም የማሸነፍ ጉዟቸውን ይቀጥላሉ።
ግምት፡ 0 – 1
ሰኞ
ሊድስ ከ ኖቲንግሃም ፎረስት
በእነዚህ ሁለት ቡድኖች ምክንያት ከደጋፊዎች ከፍተኛ ትችት ገጥሞኛል። ይህ የሆነው ደግሞ ሁለቱም እንደሚወርዱ እና ፎረስት በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች እንደሚሸነፍ በመገመቴ ነበር።
በዚህ ጨዋታ ምን እንደሚፈጠር እንመልከት። በሜዳቸው እንደመጫወታቸው ሊድሶች የሚጠቀሙ ይሆናል። ፎረስት ያስመጣቸውን ተጫዋቾች እስኪያዋህድ ጊዜ ያስፈልገዋል።
ፎረስት ባለፈው ሳምንተ 2 ለ 0 ከመምራት በበርንማውዝ መሸነፉ ቡድኑን ይጎዳዋል።
ግምት፡ 3 – 1