ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት መሆኗን በይፋ አወጀች
ሰሜን ኮሪያ ራሷን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት መሆኗን ይፋ የሚያደረግ ሕግ ማወጇን የአገሪቱ መንግሥት ዜና ወኪል ኬሲኤንኤ ዘገበ።
የአገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ውሳኔውን "የማይቀለበስ" ሲሉ ገልጸውታል። ኒውክሌር ካለመታጠቅ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ድርድር ሊኖር እንደማይችልም ገልጸዋል።
በአዲሱ ሕግ መሠረት ሰሜን ኮሪያ ራሷን ለመከላከል በሚል ቀድሞ የኒውክሌር ጥቃት የመፈጸም መብት እንዳላት ይደነግጋል።
ፒዮንግያንግ በተደጋጋሚ ማዕቀብ ቢጣልባትም ከ2006 እስከ 2017 ባለው ጊዜ ስድስት የኒውክሌር ሙከራዎችን አድርጋለች።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎችን በመጣስ ወታደራዊ አቅሟን ማሳደጓን ቀጥላለች። የጦር አቅሟን በማሳደግ ከጎረቤቶቿ በተጨማሪ አሜሪካን ማጥቃት ሚያስችሉ መሣሪያዎችን ታጥቃለች።
ኪም እ.ኤ.አ. በ2019 ከወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ሁለት ዙር ንግግር ካደረጉ በኋላም የረዥም ርቀት የሚሳኤል እና የኒውክሌር ሙከራዎችን አድርገዋል።
በአሜሪካ እና በሰሜን ኮሪያ መካከል ሶካሄድ የነበረው ውይይት በኋላ ላይ ተቋርቷል።
የባይደን አስተዳደር ከፒዮንግያንግ ጋር ለመነጋገር ፍቃደኛ መሆኑን ተጠቁሟል። ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ከኪም ጋር በቀጥታ መገናኘት ስለመፈለጋቸውን ግን አልተነገረም።
ፒዮንግያንግን ለማግኘት እና በኮቪድ ወረርሽኙ ዙሪያ ድጋፍ ለማድረግ ያደረገው ሙከራ አለመሳካቱን ዋይት ሐውስ አስታውቋል።
አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ላይ ያላትን ፖሊሲዋን ባለፈው ዓመት ገምግማለች። የኮሪያ ልሳነ ምድር "ሙሉ በሙሉ ከኒውክሌር ነጻ መሆኑ" ዓላማው እንደሆነ በድጋሚ ተናግራለች።
ባይደን ከአገሪቱ ጋር የሚኖራቸው ግንኙት ዲፕሎማሲ እና "ጠንካራ መከላከልን" እንደሚያጣምር ተናግሯል። ኪም በበኩላቸው አገራቸው "ለውይይት እና ለግጭት" መዘጋጀት አለባት ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በዚህ ዓመት ፒዮንግያንግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የባለስቲክ ሚሳኤሎችን በማስወንጨፍ በኮሪያ ልሳነ ምድር ያለውን ውጥረት አባብሳለች።
ይህን ተከትሎ ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ ሚሳኤል በማስወንጨፍ እና በባሕረ ገብ መሬቱ አካባቢ ትልቅ የተባለውን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ በማድረግ ምላሽ ሰጥተዋል።