ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፕሪሚየር ሊግ ግምቶች፡ ሊቨርፑል ሲቲን አስቁሞ ለአርሰናል ውለታ ይውል ይሆን?
ፕሪሚየር ሊጉ ከዓለም አቀፍ ውድድሮች እረፍት በኋላ ሲመለስ ላለመውረድ የሚታገሉ ቡድኖችን ከማገናኘቱም በላይ ለሻምፒዮንነት በሚደረገው ፉክክር ላይ ጉልህ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።
የፕሪሚየር ሊጉ የመጨረሻዎቹን 10 ጨዋታዎች ወሳኝነትን ለመግለጽ ቀሪ ጨዋታዎች ‘10 የፍጻሜ ግጥሚያዎች’ ተብለው እየተገለጹ ነው።
የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱቶን የተጠባቂዎቹን ጨዋታዎች ግምት እንደሚከተለው አቅርቧል።
ማንቸስተር ሲቲ ከ ሊቨርፑል
ለሲቲ በዚህ ጨዋታ ነጥብ መጣል ማለት ዋንጫውን ለአርሰናል አሰልፎ እንደመስጠት ነው። ሱቶን ሲቲ ይህን ጨዋታ ማሸነፉ የግድ ነው ይላል።
ሊቨርፑልም ቢሆን ለሲቲ እጅ አይሰጥም። “ሲቲን ያስጨንቃሉ ብዬ እጠብቃለሁ ግን የሊቨርፑል የተከላካይ መስመር አቋም ስለሚዋዥቅ ሲቲ ይህን ጨዋታ ሊያሸንፍ ይችላል” ይላል ሱቶን።
ግምት፡ ሲቲ 3 - 1 ሊቨርፑል
አርሰናል ከ ሊድስ
ሱቶን ሊድስ ዩናይትድ ብዙ አስደናቂ ተሰጥዖ ያላቸው ተጫዋቾች እንዳሉት ይገልጻል። ከእረፍት በፊትም ዎልቭስን 4 - 2 ውጤት ማሸነፍ ችለው ነበር።
“ይህ ቢሆንም ግን ሊድሶች ለአርሰናል ችግር ይፈጥራሉ ብዬ አለሳብም” ይላል ሱቶን። መድፈኞቹ በሲቲ በሜዳቸው ሽንፈትን ካስተናገዱ ወዲህ ያደረጓቸውን ስድስት ጨዋታዎች በሙሉ ማሸነፋቸውን በማስታወስ ሊድስንም በኤሚሬትስ እንደሚረቱ ግምቱን አስቀምጧል።
ግምት፡ አርሰናል 2 - 0 ሊድስ
ቦርንመዝ ከ ፉልሃም
በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ቦርንመዞች ላለመውረድ በሚያደርጉት ትግል ወሳኝ ነጥቦችን በሜዳቸው በመሰብሰብ ላይ ይገኛሉ። “ፉልሃምን ማሸነፍ ቢያቅታቸው እንኳ በሜዳቸው ነጥብ ተጋርተው ይወጣሉ የሚል ግምት አለኝ።”
ያለ ሚትሮቪች እና ዊሊያን ወደ ሜዳ የሚገባው ፉልሃም፤ “በሁሉም ውድድሮች ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች መሸነፋቸውን ከግምት በማስገባት የቅዳሜ ከሰዓቱ ጨዋታ ይከብዳቸዋል የሚል ግምት አለኝ” ብሏል ሱቶን።
ግምት፡ በርንመዝ 1 - 1 ፉልሃም
ብራይተን ከ ብሬንትፎርድ
የእነዚህ ሁለት ክለቦች ግጥሚያ ማራኪ የሆነ ጨዋታ የሚታይበት ይሆናል።
ሁለቱም ክለቦች በሊጉ መልካም የሚባል ጊዜን እያሳለፉ ይገኛሉ። ውጤቱንም መገመት ከባድ ነው። “ሁለቱም ክለቦች ጎል ያስቆጥራሉ ድሉ ግን የብራይተን ይሆናል” ይላል ሱቶን።
ግምት፡ ብራይተን 2 - 1 ብሬንትፎርድ
ክርስታል ፓላስ ከ ሌስተር
ሮይ ሆድሰን ዳግም የፓላስ አሰልጣኝ ሆነው ወደ ሴለሀረስት ፓርክ ይመለሳሉ።
ሮይ ሆድሰን በመጀመሪያ ጨዋታቸው በተለይ ደግሞ በሜዳቸው ይሸነፋሉ ብዬ አልጠብቅም። ሌስተር በበኩሉ እንደ ጀምስ ማዲሰን እና ባርንስ ያሉ አስደናቂ ተጫዋቾች እያለው ጥሩ አቋም እያሳየ አይደለም።
ግምት፡ ፓላስ 1 - 1 ሌስተር
ኖቲንግሃም ፎረስ ከ ዎልቭስ
ውጤት ለመገመት ከሚከብዱ ጨዋታዎች መካከል አንዱ ይህ ነው። የዎልቭስ ሁኔታ ያሳስበኛል። የመውረድ ስጋት አለባቸው። ግን ከዎልቭስ በላይ ኖቲንግሃም ፎረስት ነው የበለጠ አደጋ ውስጥ ያለው።
ፎረስት በሜዳቸው ያለመሸነፍ ጠንካራ ክብረ ወሰን ቢኖራቸውም በዚህ ጨዋታ ምንም ነጥብ እንደማያገኙ እገምታለሁ።
ግምት፡ ፎረስት 0 - 1 ዎልቭስ
ቼልሲ ከ አስተን ቪላ
ቪላ ስቴፈን ጄራርድን አሰናብቶ ኡናይ ኤምሪን ከተካ በኋላ አስደናቂ ብቃት አሳይቷል። ኡናይ ኤምሪ ቪላን ከተረከቡ በኋላ ቡድኑ በተለይ የአጥቂ መስመሩ በየትኛውም ሰዓት አደጋ የመፍጠር አቅም አለው።
ይህ ቢሆንም “ሰማያዊዎቹ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻልን እያሳዩ ስለሆነ ድሉ የቼልሲ እንደሚሆን ግምቴ ነው።”
ግምት፡ ቼልሲ 2 - 1 ቪላ
እሁድ
ዌስት ሃም ከ ሳውዝሃምፕተን
ዌስት ሃም ወራጅ ቀጠና ውስጥ ነው ያለው። ተጋጣሚያቸው ደግሞ በ1 ነጥብ ዝቅ ብሎ የሚገኘው ሳውዝሃምፕተን ነው። ከሊጉ ላለመውረድ ከሚደረጉ ትንቅንቆች መካከል አንዱ ይህ ጨዋታ ነው።
ዌስት ሃም ላለመውረድ እንደዚህ አይነት ጨዋታዎችን ማሸነፉ የግድ ነው። ከቅጣት ምት በአስደናቂ ሁኔታ ግብ ማስቆጠር የሚችለውን ጄምስ ዋርድ-ፕራውስን የያዙት ሴንትስ እንዲሁ ጨዋታው ለእነርሱም እጅግ ወሳኝ ነው።
“ይህ ጨዋታ በጠባብ ውጤት አቻ የሚጠናቀቅ ይመስለኛል።”
ግምት፡ ዌስት ሃም 1 - 1 ሳውዝሃምፕተን
ኒውካስል ከ ማንቸስተር ዩናይትድ
ዩናይትድ በኤፍ ኤ ዋንጫ ፉልሃምን ማሸነፋቸው በጣም ዕድለኛ ያደርጋቸዋል። ዩናይትድ ከሰሞኑ ጥሩ የሚባል አቋም ላይ አይደለም ያሉት።
ዩናይትድ ወደ ኒውካስል አቅንቶ ቢያሸንፍ አይደንቀኝም ግን ጨዋታው ቀላል አይሆንለትም። “በሦስተኛ እና በአምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ክለቦች እስከ አራተኛ ድረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ በሚደረገው ሩጫ ከባድ ፉክክር ያደርጋሉ ብዬ ጠበቃለሁ።”
“የኒውካስሎች አጨዋወት ሁሌም ጎል ባያስገኝም በጣም ይማርከኛል። ወደ አቋም የተመለሰው አሌክሳንደር ኢሳክ ልዩነት ፈጣሪ ይሆናል ብዬ አምናለሁ።”
ግምት፡ ኒውካስል 2 – 1 ማንቸስተር ዩናይትድ
ኤቨርተን ከ ቶተነሃም
“የዚህን ጨዋታ ግምት ሦስት ጊዜ ነው የቀየርኩት። ለመገመት እጅግ በጣም ከባድ ነው።”
ቶተነሃም ወጥ የሆነ አቋም ስለሌለው ጨዋታውን መገመት አስቸጋሪ ነው። ምናልባት ቶተነሃም ከአንቶኒዮ ኮንቴ ውጪ የተሻለ ስለመሆኑ የምናይበት ጨዋታ ሊሆን ይችላል። “ግን የኮንቴ ምክትል የነበሩት ክርስቲያን ስቴሊኒ አዲስ ነገር ያመጣሉ ብዬ አልጠብቅም ይላል” ሱቶን።
ኤቨርተን ደግሞ በሾን ዳይሽ እየተመራ በሜዳው የተሻለ ነጥብ ሲያስመዘግብ ቆይቷል። “ባለፈው ጨዋታ ሳውዝሃምፕተን እንዴት በቶተነሃም ላይ የበላይነት እንደወሰደ ዳይሽ የተመለከቱ ይመስለኛል። ይህን ይደግሙታል ብዬ እጠብቃለሁ።”
ግምት፡ ኤቨርተን 2 - 1 ቶተነሃም