የ78 ዓመቷ አሜሪካዊት አዛውንት ባንክ በመዝረፍ ተከሰው ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, PLEASANT HILL MISSOURI POLICE DEPARTMENT
በአሜሪካዋ ሚዙሪ ግዛት ከዚህ ቀደም ባንክ በመዝረፍ ሁለት ጊዜ የተፈረደባቸው የ78 አመቷ ሴት ለሶስተኛ ጊዜ ባንክ በመዝረፍ መታሰራቸውን ፖሊስ ገልጿል።
ቦኒ ጉች የተባሉት አዛውንት ጎፔርት ወደተሰኘው ባንክ ገብተው ለገንዘብ ከፋዩ በሺዎች የሚቆጠር ዶላር እንዲሰጡት የሚጠይቅ ጽሁፍ ሰጥተዋል።
ገንዘቡን ይዘው በተሽከርካሪያቸው ከመሰወራቸው በፊት “አመሰግናለሁ፣ ማስፈራራት ፈልጌ አይደለም” የሚል ጽሁፍ ትተዋል።
አዛውንቷ ከ25 ሺህ ዶላር ማስያዢያ ጋር በእስር ላይ ይገኛሉ።
ጎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል፣ ጥቁር የጸሃይ መነጽርና የፕላስቲክ ጓንት በማጥለቅ ባለፈው ረቡዕ ነበር ወደ ባንኩ ያመሩት። ባንክ እንደገቡም ወደ ከፋዩ በማምራት “13 ሺህ ዶላር እፈልጋለሁ” የሚል ጽሁፍ የያዘ ወረቀት መስጠታቸውን የፍርድ ቤት ሰነዶችን ዋቢ አድርገው መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ወ/ሮ ጎች ጠረጴዛ እየደበደቡ ገንዘቡ በፍጥነት እንዲሰጣቸው ሲጠይቁም በደህንነት ካሜራ በተቀረጸ ቪዲዮ ላይ ታይተዋል።
ባንኩ ወደ ፖሊስ መደወሉን ተከትሎ አዛውንቷ ለይ በተደረገ ክትትል መኪናቸው ውስጥ ከጠንካራ የአልኮል ሽታና ወለሉ ላይ ከተበተነ ገንዘብ ጋር መያዛቸውን አቃቤ ህግ ገልጿል።
ጎች የታሰሩ ሲሆን የፋይናንስ ተቋምን በመዝረፍ ወይም ለመዝረፍ በመሞከር የሚል ክስተመስርቶባቸዋል።
“የፖሊስ መኮንኖች አዛውንቷን ለመያዝ ሲሞክሩ ተደናግረው ነበር. . . ዕድሜያቸው የገፋ አዛውንት ነበር የወጡት” ሲሉ የፖሊስ አዛዡ ቶሚ ራይት ተናግረዋል።
“መጀመሪያ ላይ የያዝነው ትክክለኛዋን ሰው ሰለመሆኑ እርግጠኛ አልሆንም ነበር” ሲሉም አክለዋል።
ሆኖም ይህ አይነት ክስ ለአዛውንቷ የመጀመሪያ አይደለም። ሁለት ጊዜ በተመሳሳይ ክስ ተፈርዶባቸው ነበር።
የመጀመሪያ እንደ አውሮፓውያኑ በ1977 በካሊፎርኒያ የፈጸሙት ዝርፊያ ሲሆን ሁለተኛው በ2020 ለገንዘብ ከፋዩ “ይህ ዘረፋ ነው” የሚል የልደት ካርድ እንደሰጡ ተነግሯል።
የ2020 ክሳቸው የተጠናቀቀው በጥቅምት 2021 ነበር።
የፖሊስ አዛዡ ተካሳሿ በምርመራ የተገኘ ህመም እንደሌለባቸው ገልጸው እድሜ ምክንያት የሚመጣና ያልተደረሰበት ለክስተቱ ምክንያት የሆነ የጤና ሁኔታ ለማጣራት እንሞክራለን ብለዋል።












