ሸሚማ ቤጉም አይኤስን ለመቀላቀል ሶሪያ የገባችው በካናዳ ሰላይ እርዳታ ነው ተባለ

ሸሚማ ቤጉም
የምስሉ መግለጫ, ሸሚማ ቤጉም የ15 ዓመት ወጣት ሳለች እአአ 2015 ላይ ከሌሎች ሁለት ሴቶች ጋር ከለንደን ተነስተው እስላሚክ ስቴትን ለመቀላቀል ወደ ሶሪያ ተጉዘዋል።
ታትሟል

የዩናይትድ ኪንግደም ዜግነት የነበራት ሸሚማ ቤጉም ከለንደን ወደ ሶሪያ በድብቅ የተሻገረችው በካናዳ መንግሥት ሰላይ ነው ተባለ።

ሸሚማ ቤጉም የ15 ዓመት ወጣት ሳለች እአአ 2015 ላይ ከሌሎች ሁለት ሴቶች ጋር ከለንደን ተነስተው እስላሚክ ስቴትን ለመቀላቀል ወደ ሶሪያ ተጉዘዋል።

ቢቢሲ በተመለከታቸው ሰነዶች ላይ ለካናዳ መንግሥት መረጃ የሚሰበስበው ሰላይ፤ የሸሚማ ቤጉም ፓስፖርት ዝርዝርን ለካናዳ መንግሥት ማጋራቱን እና ሌሎች የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸውን ወጣቶች ለአይኤስ እንዲዋጉ ወደ ሶሪያ ማሸጋገሩን ገልጿል።

የዩኬ መንግሥት የቤጉምን ዜግነትን ሰርዟል። የቤጉም ጠበቆች ግን ደንበኛችን የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠቂ በመሆኗ ዜግነቷ መሰረዝ የለበትም እያሉ ይከራከራሉ።

ከለንደን የተነሱት ሦስቱ ከ15-16 የእድሜ ክልል ውስጥ የነበሩት ሴቶች ቱርክ ኢስታንቡል ከደረሱ በኋላ መሐመድ አል ራሺድ የተባለ ግለሰብን አግኝተዋል። ግለሰቡ በአይኤስ ቁጥጥር ሥር ወደሚገኝ የሶሪያ ክፍል እንዲጓዙ ሁኔታዎችን አመቻችቷል።

አይኤስን የሚዋጋ የመንግሥታት ጥምረት የደኅንነት ባልደረባ የሆነ ግለሰብ ለቢቢሲ እንዳረጋገጠው ሦስቱን ሴቶች ወደ ሶሪያ እንዲዘዋወሩ የረዳው ግለሰብ በተመሳሳይ ወቅት ለካናዳ መንግሥት የደኅንነት መረጃዎችን ያቀብል ነበር።

ቢቢሲ መሐመድ አል ራሺድ በተመለከተ የደኅንነት መረጃዎችን እንዲሁም ከራሱ ራሺድ መረጃ ማከማቻ (ሃርድ ዲስክ) ባገኘው መረጃ መሠረት እንዴት ይሠራ እንደነበር ለማወቅ ችሏል።

ሦስቱን ሴቶች ወደ ሶሪያ ካሻገረ በቀናት ልዩነት በቁጥጥር ሥር የዋለው መሐመድ አል ራሺድ፤ ለቱርክ ፖሊስ የቤጉምን የፓስፖርት ዝርዝር መረጃ ጆርዳን ለሚገኘው የካናዳ ኤምባሲ መስጠቱን ተናግሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዩኬ ፖሊስ የጠፋችውን ወጣት ሴት በሚፈልግበት ወቅት የካናዳ መንግሥት ግን አድራሻዋን ያውቅ እንደነበረ ከራሺድ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።

ራሺድ ቤይጉምን ወደ ሶሪያ ከማሸጋገሩ በፊት በነበሩት ስምንት ወራት መቀመጫውን ቱርክ አድርጎ የእንግሊዝ ዜጎች የሆኑ ወጣቶችን ወደ አይኤስ ይዞታ እንዲሸጋገሩ ሲያመቻች ነበር ተብሏል።

ቤይጉም ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ በሰጠችው ቃል ላይ፤ ያለ ሰዎች አዘዋዋሪ ወደ ሶሪያ መሻገር የማይቻል ነበር ብላ ነበር።

“ብዙ ሰዎች እንዲገቡ ረድቷል . . . የሚነግረንን ሁሉ ስናደርግ ነበር። ምክንያቱም እርሱ ሁሉንም ነገር ያውቃል፤ እኛ ደግሞ ምንም አናውቅም” ብላ ነበር።

ራሺድ ምዕራባውያን ዜግነት ኖሯቸው ለአይኤስ የሚዋጉ፣ በአይኤስ ቁጥጥር ሥር በሚገኙ አካባቢ ያሉ ኢንተርኔት መጠቀሚያ ቤቶች አድራሻዎችን እና ከአይኤስ ተዋጊዎች ጋር የሚያደርጋቸውን ንግግር ሲመዘግብ ቆይቷል።

ራሺድ ሰዎችን ወደ ሶሪያ የሚያሸጋግረው ጆርዳን ለሚገኘው የካናዳ ኤምባሲ መረጃውን እያቀበለ እንደሆነ ተናግሯል።

ራሺድ እንደሚለው እአአ 2013 ጆርዳን ወዳለው የካናዳ ኤምባሲ አቅንቶ ጥገኝነት መጠየቁን ተናግሯል። “የአይኤስ እንቅስቃሴን በተመለከተ መረጃ ከሰበሰብክ የካናዳ ዜግነት እንሰጥሃለን ብለውኝ ነበር” ይላል።

ቢቢሲ ራሺድ ከእአአ 2013-2015 ባሉት ዓመታት ለበርካታ ጊዜ ወደ ጆርዳን መመላለሱን አረጋግጧል።

ሸሚማ ቤጉም እአአ በ2019 የዩኬ ዜግነቷን ተነጥቃ በሰሜን-ምስራቅ ሶሪያ በሚገኝ ማጎሪያ ጣቢያ ውስጥ በእስር ላይ ትገኛለች።

ጉዳዩን በተመለከተ የካናዳ እና የዩናይትድ ኪንግደም የደኅንነት መስሪያ ቤቶች የደኅንነት ጉዳዮችን በተመለከተ አስተያየት እንደማይሰጡ ተናግረዋል።