ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጋምቤላ ክልል ከባለፈው ዓመት ግንቦት ጀምሮ በነበሩ ግጭቶች 138 ሠዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋምቤላ ክልል ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተለያዩ ወረዳዎች በተነሱ ግጭቶች ስደተኞችን ጨምሮ 138 ሠዎች መገደላቸውን ገለጸ።
ኮሚሽኑ ከመስከረም 20 እስከ መስከረም 30/ 2016 ዓ.ም ድረስ አከናውኘዋለሁ ባለው ምርመራ ግጭቶቹ በኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ በጋምቤላና ጉግ ወረዳዎች እንዲሁም በክልሉ ዋና ከተማ ጋምቤላ ተከስተዋል ብሏል።
ለምርመራው 93 ሠዎችን ማነጋገሩን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ 113 ሠዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱንም አሳውቋል።
ግንቦት 2015 ዓ.ም ለእንጨት ለቀማ ወጥቶ በጠፋ ሠው ምክንያት በፒኝዋ እና ሌር ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭቱ ቀስ በቀስ ወደ ማሕበረሰባዊ ግጭት ተሸጋግሮ በኢታንግ ልዩ ወረዳ ቢያንስ 82 ሠዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ በመግለጫው አስፍሯል።
ግጭቱ እስከ ጥር 2016 ዓ/ም ድረስ ባሉት ጊዜያት እንደቀጠሉ የጥቃቶቹንን ቀንና ዝርዝር የጠቀሰው ኮሚሽኑ፤ በምርመራ ሪፖርቱ የዐይን እማኞችን ምስክርነት አካቷል።
“በኢታንግ ልዩ ወረዳ አኩራ ቀበሌ፣ ፒኖ ንኡስ ቀበሌ ሐምሌ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 5፡00 ሰዓት አካባቢ ቁጥራቸው በዛ ያለ የታጠቁ [ሰዎች] እንደ ብሬን ዐይነት ከባድ የጦር መሣሪያ ታጥቀው በመምጣት በርካታ ሰዎችን በጥይት ገድለው፣ በርካታ ሰዎችን አቆሰሉ። ወደ አምስት የሚሆኑ ሰዎች ከጥቃቱ ለማምለጥ ሲሞክሩ ባሮ ወንዝ ውስጥ ገብተው ቀሩ። ጥቃት ከተፈጸመባቸው ሰዎች መካከል ሕፃናት እና ሴቶች አሉበት።” ብሏል።
በክልሉ ስደተኞችም ጥቃት የተደረሰባቸው ሲሆን፤ በመጠለያ ጣቢያዎችና ከመጠለያ ጣቢያ ውጭ በታጣቂዎችና በግለሰቦች በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 27 ስደተኞች ተገድለዋል።
ጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን የመጡ ከ380 ሽህ በላይ ስደተኞችን ስድስት በሚሆኑ መጠለያ ጣቢያዎች ያስተናግዳል።
ኮሚሽኑ በጎግ ወረዳ፣ ፑኚዶ አንድ በተባለ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ “የቀድሞውን የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል መለዮ ልብስ የለበሱ የታጠቁ ቡድኖች እንጨት ለመልቀም የሄዱ ሰባት ሴት ስደተኞች ላይ ጥቃት ከከፈቱ በኋላ ስድስቱ ሲያመልጡ አንዷን ይዘው በጩቤ ወግተው መግደላቸውን የሟች ቤተሰብ እና ሌሎች ምስክሮች አስረድተዋል”ሲል አስፍሯል።
ኢሰመኮ በባለ 15 ገጽ የምርመራ ሪፖርቱ በክልሉ በተከሰቱ ግጭቶች ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን፣ በርካታ ቤቶችና ንብረቶች መቃጠላቸውን እና ዘረፋ መፈጸሙን ለማወቅ ችያለሁ ብሏል።
ለግጭቶቹ በመንግሥት የተሰጠውን ምላሽ የመረመረም ሲሆን በግጭቶቹ የመንግሥት አካላት እጅ እንደነበረበት ጠቁሟል።
ለአብነትም በኢታንግ ልዩ ወረዳ በግጭቱ እጃቸው አለበት የተባሉ ሦስት የመንግሥት አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በአኝዋ ብሄረሰብ ዞን ከጉዳዩ ጋር ተሳትፎ አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ አመራሮች ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውንና ምርመራ እተደረገባቸው እንደሆነ ዞኑ አሳውቆኛልም ብሏል።
ኮሚሽኑ በግጭቱ በቀጥታ በተሳተፉ “የአስተዳደር አካላት፣ የክልሉ መንግሥት የጸጥታ ኃይል አባላት፣ የታጠቁ ቡድኖች እና ግለሰቦች” ላይ ተገቢውን የወንጀል ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ ለመንግሥት ምክረ-ሀሳብ አቅርቧል።
ክልሉ የጸጥታ መዋቅሩን በመፈተሽ “ከወገንተኝነት የጸዳ” ብቁ የጸጥታ መዋቅር እንዲገነባም ጠይቋል።
በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሠዎች ተገቢውን ካሳ እንዲያገኙ ይደረግ ያለም ሲሆን፤ በስደተኞችና በማሕበረሰቡ መካከል ያሉ አለመግባባቶች በዘላቂነት የሚፈቱበት መንገድ እንዲፈጠር ጥረቶች ይደረጉ ሲል ምክሩን ለግሷል።