በአውስትራሊያ ያለ ምግብ እና ውሃ ስድስት ቀናትን ያሳለፉ አሳ አስጋሪዎች በሕይወት ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, AUSTRALIAN MARITIME SAFETY AUTHORITY
በአነስተኛዋ የአውስትራሊያ ደሴት ያለ ምግብ እና ውሃ ስድስት ቀናትን ያሳለፉ አስራ አንድ ኢንዶኖኔዣውያን አሳ አስጋሪዎች በሕይወት ተገኙ።
የአውስትራሊያ የባሕር ደኅንነት ባለስልጣን አሳ አስጋሪዎቹን ከምስራቃዊ አውስትራሊያ ቤድዌል ደሴት በአየር የነፍስ ማዳን ስራ መስራቱን አስታውቋል።
ይሁን እንጂ ሌሎች 9 አሳ አስጋሪዎች በሕይወት ላይኖሩ ይችላሉ የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
በሕይወት የተገኙት አሳ አስጋሪዎች በሁለት ጅላባ ሲጓዙ ኢልሳ በተሰኘው ከባድ አውሎ ንፋስ እንደተመቱና አንደኛዋ ጅላባ እንደሰጠመች ገልጸዋል።
በሰጠመው ጀልባ ውስጥ ከነበሩ 10 ሰዎች ዘጠኙ የገቡበት እስካሁን አልታወቀም።
የአውስትራሊያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዘገባ እንደሚያሳየው ከሆነ ከሰጠው ጀልባ በሕይወት የተረፈው ብቸኛው አሳ አስጋሪ ጄሪካን ላይ ለሰዓታት ውቅያኖስ ላይ ተንጠላጥሎ ከቆየ በኋላ በሌላኛ አሳ አስጋሪዎች ጀልባ ላይ ተሳፍሮ ሕይወቱን ታድጓል።
ከሁለቱ ጀልባዎች አንደኛው በወጀብ ተገፍቶ የባሕር ዳርቻ ላይተ ታይቷል።
ለስድት ቀናት ያለምግብ የቆዩት አሳ አስጋሪዎች በደንገት በአውስትራሊያ ጦር የደንብር ዘብ አውሮፕላን እይታ ውስጥ የገቡ ሲሆን በሂሊኮፕተር አሁን ሕክምና እያገኙ ወዳሉበት ሆስፒታል ተወስደዋል።
አሳ አስጋሪዎቹ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢያልፉም ሁሉም በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ኤቢሲ የደንብር ዘቡን ቃል አቀባይ ጠቅሶ ዘግቧል። መንግሥትም “በተቻለ ፍጥነት ወደ አገራቸው ለመሸኘት” እየተዘጋጀ እንደሆም ተገልጿል።
ኢልሳ የተሰኘው ከባድ አውሎ ንፋስ በምዕራባዊ አውስትራሊያ ከ14 ዓመት ገደማ በኃላ የተከሰተ ከባድ የአየር ሁኔታ ቢሆንም ሰዎች ወደ ሚበዛባቸው አከባቢዎች ባለመዘመቱ ከፍ ያለ ጉዳት አላደረሰም።












