ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተመልካች ስልክን እንደ ቪኤአር ተጠቅመው ጎል የሰረዙት ዳኛ ከሥራቸው ታገዱ
ግብፃዊው የመሃል ዳኛ ሞሐመድ ፋሩክ የተመልካች ስልክ እንደ ‘ቪኤኤር’ [ቪድዮ እገዛ] ተጠቅመው የገባ ጎል በመሻራቸው ከሥራቸው ታግደዋል።
ባለፈው ሳምንት በግብፅ ሁለተኛው ዲቪዚዮን አል-ናስር እና ስዊዝ ቡድን ጋር ሲጋጠሙ ነበር ዳኛው ይህንን ያረጉት።
አል-ናስር በተሟጠጠ ሰዓት የስዊዝ መረብ ላይ ጎል አስቆጥረው አቻ ቢሆኑም ዳኛው አንድ ጊዜ ፊሽካዬን ያዝሉኝ ብለው ወደ ተመልካች አቅንተዋል።
የግብፅ ሁለተኛው ዲቪዚዮን የጨዋታ እንቅስቃሴን መልሶ መመልከቻ የቪድዮ አጋዥ ዳኛ (ቪኤኤር) የለውም።
ነገር ግን በቴክኖሎጂ ዘመን ቪኤአር ለምን ያሉት ዳኛ ፋሩክ ወደ ተመልካች አቅንተው በተንቀሳቃሽ ስልክ የተቀረፀውን ምስል ካዩ በኋላ ኳስ በእጅ ተነክታለች ሲሉ ሰርዘዋል።
የግብፅ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባወጣው መግለጫ፤ በዕለቱ ጨዋታውን የዳኙ ሁሉ ለጊዜው ከሥራቸው ታግደዋል ብሏል።
ፖርቹጋላዊው የግብፅ ዳኞች ኮሚቲ ኃላፊ የሆኑት ቪቶር ፔሬራ ናች ይህን ውሳኔ ያስተላለፉት።
ከፔሬራ በፊት የቀድሞው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዳኛ የነበሩት ማርክ ክላተንበርግ የግብፅ የእግር ኳስ ዳኞች ኮሚቲ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።
የግብፅ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አክሎ ሞሐመድ ፋሩክ የዳኙትን ጨዋታ እየመረመረ መሆኑን ገልጿል።
ፌዴሬሽኑ፤ ዳኛው የተመልካች ስልክ ተጠቅመው ጎል መሰረዛቸውን ተከትሎ ጥብቅር እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ተዘግቧል።
ስዊዝ፤ ጎል ከተሰረዘ በኋላ ሦስተኛ ጎል በማከል ጨዋታውን 3 ለ 1 ሲረቱ የዕለቱ ዳኛ 15 ደቂቃ ጭማሪ ሰጥተዋል።
ፋሩክ፤ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ በፖሊስ ተከበው ነው ከስታድየም የወጡት።
የአል-ናስር ተጫዋቾች እና ባለሥልጣናት ዳኛው ሕግ ጥሰዋል በሚል ፍርድ ቤት እንገትራቸዋለን ብለዋል።