በዩኬ ከሶስት አስርት አመታት በፊት በደም ልገሳ ወቅት ኤችአይቪን ጨምሮ በሌሎች በሺታዎች የተጠቁ ተጎጂዎች ካሳ ሊከፈላቸው ነው

ታትሟል

በዩናይትድ ኪንግደም በአውሮፓውያኑ በ970ዎቹና በ80ዎቹ በ በደም ልገሳ ወቅት ካልተመረመሩ እና በሌሎች በሽታዎች ከተጠቁ ግለሰቦች ደም ያገኙ ህሙማን ኤችአይቪን ጨምሮ ለሌሎች በሽታዎች ተዳርገው ነበር።

በነዚህ የደም ልገሳዎች ተጎጂ የሆኑ ህሙማን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ 100 ሺህ ፓውንድ የካሳ ክፍያቸውን የሚያገኙ ቢሆንም የፍትህ ዘመቻው እንደሚቀጥል ተነግሯል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጥቅምት ወር መጨረሻ ገንዘባቸውን ይቀበላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ካሳውን የሚያገኙት በቀጥታ ደም የተለገሳቸው ወይም አጋሮቻቸው ብቻ ናቸው ተብሏል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ደም የተሰጣቸው ህሙማን ልጆችና ወላጆቻቸው ፍትህ እየጠየቁ ይገኛሉ።

እነዚህ ግለሰቦች ደም ከተለገሱ ቤተሰቦች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በሄፕታይተስ ሲ ወይም በኤች አይ ቪ የተጠቁ ናቸው።

በ1970ዎቹ እና 1980ዎቹ ውስጥ በነዚህ ህመሞች ተጠቅተዋል የባሉ ግለሰቦችን በተመለከተ ብሄራዊ ምርምራ እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

‘በሠፈራችን የኤድስ ቤተሰብ እንባል ነበር'

የጃኔት እና የኮሊን ስሚዝ የመጨረሻ ልጅ ከቀዶ ህክምና ወቅት በተሰጠው ደም ምክንያት በበሽታዎች ተጠቅቷል። 

የኒውፖርት ነዋሪ የሆነው ኮሊን በሄፕታይተስ ሲ እና በኤች አይ ቪ መያዙን ተከትሎ በሰባት ዓመቱ ህይወቱ አልፏል።

ቤተሰቦቹ በዚህ ምክንያት እንግልት እንደደረሰባቸው ይናገራሉ። 

በራቸው ላይ ምልክቶች፣ የስድብ የስልክ ጥሪዎችን እና በቤታቸው ላይ አጸያፊ ጽሁፎችም ይሰፍሩ ነበር ብለዋል።

"በሠፈራችን ኤድስ ያለበት ቤተሰብ እየተባልን እንታወቅ ነበር። በዚህም ተገለናል” ብለዋል ስሚዝ።

"ሌሎች ወንድ ልጆቻችን በትምህርት ቤት ጥቃት ይደርስባቸው ነበር። የኮሊን አባት ሥራ አጥቷል። መቼም ስራ እንደማያገኝም ተነግሮታል።” ይላሉ።

"ኮሊን በፍጹም መሞት አልነበረበትም። ደም ያለመርጋት ችግር ነበረበት። ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባ ነበር። ህክምናው ግን ገድሎታል። ይህ መሆን የለበትም” ብለዋል።

"እንዲህ ዓይነቱ ህመም በመንግስት ዕውቅና ሊሰጠው በተገባ ነበር።” ይላሉ።

"ኮሊን አሁንም የሕይወታችን ትልቅ አካል ነው። ሁላችንም ያለምክንያት መሞት እንዳልነበረበት እንዲታወቅ እንፈልጋለን” ሲሉ ገልጸዋል። 

ለአንዳንዶች በሚከፈለው ክፍያ ደስተኛ ቢሆኑም ሁሉም ክፍያ የማግኘት ዕድል ስለሌላቸው ደስታው “ትንሽ ቀንሷል” ብለዋል።

ጉዳዩ ገንዘቡ አይደለም "ልጆች በዚህ ደም ልገሳ ተበክለው ስለመሞታቸው ዕውቅና መስጠት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የቤቭ ቱሜልቲ ሁለት ወንድሞች ሃይድ እና ጋሬዝ በ1980ዎቹ በደም ልገሳ ወቅት በበሽታ ከተጠቁ ​​በኋላ በ2010 ህይወታቸውን አጥተዋል።

"ዘመቻውን ላካሄዱት ትልቅ ቀን ሲሆን ክፍያ ለሚያገኙ ሰዎች ደግሞ ብሩህ ነው" ብለዋል።

"የወንድሜ ሚስት ክፍያ የምታገኝ ሲሆን በገንዘብ እጦትም እየተሰቃየች ነበር”

ቱሜልቲ እንዳሉት ሁለቱም ወንድሞቿ በተደረገላቸው ህክምና ምክንያት በበሽታው ከተያዙ በኋላ ከስራቸው መልቀቅ ነበረባቸው።

“መሥራት አልቻሉም። የህይወት መድን ወይም ብድር ማግኘትም አልቻሉም። በቤተሰብ ደረጃ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል” ሲሉ ገልጸዋል። 

"ትልቅ ገንዘብ ይመስላል። የሚያስጨንቃቸውን ሸክም ያቃልላቸዋል። ነገር ግን ከ 30 እስከ 40 ዓመታት መልፋታችን ሲታሰብ ገንዘቡ ትልቅ አይደለም።”

የሁለቱም የቤቭ ወንድሞች በደም ልገሳው ወቅት ተበክለው ተጎጂ ለሆኑ ቤተሰቦች ፍትህ እንዲያገኙ ዘመቻ አድርገዋል።

"ይህ መልካም እርምጃ ነው። ምንም ነገር ግን ወንድሞቼን አይመልስም። ይህ መሆን አልነበረበትም" ብለዋል።

የሄሞፊሊያ ዌልስ ሊቀመንበር ሊን ኬሊ እንዳሉት ብዙዎች በህይወት ሆነው ባያዩትም ጊዜያዊ ክፍያዎቹ ለብዙዎች መጽናኛ ይሆናሉ ሲሉ አስረድተዋል።

"በርካታ አባላቶቻችን መጨረሻውን አያዩም። እነሱ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው። የተወሰነ ዕውቅና እንዲኖራቸው እንፈልጋለን" ሲሉ ኬሊ ተናግረዋል።

"ይህ ትክክለኛ እርምጃ ነው። መንግሥት ካሳ የሚለውን ቃል ሲጠቀም ለመጀመሪያ ጊዜው ነው። እውነታዎች ተሸፍነው እውነቱ ለህዝቡ ተነግሮ አያውቅም” ብለዋል።

"ተጎጂዎች ሁልጊዜ እውነቱን ያውቃሉ። እውነት ለሁሉም ሰው በጣም አስፈላጊ ነው።”

ገንዘቡ እና ዕውቅናው ጠቃሚ ነው ብለዋል።

“ከጥያቄዎቹ ምላሾች አንዱ ለተጎዱት ሰዎች ሁሉ ካሳ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉ አጠቃለዋል።