ኢራን ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎት የጠፋው ለምንድነው?

በኢራን ተቃውሞው በርትቷል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በኢራን ተቃውሞው በርትቷል
ታትሟል

በኢራን የሕዝብ አንቂዎችና የመብት ተሟጋቾች የበይነ መረብ ግንኙነቶች መቋረጣቸውን እየተናገሩ ነው።

ይህ የሆነው በሞራል ደንብ አስከባሪዎች ሒጃብ አል’ለበሽም ተብላ ድብደባ እንደደረሰባት የተነገረላት እና በእስር ላይ ሳለች የሞተችን ወጣት ሴት ተከትሎ በተቀሰቀሰ ሕዝባዊ ቁጣ ምክንያት ነው። 

በዓለም ዙሪያ ያለውን የኢንተርኔት አገልግሎትን የሚከታተለው ድርጅት ኔትብሎክስ እንደሚለው ኢንስታግራምና ዋትስአፕ አሁን በኢራን መሥራት አቁመዋል።

ዋትስአፕ እና ኢኒስታግራም በኢራን በስፋት አገልግሎት ይሰጡ ነበር።

ዋትስአፕ በበኩሉ በኢራን አገልግሎቱን ለማስቀጠል እየጣረ እንደሆነ ተናግሯል። 

ሜታ ኩባንያ በባለቤትነት የሚያስተዳድራቸው ዋትስአፕ እና ኢንስታግራም ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አሏቸው። 

በተለይ በኢራን ፌስቡክ እና ትዊተር ከተዘጉ በኋላ ሁለቱ መተግበሪያዎች ብዙ ተጠቃሚዎችን መሳብ ችለዋል።

ቴሌግራም፣ ዩቲዩብ እና ቲክቶክም አልፎ አልፎ መዘጋታቸው አልቀረም።

በሞራል ፖሊሶች ድብደባ እንደደረሰባት የተዘገበው የወጣቷ የማሻ አሚንን ሞት ተከትሎ በበርካታ የኢራን ከተሞች ቁጣ ተከስቷል።

በርካታ ሴቶች ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ሒጃባቸውን አውልቀው እስከማቃጠልም ደርሰዋል።

ይህን ተከትሎ ነው ብዙዎቹ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ዝግ የተደረጉት።

ኔትብሎክስ እንደሚለው ከሆነ ኢንተርኔት ሐሙስ ማታ በከፊል መሥራት ጀምሮ ነበር። ሆኖም ከዐርብ ጀምሮ ግን በአገር ደረጃ ተዘግቶ ቆይቷል።

የኢኒስታግራም ኃላፊ አዳም ሞሰሪ በትዊተር እንዳስታወቁት ኢራናውያን ከበይነ መረብ አገልግሎቶች ገለል ተደርገዋል። “ተስፋ እናደርጋለን ቶሎ ወደ ግንኙነት እንደሚመለሱ” ሲሉም አክለዋል።

ይሁንና አንዳንድ ኢራናውያን ከዚህ ግንኙነት መቋረጥ ጀርባ ሜታ ኩባንያ እጁ አለበት ወይም ተባባሪ እንደሆነ ይጠረጥራሉ።

ይህን የሚሉት ደግሞ የተቃውሞ ድምጽ የሚያሰሙ ይዘቶች ከማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹ ላይ ቶሎ እየተወገዱባቸው በመመልከታቸው ነው።

ሜታ ኩባንያ የፐርሺያ ቋንቋን የሚናገሩ የይዘት ገምጋሚዎች አሉት።

ደንብና ሁኔታዎችን የማያከብሩ ያሏቸውን ተጠቃሚዎችን ይዘቶች የማስወገድ ሚናም አላቸው።

ይሁንና በይዘታቸው ችግር የሌለባቸው ሐሳቦች ሲወገዱ እንደነበር ኢራናውያኑ ይናገራሉ።

ሌሎች ኢራናውያን ደግሞ ቪፒኤንን የመሰሉ በግርዶሽ የኢንተርኔት መግቢያ ስልቶች በኩል፣ በጓሮ በር ዋትስአፕ እና ሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያዎችን ለመጠቀም እንኳ ተቸግረናል ብለዋል።

ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ ሜታ ኩባንያ ተባባሪ ስለሆነ ነው ሲሉ ይከሳሉ።

የኢራን ባለሥልጣናት በአመጽ ጊዜ ኢንተርኔት ያጠፋሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኢራን ባለሥልጣናት በአመጽ ጊዜ ኢንተርኔት ያጠፋሉ

በኢራን በትክክል እየሆነ ያለው ምንድነው? 

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢንተርኔት መጥፋቱ ዋንኛው ምክንያት በኢራን ትልቁ የስልክ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ ከአገልግሎት ውጪ በመደረጉ ነው።

ሞባይል ኮሚኒኬሽን ካምፓኒ የሚባለው ይህ ድርጅት 60 ሚሊዮን ደንበኞች አሉት።

በሳምንቱ መጀመሪያ የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ የኢንተርኔት መቋረጡ የተከሰተው ከደኅንነት ሥጋት ጋር በተያያዘ እንደሆነ ተናግረው ነበር።

ነገር ግን የኢንተርኔት አገልግሎት ተቆጣጣሪ የሆነው ኔትበሎክስ ለቢቢሲ እንደተናገረው የኢራን ባለሥልጣናት ተቃውሞን ለማፈን ሲሉ የሚያደርጉት ነገር ነው።

“የኢራን ባለሥልጣናት ትልቁ እጃቸው ላይ ያለ አመጽ ማብረጃ ኢንተርኔትን ማጥፋት ነው” ትላለች የኔትብሎክስ ባልደረባ ለቢቢሲ።

ይህን ስታብራራም፣ በኢራን የግል ሚዲያ ባለመኖሩ ሰዎች ግንኙነታቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተንጠለጠለ ነው።

የአሚኒ ሞት በኢራን የግለሰብ ነጻነት፣ የመናገር ነጻነቶችን፣ የጾታ መብቶችን ሁሉ ዜጎች እንዲጠይቁ አድርጓቸዋል።

ብዙዎቹ በዚህ ተቃውሞ ተሳትፎ እያደረጉ ያሉት ደግሞ ሴቶች ናቸው። ሒጃባቸውን እስከማቃጠልም ደርሰዋል።

መንግሥት የግንኙነት መስመሮችን ከዘጋ በኋላ በተቃዋሚዎች ላይ መጠነ ሰፊ እስር ይፈጽም ይሆናል የሚል ፍርሃት አለ።

አንዲት ኢራናዊት እንደተናገረችው፣ “ኢንተርኔት ሲዘጋ ዓለም ስለኛ ማሰቡን ያቆማል። ብዙዎቹ ተቃውሞ ድምጾች መነሻና ማሳለጫዎች ማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ነበሩ። እነሱ ሲዘጉ ሁኔታዎች አስቸጋሪ ይሆናሉ።”

ሻያን ሳርዳዛዲህ የቢቢሲ የመረጃ ባለሙያ ናት።

“በኢራን ኢንተርኔት ልክ እንደ የኒውክሊየር ማስፈራሪያ ነው የሚታየው። ዜጎች ለመንግሥት የሚያሰጋ አመጽ ላይ እንደደረሱ ሲታሰብ ቶሎ ኢንተርኔቱ ይዘጋል” ትላለች። 

የበይነ መረብ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ መዘጋቱ በኢራን ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳትን ያደርሳል። 

ይሁንና ባለሥልጣናቱ አመጽ ከሚቀጥል የኢኮኖሚ ጉዳቱን ይመርጣሉ። 

አሁን የኢራን ባለሥልጣናት ስጋት አመጹ ተስፋፍቶ ልክ በፈረንጆቹ 2019 እንደሆነው ሰፊ አደጋና ጣጣ ይዞ እንዳይመጣ ነው። 

በዚያን ጊዜ በኢራን የቅርብ ታሪክ ከፍተኛ የተባለ ተቃውሞ ተነስቶ የነበረው የነዳጅ ዋጋ መጨመርን ተከትሎ ነበር። 

በዚያ አደገኛ በተባለ አመጽ ወቅትም የኢራን ባለሥልጣናት ተቃውሞውን ማብረድ የቻሉት ኢንተርኔትን በመዝጋት ነበር።

የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ “ተቃውሞ ማድረግ ይቻላል፤ ንብረት ማውደምን ግን አንታገስም” ብለዋል።

“ተቃውሞ ሁልጊዜም በኢራን አለ፤ ያ ሁልጊዜም የምንፈቅደው ነው፤ ድምጻቸውንም ለመስማት እንሞክራለን፤ ነገር ግን ተቃውሞና ሕገወጥ አመጽ መለየት አለበት” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ