‘በሕይወት ያለሁት በፈጣሪ ምክንያት ነው’ - ከግድያ ሙከራ ለጥቂት የተረፉት ምክትል ፕሬዝዳንት

ታትሟል

ሽጉጥ በመንከሱ ከግድያ ሙከራ የተረፉት የአርጀንቲና ምክትል ፕሬዝዳንት ክርስቲና ፈርናንዴዝ ደ ኩችነር “በሕይወት ያለሁት በፈጣሪ እና በድንግል ማርያም ምክንያት ነው” አሉ።

ከሁለት ሳምንታት በፊት በመዲናዋ ቦነስ አይረስ ከተሞከረባቸው የግድያ ሙከራ በኋላ አስተያየት የሰጡት ምክትል ፕሬዝዳንቷ ፖፕ ፍራንሲስ ደውለው እንዳጽናኗቸውም ገልጸዋል።

የ35 ዓመቱ ፈርናንዶ ሳባግ ሞንቴል እና የ23 ዓመቷ የፍቅር አጋሩ ብሬንዳ ዩሊያርቴ በግድያ ሙከራ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ሁለቱም የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።

ከቀሳውስት እና መነኩሳት ጋር ውይይት ያደረጉት ፈርናንዴዝ “ፈጣሪን እና ድንግል ማርያምን ለማመስገን በቀሳውስት መከበብ እንዳለብን ተሰምቶኛል” ሲሉ ተናግረዋል።

የግድያ ሙከራው ተከትሎ ለደወሉላቸው አርጀንቲናዊው ፖፕ ፍራንሲስም ምስጋናቸውን አቀርበዋል።

“ፖፕ ፍራንሲስ በቀጣዩ ቀን ደውለውልኝ ነበር። ‘የጥላቻ እና የጥቃት ድርጊቶች ሁሌም የጥላቻ እና የጥቃት ቃላትን ያስቀድማሉ’ ብለውኛል” ብለዋል።

ፈርናንዴዝ ቤታቸው ደጃፍ ላይ ደጋፊዎቻቸውን ለማናገር ከወጡ በኋላ ነበር የግድያ ሙከራው የተፈጸመባቸው።

በሙስና ወንጀል የተከሰሱትን ምክትል ፕሬዝዳንት ከጎንዎት ነን ለማለት ነው ደጋፊዎቻቸው የተሰባሰቡት። በዚህ ወቅት ነው አንድ ግለሰብ ፊታቸው ላይ ሽጉጥ የደቀነው። አጋጣሚው በካሜራ እይታ ሊገባ ችሏል።

ምላሸጩ ሲሳብ ሽጉጡ ባይተኩስም አምስት ጥይቶች ተሞልተ እንደነበር ፕሬዝዳንት አልቤርቶ ፈርናንዴዝ አሳውቀዋል። በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ ብለው “ክርስቲና በህይወት አለች። ምክንያቱ ባልተረጋገጠ ምክንያት ሽጉጡ ሊተኩስ አልቻለም” ብለው ነበር።

ክስተቱን እአአ በ1983 “ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከተመለሰ ወዲህ የተከሰተ ትልቅ አጋጣሚ” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ገልጸውታል።

ብራዚል ተወልዶ አርጀንቲና ያደገው ፈርናንዶ ሳባግ ሞንቴል ከደቂቃዎች በኋላ በቁጥጥር ስር ውሏል። የፍቅር ጓደኛው ከቀናት በኋላ በቁጥጥር ስር ውላለች።

መርማሪዎች ግድያ ሙከራውን ምክንያት ለማወቅ እየሠሩ ነው። ግራ ዘመሟ ምክትል ፕሬዝዳንት በደጋፊያቸው ሲወደሱ ብዙዎችን በማግለልም ይታወቃሉ።

በ2019 ምክትል ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት እአአ 2007 እስከ 2015 ፕሬዝዳንት ሆነው ሃገራቸውን አገልግለዋል።  ከ2003 እስከ 2007 ደግሞ ቀዳማይ እመቤት ነበሩ።