በትግራይ ቴሌቪዥን የኤርትራ ጦር ምርኮኞች ተብለው በቀረቡ ግለሰቦች ላይ ቤተሰቦቻቸው ጥያቄ አነሱ

የፎቶው ባለመብት, Tigray TV
በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸማቸው የተገለጸ የኤርትራ የጦር ምርኮኞች የተባሉ ግለሰቦች በትግራይ ቴሌቪዥን መቅረባቸውን ተከትሎ ዘመዶቻቸው ክሱን አጣጥለውታል።
በህወሓት የሚተዳደረው የትግራይ ቴሌቪዥን በምዕራብ ትግራይ አዋላ በተባለች ስፍራ አቅራቢያ ተያዙ የተባሉ አራት የኤርትራ ጦር ምርኮኞች ዘገባ ግንቦት 22/2014 ዓ.ም. ማሰራጨቱን ተከትሎ በማኅበራዊ ትስስር ገፆች መነጋገሪያ ሆኗል።
“በምዕራብ ትግራይ አዲ አዋላ አቅራቢያ በሚገኘው ገዛ ጊሌ የኤርትራ 57ኛ ክፍለ ጦር ሁለት ብርጌዶች እና የ21ኛ ክፍለ ጦር ሠራዊት አንድ ሻለቃ ክፍል በትግራይ ወታደሮች ላይ ግንቦት 16/2014 ዓ.ም ጥቃት ፈፅመዋል” ሲል የትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
የቴሌቪዥን ጣቢያው የኤርትራ ወታደሮች ናቸው የተባሉትን ሰመረ ገብረ ሕይወት፣ ገብሩ አልዓዛር፣ ኡመር ኡስማንና ይቤዮ ክፍላይ የተባሉ ግለሰቦችን አቅርቧል።
በዘገባው ላይ እነዚህም ግለሰቦቹ በኢትዮጵያውያን ላይ ግድያና መድፈር መፈጸማቸውን ሲናገሩም ይሰማሉ።
የሁለቱ ግለሰቦች ቤተሰቦች ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ግን ተያዙ የተባሉት ሰዎች የሰጡትን ምስክርነት ውድቅ አድርገውታል።
“ሰመረ አካል ጉዳተኛ ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ የአእምሮ እክል ነበረበት። ሁኔታው እያሽቆለቆለ ሄዶ በሚጥል በሽታም ታመመ። ያለ መድኃኒት ብዙ መስራት አይችልም” ሲል ታናሽ ወንድሙ ህሩይ ገብረ ሕይወት ለቢቢሲ ተናግሯል።
የሰመረ ሌላኛው ወንድም ክፍሎም ገብረ ሕይወት ሰመረ በጤናው ምክንያት በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ለመመዝገብ ብቁ እንዳልነበረ የሚያሳዩ ሰነዶችን ለቢቢሲ ዘጋቢ ልኳል።
ክፍሎም እንደሚናገረው ቤተሰቡ በኢትዮጵያ የትግራይ ድንበር አቅራቢያ በምትገኝ የሸሸቢት በተባለች የኤርትራ መንደር ነዋሪ ናቸው ይላል።
ቢቢሲ በኤርትራ ጋሽ ባርካ የሚገኘውን የብሔራዊ የአእምሮ ህሙማን ማኅበር ተወካይን አነጋግሮ ሰመረ ከጥር ወር ጀምሮ የድርጅቱ አባል እንደነበር አረጋግጧል።
“በበጋ ወቅት በመንደራችን ያለችው ትንሹ የሸሸቢት ግድብ ይደርቃል። በዚህም ማኅበረሰቡ ከብቶቹን ውሃ ለማጠጣት ወደ ዋናው ወንዝ መውረድ አለበት። መጋቢት 30/2014 ዓ.ም ሰመረ ገብረ ሕይወት፣ ገብሩ አልዓዛር፣ ኢሳያስ ምህረተአብ እና ሀብቶም የተባሉ የሸሸቢት ነዋሪዎች ከብቶቻቸውን ይዘው ወደ ሸሸቢት ወንዝ ወረዱ” ብሏል።
ስድስት የትግራይ የደኅንነት መኮንኖች ከግለሰቦቹ ጋር ፊት ለፊት በመጋፈጥ ሦስቱን እንደያዙ የሚያስረዳው ክፍሎም ከመካከላቸው አንዱ አምልጧል ብሏል።
በትግራይ ቴሌቪዥን በነበረው ዘገባ ሰመረ 41 ንፁሀን ዜጎችን መግደሉን እና ከ35 በላይ ሴቶችና ልጃገረዶችን እንደደፈረ ተናግሯል።
ክፍሎም ወንድሙ ፈጸምኩት ያለውን ውድቅ አድርጎታል።
“ሰመረ የሚናገረው፣ ይልቁንም መደጋገሙ የሚያሳየኝ እንደፈራ ነው። ባህርዩንና ጤንነቱን ስለማያውቅ” ሲል ክፍሎም ለቢቢሲ ተናግሯል።
በዚህ ዘገባ ላይ በተጨማሪ ገብሩ አልዓዛር የተባለ ግለሰብ ከ10 ያላነሱ የጦር ምርኮኞችን ተኩሶ መግደሉን መናገሩ ተዘግቧል።
በጀርመን የሚኖሩ የገብሩ የአጎት ልጅ ገብረማርያም ማርቆስ፣ ገብሩ የተወለደው በአውሮፓውያኑ 1993 ዓ.ም በሸሸቢት መሆኑን ገልጸው፣ ገብሩ በቤተሰባቸው ችግር ምክንያት ወደ ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት እንዳይገባ መደረጉን ያስረዳሉ።
“ገብሩ ወላጆቹን እና የተቀረውን ቤተሰብ ይንከባከብ ነበር። ወላጆቹንም የከብቶች እረኛ በመሆን ይረዳ ስለነበር በዚህ ኃላፊነት የተነሳ ወደ ብሔራዊ ውትድርና እንዳይቀላቀል ምክንያት ሆነ” ሲሉ ገብረማርያም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ሰመረ እና ገብሩ ከጠፉበት ቀን ጀምሮ የሰፈሩ ሰዎች ወላጆቻቸውን ሲያፅናኗቸው ነበር” ብለዋል።
የትግራይ ቴሌቪዥን በግንቦት 22 ዘገባው በአዲ አዋላ አካባቢ በነበረው ግጭት ሰመረ፣ ገብሩ፣ ኦመር ዑስማን እና ይቤዮ ከፍላይ መያዛቸውን ገልጿል።
ለግለሰቦቹ ቤተሰቦች ክስ ምላሽ እንዲሰጡን የትግራይ ቴሌቪዥን እና የትግራይ ኃይሎችን ብንጠይቅም ምንም አስተያየት አላገኘንም።












