ዩናይትድ ኪንግደም ለታዳጊ አገራት ምርቶች የቀረጥ ቅነሳ ልታደርግ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩናይትድ ኪንግደም የንግድ ግንኙነቷን ለማሳደግ ከታዳጊ አገራት ከምታስገባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ምርቶች ላይ ቀረጥ ልትቀንስ ነው።
ይህ ለታዳጊ አገራት የታሰበው የንግድ ዕቅድ በጥር ወር ተግባራዊ ይሆናል። ይህም ዩናይትድ ኪንግደም የአውሮፓ ኅብረት አባል በነበረችበት ጊዜ በነበረው ዕቅድ ላይ ይመሠረታል ተብሏል።
በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በስፋት የማይመረቱ እንደ ልብስ፣ ጫማ እና ምግቦች ያሉ ዕቃዎች ዝቅተኛ ወይም ዜሮ ታሪፍ ይጣልባቸዋል።
ዕቅዱ 65 ታዳጊ አገራትን ያጠቃልላል ተብሏል።
ዕቅዱ በማደግ ላይ ያሉ አገራት ያለ ታሪፍ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ከሚልኳቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ምርቶች በተጨማሪ ሲሆን፣ ከአፍሪካ ወደ አገሪቱ የሚገቡ 99 በመቶ ሸቀጦችን የሚመለከት ነው።
የዓለም አቀፍ ንግድ ቢሮ እንደገለጸው ዕቅዱ ንግድን “ዕድገት ለማስመዝገብ እና ድህነትን ለማጥፋት" እንዲሁም የእርዳታ ጥገኝነትን ለመቀነስ ዩናይትድ ኪንግደም የምታደርገው ጥረት አካል ነው።
ዕቅዱ አገራት በሰብዓዊ መብት፣ በጉልበት ብዝበዛ ወይም በአየር ንብረት ለውጥ ግዴታቸውን ባለመወጣታቸው ምክንያት የማገድ ሥልጣንን ያካትታል።
የዓለም አቀፍ ንግድ ኃላፊ የሆኑት አን-ማሪ ትሬቬሊያን እንዳሉት "የንግድ ፖሊሲያችንን እንደገና እየተቆጣጠርን የዩናይትድ ኪንግደም ንግዶችን የሚደግፉ ውሳኔዎችን ከመውሰድ ባለፈ በኑሮ ውድነት እና የታዳጊ አገራትን ኢኮኖሚ ይደግፋል።"
ከ65 ድሃ አገራት ከጨርቃ ጨርቅ እስከ ፍራፍሬ የሚደርሱ ምርቶች በዩናይትድ ኪንግደም ሲሸጡ፣ የአነስተኛ ወይም የዜሮ ታሪፍ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ይህም ይበልጥ ተፎካካሪ ያደርጋቸዋል።
አዲሱ ዕቅድ የተወሰኑትን ተጨማሪ ክፍያዎችም ይቀንሳል ተብሎም ይጠበቃል።
ለውጦቹ አስመጪዎችን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ፓውንድ እንዲያድኑ ያግዛሉ። ሆኖም ሙሉ በሙሉ ቢተገበር እንኳን ለተጠቃሚዎች የሚደርሰው የዋጋ ቅናሽ አነስተኛ ሊሆን ይችላል።
ለታዳጊ አገራት የሚሰጠው ዕርዳታን በመቀነሱ በምትኩ መንግሥት በንግድ የመደገፍ ፖሊሲ እንዳለው ያሳያል ተብሏል።
ከወቅቶች መለዋወጥ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ምርቶች ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ መመረት በማይችሉበት ወቅት በምርቶቹ ላይ የሚጣለው አነስተኛ ታሪፍም ይነሳል።
አንዳንድ ደንቦችም ቀላል ይሆናሉ፤ ለምሳሌ አንድ ምርት አብዛኛውን ግብዓቶቹን ከየት ነው የሚያገኘው በሚል የምርቱን መነሻ አገር የመወሰን ጉዳይም አንዱ ነው።
በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የተሰማራው የባንግላዲሹ የዲቢኤል ግሩፕ ሥራ አስኪያጅ መሐመድ ጃባር ዕቅዱ ለድርጅታቸው "ትልቅ ለውጥ" መሆኑን ጠቅሰዋል።
“በለውጦቹ ምክንያት ጥጥ ቀድም ሲል ከምናገኝባቸው አገራት በተጨማሪ ከሌሎችም በርካታ አገራት ማግኘት እንችላለን ማለት ነው። ይህም ንግዱን የበለጠ ተወዳዳሪ እና የአቅርቦት ሰንሰለቶቻችንን በጣም ጠንካራ ያደርገዋል” ብለዋል።












