ስኮትላንድ የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ በነጻ እንዲቀርብ በሕግ ወሰነች

የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች
ታትሟል

ስኮትላንድ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን በነጻ የማግኘት መብትን የሚያስከብር ሕግን አጸደቀች።

ወዲያው ተግባራዊ እንዲሆን የተደረገው ሕግ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን በነጻ የማግኘት መብትን ለመጠበቅ አዲስ ሕግ ያወጣች የዓለማችን የመጀመሪያዋ አገር በመሆን እንድትመዘገብ አድርጓታል።

በዚህ ሕግም ሕዝብ የሚገለገልባቸው ህንጻዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች እና ሌሎች ተቋማት የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን በነጻ ለማቅረብ ይገደዳሉ።

የየአካባቢው ባለሥልጣናት ማንኛውም ምርቶችን የሚፈልግ ሰው በነጻ እንዲያገኝ የማመቻቸት ግዴታ አለባቸው ተብሏል።

በሕዝብ መገልገያ ቦታዎች የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን በነጻ ለማቅረብ እንደ አውሮፓውያኑ ከ2017 ጀምሮ ወደ 27 ሚሊየን ዩሮ የሚጠጋ ገንዘብ ወጥቷል።

የሌበር ፓርቲ የስኮትላንድ ፓርላማ አባል የሆኑት ሞኒካ ሌኖን ሕጉ እንዲወጣ ዘመቻ ሲያካሂዱ ነበር። ይህም ከሁለት ዓመት በፊት በስኮትላንድ ፓርላማ በሙሉ ድምጽ ድጋፍ አግኝቷል።

የፓርላማ አባሏ የአካባቢ ባለሥልጣናት እና አጋር ድርጅቶች የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን በነጻ የማግኘት መብት ሕጋዊ መብት እንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ብለዋል።

የሕጉ መጽደቅ የወር አበባ ተፈጥሯዊ ክብር እንደሆነ ሲታገሉ ለነበሩ ተሟጋቾች እና ማኅበረሰባዊ እንቅስቃሴዎች ትልቅ ድል ሆኗል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በስኮትላንድ በተሰራ አንድ ኢመደበኛ ጥናት መሰረት ከ2000 በላይ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እና የኮሌጅ ተማሪዎች በቀረበላቸው ጥያቄ ከአራት ሴቶች መካከል አንዷ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ መግዛት አትችልም።

በዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኙ ሴቶች መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት የወር አበባ መገልገያዎችን መግዛት የማይችሉ ሲሆን 15 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በበቂ ሁኔታ መግዛት አይችሉም።

በተጨማሪም 19 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በዋጋው ውድነት ምክንያት ጥራት የሌላቸውን እና ለመጠቀም የማይመቹ መገልገያዎችን ለመግዛት ተገደዋል።

በጥናቱ መሰረት እድሜያቸው ከ14 እስከ 21 ከሆኑ ሴቶች መካከል 71 በመቶ የሚሆኑት የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያዎችን ከመድኃኒት ቤቶችና ሌሎች ቦታዎች ሄደው ለመግዛት ያፍራሉ።

የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን በቀላሉ ማግኘት አለመቻል በተለይ በማደግ ላይ ባሉ አጋራት እጅግ የከፋ ነው።

በኢትዮጵያም ለሴቶች መብት የሚሰሩ ማኅበራት፣ ተቋማትና ግለሰቦች የሴቶችን ጤናና ሁለገብ ተሳትፎ ለማበረታታት መንግሥት የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን ዋጋ በእጅጉ የሚቀንሱ እርምጃዎችን እንዲወስድ ለዓመታት ሲወተውቱ ቆይተዋል።

ይህንን ተከትሎም ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር በመሠረታዊ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ የቀረጥና የታክስ ማሻሻያ ማድረጉን መግለጹ ይታወሳል።

ሚኒስቴሩ በወቅቱ እንደገለጸው በዚህ ውሳኔ መሰረት የሴቶች ወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ (ሞዴስ) እንዲሁም የህፃናት ንጽህና መጠበቂያ (ዳይፐር) በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ለምርታቸው በሚያስፈልጉና ከውጭ በሚያስገቧቸው የጥሬ እቃ ግብዓቶች ላይ የነበረው ታክስ እንዲነሳ መወሰኑን አመልክቶ ነበር።