ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጣሊያን ከመረጃ ደኅንነት ጋር በተያያዘ አዲሱን የመረጃ መፈለጊያ ቻትጂፒቲን አገደች
ጣሊያን አዲሱን የመረጃ መፈለጊያ ቻትጂፒቲ (ChatGPT)ን በማገድ ከምዕራብ አገራት ቀዳሚዋ ሆነች።
የጣሊያን የመረጃ ጥበቃ ባለሥልጣን መተግበሪያውን ያገደው በአሜሪካ ጀማሪ ድርጅት ኦፕንኤአይ (OpenAI) የተሰራውና በግዙፉ ማይክሮሶፍት ደርጅት የተደገፈው አዲሱ ሞዴል የደኅንነት ሥጋቶች አሉት በሚል ነው።
የመረጃ ተቆጣጣሪው፣ ቻትጂፒቲ የተሰኘውን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) እና ኦፕንኤአይ ላይ ጊዜ ሳይሰጥ ምርመራ እንደሚያደርግ ገልጿል።
ቻትጂፒቲ አገልግሎት ላይ ከዋለበት የፈረንጆቹ ኅዳር 2022 አንስቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተጠቅመውበታል።
ከዚህ በፊት የጉግል የመረጃ ማሰሻን በማሻሻል የተሰራውና ክህሎት የሚጠይቀውን ጉዳይ በአጭር ጥያቄ መልስ ለማግኘት የሚያስችለው ቻትጂፒቲ፣ ተፈጥሯዊ፣ የሰው ልጆች ቋንቋን እንዲሁም የኢንተርኔትን የመረጃ ቋት በመጠቀም ሌሎች የአጻጻፍ ስልቶችን በማንበብ ጥያቄዎችን መመለስ ይችላል።
ማይክሮሶፍት በቻትጂፒቲ ላይ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን ያወጣ ሲሆን ባለፈው ወር መረጃን ወደ ተግባር ወደሚቀይረው ማይክሮሶፍት ቢንግ ውስጥ አካቶታል።
ከዚህም በተጨማሪ ዎርድ፣ ኤክስኤል፣ ፓዎርፖይንት እና አውትሉክን ጨምሮ በማይክሮሶፍት ኦፊስ መተግበሪያዎች የቴክኖሎጂ ስሪት ላይ እንደሚጨምረው ገልጿል።
አርተፊሻል ኢንተለጀንስ በሥራ እድል እንዲሁም የተሳሳተና አድሏዊ መረጃዎችን ማሰራጨትን ጨምሮ ስለሚኖረው አደጋ ስጋቶች አሉ።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ኤሎን መስክን ጨምሮ እውቅ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ይህንን ለማበልጸግ የሚደረገው ሩጫ ከቁጥጥር ውጭ ነው በሚል ስጋት ይህን መሰል የአርተፊሻል አስተውሎት ሥርዓት እንዲታገድ ጠይቀዋል።
የጣሊያን የመረጃ ተቆጣጠሪም የኦፕንኤአይን ቻትቦት ማገድ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የመረጃ ጥበቃ ደንቦች(GDPR) መጣረስ አለመጣረሱን ለማወቅ ምርመራ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ጂዲፒአር የግል መረጃዎቻችንን የምንጠቀምበትን፣ የምንሰራበትን እና የምናስቀምጥበትን መንገድ ይቆጣጠራል።
ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን እንደሚለው ከአስር ቀናት በፊት መተግበሪያው በተጠቃሚዎች የመረጃ ልውውጥ እና የክፍያ መረጃ ውስጥ ጣልቃ በመግባት የመረጃ ጥሰት አጋጥሞት ነበር።
“መተግበሪያው እንዲሰራ የሚያስችለውን የኮምፒዩተር ስልተ ቀመር (አልጎሪዝም) ለማሰልጠን ዓላማ የግል መረጃን በጅምላ መሰብሰብን እና ማከማቸትን በተመለከተ ለመጠየቅ የሚያስችል ሕጋዊ መሠረት የለም" ሲልም ባለሥልጣኑ ጨምሮ ስጋቱን ገልጿል።
ከዚህም ባሻገር የተጠቃሚዎቹን እድሜ ማረጋገጥ የሚችልበት መንገድ ስለሌለው መተግበሪያው ልጆችን እድገታቸውንና ግንዛቤያቸውን ለማይመጥን መረጃ ሊያጋልጣቸው ይችላልም ብሏል።
ተቀናቃኙ የጉግል አርተፊሻል አስተውሎት ቻትቦት የሆነው ቦርድ፣ አሁን ላይ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ባለው ተመሳሳይ ስጋት ምክንያት መጠቀም የሚችሉት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ተጠቃሚዎች ናቸው።
የጣሊያን የመረጃ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ኦፕንኤአይ ተቋሙ ላቀረበው ስጋት መልስ ለመስጠት ከ21.7 ሚሊዮን ዶላር ወይም አራት በመቶ ዓመታዊ ግብር ቅጣት ጋር 20 ቀናት ነበረው ብሏል።
በአውሮፓ ኅብረት ያሉ ግለሰቦች የግል መረጃቸው እንዲጠበቅ ያላቸውን መሠረታዊ መብት የማስከበር ኃላፊነት ያለው የአየርላንድ የመረጃ ተቆጣጠሪ ኮሚሽን በበኩሉ፣ የጣሊያን ተቆጣጣሪዎች እርምጃውን ለመውሰድ ያደረጋቸውን ምክንያት ለመረዳት እየተከታተለ መሆኑንና ከእገዳው ጋር በተያያዘም ያለውን ሁኔታ ለማጣራት በአውሮፓ ኅብረት ካሉ የመረጃ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት ጋር አብሮ እንደሚሰራ ለቢቢሲ ገልጿል።
በዩናይትድ ኪንግደም ገለልተኛ የሆነው የመረጃ ተቆጣጣሪው ኢንፎርሜሽን ኮሚሽነር ቢሮ ም የአርተፊሻል አስተውሎት እድገትን እንደሚደግፍ ገልጾ፣ የመረጃ ጥበቃ ሕጎች የማይከተሉትን ለመቃወም ዝግጁ መሆኑን ለቢቢሲ አስረድቷል።
በሴኩሪቲስኮርጋርድ የመረጃ መረብ ደኅንነት ባለሙያው ዳን ሞርጋን፣ እገዳው በአውሮፓ ለሚሰሩ ድርጅቶች የመረጃ ቁጥጥር ምን ያህል እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የተጠቃሚዎች መብት ተሟጋች ቡድን ቢኢዩሲ (BEUC)ም፣ በአሜሪካ የቀረበውን ቅሬታ ተከትሎ የመረጃ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናትን ጨምሮ የአውሮፓ ኅብረት እና ብሔራዊ ባለሥልጣናት ቻትጂፒቲን እና ተመሳሳይ ቻትቦቶችን እንዲመረምሩ ጠይቋል።
የአውሮፓ ኅብረት ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ በአርተፊሻል አስተውሎት የመጀመሪያውን ሕግ አውጥቶ እየሰራ ነው።
ይሁን እንጂ ተሟጋች ቡድኑ፣ በበቂ ሁኔታ ቁጥጥር ባልተደረገበት ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎችን ለአደጋ ማጋለጥን በተመለከተ የተቀመጠው የአርተፊሻል አስተውሎት ሕግ ተግባራዊ እስከሚሆን ዓመታትን ሊወስድ ይችላል የሚል ስጋት አለው።
የተሟጋች ድርጅቱ ምክትል ዳይሬክተር ኡርሱላ ፓቺል፣ የቴክኖሎጂ ማኅበረሰቡ አርተፊሻል አስተውሎት ከሚያስከትለው ጉዳት በበቂ ሁኔታ የተጠበቀ እንዳልሆነ አስጠንቅቀዋል።
ምክትል ዳይሬክተሯ "በቻትጂፒቲ እና ተመሳሳይ ቻትቦቶች ላይ ሰዎችን ሊያታልሉ ይችላሉ የሚሉ ተመሳሳይ ስጋቶች እየቀረቡ ነው። እነዚህ የአርተፊሻል አስተውሎት ሥርዓቶች ከፍተኛ የሆነ ቁጥጥር ያስፈልጋቸዋል” ብለዋል።
ቻትጂፒቲ ቻይና፣ ኢራን፣ ሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያን ጨምሮ በበርካታ አገራት ታግዷል።
ድርጅቱ ኦፕንኤአይ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥ ቢቢሲ ላቀረበለት ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።