በሱዳን ዋና ከተማ የሚገኝ ጦር ሠፈርን ለመቆጣጠር ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው

የሱዳን ጦር ሠራዊት አባላት ታንክ እና ተሽከርካሪዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በሱዳን የሚካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ከተጀመረ ከአራት ወራት በላይ ሆኖታል
ታትሟል

የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች በዋና ከተማዋ ካርቱም የሚገኝን ወሳኝ የጦር ሠፈር በቁጥጥራቸው ስር ለማስገባት ከባድ ውጊያ እያካሄዱ መሆናቸው ተነገረ።

ወራት ባስቆጠረው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊ የሆኑት የአገሪቱ ጦር ሠራዊት እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል የሚካሄደው ጦርነት በዋና ከተማዋ ውስጥ ተቀዛቅዞ የቆየ ቢሆንም አሁን ተባብሶ ቀጥሏል።

በጄኔራል አብዱል ፋታህ አልቡርሐን የሚመራው የሱዳን ጦር ሠራዊት ማክሰኞ ዕለት በፌስቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ ከተቀናቃኙ ኃይል ጋር ውጊያ መደረጉን አመልክቷል።

በደቡባዊ ካርቱም ውስጥ በሚገኘው አል-ሻጃራ በተባለው የብረት ለበስ ጓድ ጦር ሰፈር ላይ በጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመሩት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የሰነዘሩት ጥቃት ከሽፎ፣ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ጦር ሠራዊቱ ገልጿል።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በበኩል እንዳለው በተካሄደው ውጊያ የጦር ሰፈሩን የተወሰኑ ክፍሎች መቆጣጠሩን እና ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያ መማረኩን ማክሰኞ ምሽት በኤክስ (ትዊተር) ላይ ባሰራጨው መግለጫ አሳውቋል።

የጦር ሰፈሩን ለመቆጣጠር ለሦስት ቀናት ከባድ ውጊያ መካሄዱን በሳዑዲ የሚደገፈው አል አረቢያ ቴሌቪዥን የሱዳን ጦር ሠራዊት አሁንም ወታደራዊ ሠፈሩን እንደተቆጣጠረው እንደሚገኝ ዘግቧል።

በሁለቱ ጄኔራሎች መካከል ሲካሄድ በቆየው የሥልጣን ፉክክር ምክንያት ባለፈው ሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ በተቀሰቀሰው ጦርነት ሱዳን ከባድ ቀውስ የገጠማት ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ያጠፋው ጦርነት ከአራት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ከቤታቸው አፈናልቀሎ በርካቶች ለስደት መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።

ባለፉት ሳምንታት ተቀዛቅዞ የነበረው የሁለቱ ኃይሎች ጦርነት ከቅርብ ቀናት ወዲህ በዋና ከተማዋ ካርቱም፣ በቅርብ በሚገኙት ኦምዱርማን እና ባሕሪ እንዲሁም የሱዳን ምዕራባዊ ግዛት በሆነችው ዳርፉር ውስጥ ውጊያው ተጠናክሮ እየተካሄደ ነው።

የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት እና ቀጠናዊው ድርጅት ኢጋድ ተፋላሚ ወገኖችን በማቀራረብ ሰላም እንዲወርድ ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል ሱዳንን በፈላጭ ቆራጭነት የመሩት ኦማር ሐሰን አልበሽር በሕዝባዊ ተቃውሞ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ፣ ምርጫ ተደርጎ መደበኛ መንግሥት እስኪመሠረት ድረስ የሽግግር አስተዳደር ተመስርቶ እንደነበር ይታወሳል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ እና በሱዳን ጦር ሠራዊት ሲመራ የቆየው ጊዜያዊ አስተዳደር ላይ የጦር ኃይሉ መሪ ጄኔራል አል ቡርሐን መፈንቅለ መንግሥት አካሂደው ሥልጣኑን ከቆጣጠሩ በኋላ፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይ መሪ ከሆኑት ጄኔራል ሐምዶክ ጋር ጥርጣሬ እና የሥልጣ ፉክክር ውስጥ ገብተው ቆይተዋል።

ይህ የጄኔራሎቹ ፍጥጫ ሚያዝያ 07/2015 ዓ.ም. የሱዳንን የመሪነት ሥልጣን ለመቆጣጠር ወደ ግልጽ የእርስ በርስ ጦርነት አምቶ ሱዳን በከባድ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች።