የናዚ ኮማንደር ፀሐፊ በ10 ሺህ 505 ግድያዎች ተባባሪ በመሆን ጥፋተኛ ተባሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በናዚ ማሰቃያ እና ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ኮማንደር ለነበረው ግለሰብ ፀሐፊ የነበሩ ሴት ከ10 ሺህ 505 በላይ ለሆኑ ሰዎች ግድያ ተባባሪ በመሆን ጥፋተኛ ተባሉ።
በአሁኑ ወቅት የ97 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት ኢርምግራድ ፉርችነር ከአውሮፓውያኑ 1943 -1945 ባለው ጊዜ በስቱትሆፍ ማጎሪያ ውስጥ በፀሐፊነት አገልግለዋል።
ለበርካታ አስርት ዓመታት በናዚ የጅምላ ግድያ እና ጭፍጨፋዎች ክስ ከተመሰረተባቸው ጥቂት ሴቶች አንዷ የሆኑት ፉርችነር የሁለት ዓመት የገደብ የእስር ቅጣት ተፈርዶባቸዋል።
ምንም እንኳን ግለሰቧ የሰቪል ሠራተኛ ቢሆኑም ዳኛው በካምፑ ውስጥ ያለውን ነገር ሙሉ በሙሉ ያውቁ እንደነበር ገልጸዋል።
በአብዛኛው ይሁዳዊ እስረኞች በነበሩበት ስቱትፍ የሶቪየት ወታደሮች እና ሌሎች ግለሰቦችን ጨምሮ 65 ሺህ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታዎች ተገድለዋል ተብሎ ይታመናል።
በአሁኗ የፖላንድ ከተማ ግዳንስክ አቅራቢያ በምትገኘው ስቱትፍ የነበሩ እስረኞችን ለመግደል የተለያዩ ዘዴዎችን የተጠቀሙ ሲሆን ከአውሮፓውያኑ 1944 ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመርዛማ ጋዝ ታፍነው እንዲሞቱ ተደርጓል።
በሰሜናዊ ጀርመን የሚገኘው የኢትዘንሆይ ፍርድ ቤት ከካምፑ የተረፉ ሰዎች የሰጡትን ምስክርነት የሰማ ሲሆን፣ የተወሰኑትም በችሎቱ ወቅት ሕይወታቸው አልፏል።
መስከረም ወር ላይ ችሎቱ በተጀመረበት ወቅት ኢርምጋርድ ፉርችነር ከነበሩበት የጡረታ ማዕከል ሸሽተው የነበረ ሲሆን፣ በመጨረሻም በሃምቡርግ ጎዳና ላይ በፖሊስ ተይዘዋል።
የስቱትሆፍ ተቆጣጣሪ የነበሩት ፓውል ዌርነት በአውሮፓውያኑ 1955 በግድያዎቹ ተባባሪ በመሆን ታስረው የነበረ ቢሆንም ከአምስት ዓመት እስር በኋላ ተፈትተዋል።
ከአውሮፓውያኑ 2011 ጀምሮ በጀርመን በተከታታይ ክሶች የተመሰረተ ሲሆን፣ በተለይም የናዚ የሞት ካምፕ ጠባቂ የነበረው ጆን ዴምጃንጁክ ጥፋተኛ መባሉ በርካታ ነገሮችን ቀይሯል።
ይህም ብይን የሲቪል ሠራተኛዋ ኢርምግራድ ለፍርድ መቅረብ እንደምትችል የወሰነ ነበር። ግለሰቧ በቀጥታ ለካምፑ አዛዥ በምትሰራበት ወቅት በስቱትሆፍ እስረኞች ዙሪያ የተደረጉ ጉዳዮችን ያውቁ ነበር ተብሏል።
ችሎቱ ከተጀመረ ከ40 ቀናት በኋላ ዝምታቸውን የሰበሩት ግለሰቧ ለፍርድ ቤቱ “ስለሆነው ነገር ሁሉ አዝናለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
የጅምላ ግድያዎችና ጭፍጨፋ በተፈጸሙበት ወቅት የቀድሞዋ ፀሐፊ እድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች ስለነበር ችሎቱ የተካሄደው በልዩ የወጣቶች ፍርድ ቤት ነበር።
“በወቅቱ ስቱትሆፍ ውስጥ በመኖሬ ተፀፅቻለሁ። ማለት የምችለው ይህን ብቻ ነው” ብለዋል።
ተካላካይ ጠበቆቿ በሆፕ ቢሮ ውስጥ ካሉት በርካታ ፀሐፊዎች መካከል አንዷ እንደነበሩና የሚያውቁትም ነገርን በተመለከተ አጠራጣሪ እንደሆነ በመግለፅ በነፃ እንዲለቀቁ ተከራክረዋል።
ይሁን እንጂ የታሪክ ምሁሩ ስቴፋን ሆርድለር በካምፑ ቦታ ላይ ሁለት ዳኞችን በማጀብ ያስጎበኙ ሲሆን፣ በችሎቱ ላይም የሰጡትም ምስክርነት ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።
ከጉብኝቱ መረዳት እንደተቻለው ፉርቸነር በካምፑ ውስጥ እየተፈጸሙ የነበሩ አሰቃቂ ሁኔታዎችን ከኮማንደሩ ቢሮ ለማየት ይችሉ እንደነበር ነው።
የታሪክ ምሁሩ በችሎቱ ላይ እንደተናገሩት ናዚዎች ካምፑን ለማስፋፋት እና የጅምላ ግድያዎችን በዛይክሎን ቢ ጋዝ ለማፋጠን በሚል በ27 መኪኖች የተጫኑ 48 ሺህ ሰዎች ከጥቅምት 1944 ወደ ስቱትሆፍ ደርሰዋል ብለዋል።












