የቀድሞው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ አቡነ ቤኔዲክት አረፉ

ታትሟል

ለረጅም ጊዜ በህመም ላይ የቆዩት የቀድሞው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ አቡነ ቤኔዲክት 16ኛ በ95 ዓመታቸው ቫቲካን ውስጥ በሚገኘው መኖሪያቸው ማረፋቸው ተገለጸ።

የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዋነኛ መቀመጫ ከሆነችው ቫቲካን በተሰጠው መግለጫ ነው የቀድሞው ጳጳስ ህልፈት ይፋ የሆነው።

“አቡነ ቤኔዲክት 16ኛ በቫቲካን አቅሌሲያ ገዳም ውስጥ ሳሉ ማረፋቸውን በታላቅ ሐዘን እናሳውቃለን” በማለት ተጨማሪ መረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚሰጥ ቤተ ክርስቲያኗ ገልጻለ።

አቡነ ቤኔዲክት በጤና እክል ምክንያት ከጵጵስና መንበራቸው ከለቀቁ አስር ዓመት ሊሆናቸው በተቃረበበት ጊዜ ነው ማረፋቸው የተነገረው።

ጳጳሱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን እስከ 2023 (እአአ) ድረስ ለስምንት ዓመታት የመሩ ሲሆን፣ በቤተክርስቲያኗ ታሪክ በ1415 በፈቃዳቸው መንበራቸውን ከለቀቁት ከጆርጅ 12ኛ ወዲህ አቡነ ቤኔዲክት ጵጵስናቸውን ሲለቁ ከረጅም ዘመናት በኋላ የጀመሪያው ናቸው።

አቡነ ቤኔዲክት ከመንበራቸው ከለቀቁ በኋላ እዚያው ቫቲካን ውስጥ በሚገኝ ገዳም የመጨረሻዎቹን ዓመታት አሳልፈዋል።

የተኳቸው የቤተክርስቲያኗ ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስም በተደጋጋሚ ይጎበኟቸው እንደነበር ተነግሯል።

የቀድሞው ጳጳስ ለረጅም ጊዜ በህመም ላይ የቆዩ ቢሆንም፣ በእድሜ መግፋት ምክንያት የጤና ሁኔታቸው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ በዚህ ሳምንት ተገልጾ ነበር።

ባለፈው ረቡዕ አቡነ ፍራንሲስ የዓመቱ መጨረሻ ንግግራቸውን ቫቲካን ውስጥ ባደረጉበት ጊዜ፣ አቡነ ቤኔዲክት በጠና መታመማቸውን በመግለጽ ምዕመኑ “የተለየ ጸሎት” እንዲያደርግላቸው ጥሪ አቅርበው ነበር።

ጀርመን ውስጥ የተወለዱት አቡነ ቤኔዲክት የመጀመሪያ ስማቸው ጆሴፍ ራትዚንገር የነበረ ሲሆን፣ በ2005 (እአአ) በ78 ዓመታቸው የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪ ሆነዋል። በዚህም ወደ ጳጳስነት መንበር ሲመጡ በእድሜ የገፉ አባት ሆነዋል።

በጵጵስና ዘመናቸው ካቶሊካዊቷ ቤተክርስቲያን ክሶች፣ የሕጋዊ ጥያቄዎች እና ለዘመናት በቀሳውስት በሕጻናት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን የሚያጋልጡ ሪፖርቶች ይፋ ተደርገዋል።

በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት መጀመሪያ ላይ የቀድሞው ጳጳስ አቡነ ቤኔዲክት የሚዩኒክ ጳጳስ ሳሉ በ1977 እና 1982 መካከል በነበሩት ዓመታት የተፈጸሙ ጥቃቶች አያያዝ ላይ ስህተት እንደነበረ አምነዋል።