የፌደራል ፍርድ ቤቶች አመራሮች የምርጫ ቦርድ አባል እንዲሆኑ በዕጩነት ቀረቡ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተክሊት ይመስል እና የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተስፋዬ ንዋይን ጨምሮ ስድስት ሰዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ እና የሥራ አመራር ቦርድ አባል እንዲሆኑ በዕጩነት ቀረቡ።

ዕጩዎቹ የተመረጡት "የብሔር፣ የሃይማኖት እና የፆታ" ስብጥርን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት ዕጩ መልማይ ኮሚቴ አስታውቋል።

ዕጩ መልማይ ኮሚቴው፤ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ እና ሌሎች ሁለት አባላትን እንዲተኩ በዕጩነት የመረጣቸውን ስድስት ሰዎች ይፋ ያደረገው ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 13/2017 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

በመጪው ሰኔ የኃላፊነት ዘመናቸው ስለሚጠናቀቅ በአዲስ የሚተኩት የምርጫ ቦርድ ሥራ አመራር ቦርድ አባላት ምክትል ሰብሳቢው አቶ ውብሸት አየለ እንዲሁም ዶ/ር አበራ ደገፉ እና ብዙወርቅ ከተተ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እነዚህን የምርጫ ቦርድ አመራሮች ለመተካት መጋቢት ላይ ያቋቋሙት ዕጩ መልማይ ኮሚቴ፤ ከሚያዝያ 1 እስከ ሚያዝያ 21/2017 ዓ.ም. የዕጩዎችን ጥቆማ ሲቀበል ቆይቷል።

በእነዚህ ቀናት ውስጥ ከሕዝብ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የዕጩ ጥቆማዎችን መሰብሰባቸውን የኮሚቴው ሰብሳቢ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቀሲስ ታጋይ እንደገለጹት በኢሜይል፣ በዋትስአፕ፣ በስልክ እና በፖስታ አማካኝት ለኮሚቴው ከቀረቡ ጥቆማዎች ውስጥ "ድግግሞሾች ተጣርተው" 50 ሰዎች መለየታቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በኋላ በተደረገው ማጣራት የዕጩዎቹ ቁጥር በግማሽ ቀንሶ 25 መድረሱን አስረድተዋል።

ከዚህ በኋላም ከተደረገው ሌላ ማጣራት በኋላ ለቃለ መጠይቅ የቀረቡት 12 ሰዎች እንደሆኑ ቀሲስ ታጋይ ገልጸዋል። "ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሦስቱ [የምርጫ ቦርድ የኃላፊነት] ቦታዎች ላይ [ለመተካት] እንዲመርጡ ከ12ቱ ስድስቱን የመጨረሻ ዕጩ (finalist) አድርገን አቅርበናል" ብለዋል።

ቀሲስ ታጋይ ለቢቢሲ የገለጹት ስድስት ዕጩዎች የስም ዝርዝር እንደሚያሳየው ከዕጩዎቹ መካከል ቢያንስ ሦስቱ የተገኙት ከፍርድ ቤቶች ነው።

በቀዳሚነት የተጠቀሱት ዕጩ አቶ ተስፋዬ ንዋይ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት እና የፌደራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ ናቸው። አቶ ተስፋዬ ከዕጩዎቹ መካከል መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በሁለተኛነት የተጠቀሱት አቶ ተክሊት ይመስል ደግሞ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ናቸው። የፌደራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባዩ አቶ ተስፋዬ፤ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንቱን ዕጩነት ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ሦስተኛዋ ዕጩ ወ/ሮ ነሲም አሊ ናቸው። ወ/ሮ ነሲም በሐረሪ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ እንደሆኑ ቢቢሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ወ/ሮ ዳሮ ጀማል እና ወ/ሮ ፍሬሕይወት ግርማ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ አመራር ቦርድ አባል እንዲሆኑ የተመረጡት ሌሎች ሴት ዕጩዎች ናቸው።

ስድስተኛው ዕጩ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ዶ/ር ያሬድ ኃይለማርያም ናቸው። ለ18 ዓመታት ገደማ በዐቃቤ ሕግነት እና በመምህርነት የሠሩት ዶ/ር ያሬድ፤ በዕጩነት መቅረባቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት ዕጩ መልማይ ኮሚቴ የመረጣቸውን ዕጩዎች ዛሬ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ዝርዝራቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚላክ ቀሲስ ታጋይ ገልጸዋል።

ዕጩ መልማይ ኮሚቴው ይፋ ያደረጋቸው ዕጩዎች ብዛት በሕጉ ከተቀመጠው ጋር የሚጣጣም ነው። በ2011 ዓ.ም. የወጣው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ኮሚቴው የሚያቀርባቸው ዕጩዎች ብዛት "የሥራ አመራር ቦርዱ ካሉት ክፍት ቦታዎች በቁጥር እጥፍ" የሚበልጥ መሆን እንዳለበት ደንግጓል።

ኮሚቴው ከቀረቡለት ጥቆማዎች መካከል ዕጩዎችን የሚለየው በሕጉ የተቀመጡትን የቦርድ አባልነት መስፈርቶች ማሟላታቸውን በማረጋገጥ ነው።

ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆን፣ የማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባል አለመሆን፣ "መልካም ሥነ ምግባር እና ሰብዕና" መኖር እንዲሁም "ኃላፊነት ለመሸከም የሚያስችል ከፍተኛ የአመራር ብቃት" ከመስፈርቶቹ መካከል ናቸው።

"ከምርጫ ጉዳዮች ጋር ተያያዥነት ባላቸው በተለይም በሕግ፣ በፖለቲካል ሳይንስ፣ በሕዝብ አስተዳደር፣ በስታትስቲክስ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በሌሎች ተዛማጅነት ባላቸው ዘርፎች ከፍተኛ ሙያዊ ብቃት" መያዝም በመስፈርትነት ተቀምጧል።

ኮሚቴው፤ የተመረጡት ዕጩዎች በዚህ ኃላፊነት ለማገልገል ፈቃደኛ መሆናቸውን የማጋገጥ ኃላፊነት ተጥሎበታል። ቀሲስ ታጋይ እንደሚገልጹት የዕጩ መልማይ ኮሚቴው አሁን የለያቸውን ዕጩዎች ሲመርጥ "ለየት ያለ" አካሄድ መከተሉን ገልጸዋል።

"በዚህኛው ዙር ለየት ያለው፤ የፆታ፣ የብሔር እንዲሁም ደግሞ የሃይማኖት ስብጥር እንዲኖር ታስቦ የተደረገ ምልመላ እና ውድድር ነው" ሲሉ ስድስቱ ዕጩዎች የተመረጡበትን ተጨማሪ መስፈርት አስረድተዋል።

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኮሚቴው የእጩዎች ዝርዝር ከቀረበላቸው በኋላ፤ የቀረቡላቸውን እጩዎች በተመለከተ ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን ምክክር ካደረጉ በኋላ የምርጫ ቦርድ የስራ አመራር ቦርድ አባል ሆነው እንዲሾሙ የሚመርጧቸውን ሰዎች ለይተው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባሉ። የተመረጡትን ሰዎች ሹመት የሚያጸድቀው ይኸው ምክር ቤት ነው።

ሹመት ከሚሰጥባቸው የስራ አመራር ቦርድ ኃላፊነቶች መካከል የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እና ምክትል ሰብሳቢ የሚገኝበት ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለእነዚህ አመራርነት የመረጧቸውን እጩዎች ለይተው ማቅረብ እንዳለባቸውም በአዋጁ ላይ ተጠቅሷል።