ታጋቾችን ለመመለስ የተስማማው ሐማስ አሜሪካ ያቀረበችው የተኩስ አቁም ሐሳብ እንዲሻሻል ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ ላቀረበችው የተኩስ አቁም ስምምነት ምላሽ የሰጠው ሐማስ በሕይወት ያሉ እና የሞቱ ታጋቾችን እንደሚለቅ አስታወቀ።
ሐማስ የአሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲሻሻል ጠይቆ 18 የሞቱ ታጋቾችን ጨምሮ በሕይወት ያሉ እስራኤላዊንን በመልቀቅ ፍልስጤማዊያን እስረኞች እንደሚቀበል አስታውቋል።
ቡድኑ ቋሚ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚፈልግ አስታውቆ እስራኤል ሙሉ በሚሉ ከጋዛ እንድትወጣና እርዳታ ወደ ሰርጡ እንዲገባ ጠይቋል።
ሐማስ ያቀረባቸው ጥያቄዎች አሜሪካ ባቀረበችው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ አልተካተቱም።
ታጣቂው ቡድን በአሜሪካ አሸማጋይነት ለጠረጴዛ የቀረበውን ስምምነት ስለመቀበል አለመቀበሉ በግልፅ ያለው ነገር ባይኖርም ዋሺንግተን ግን እስራኤል ተቀብላዋለች ብሏል።
ሐማስ እንዳለው ምላሹን የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ ለሆኑት ስቲቭ ዊትኮፍ ማድረሱን ተናግሯል።
ዊትኮፍ በለቀቁት መግለጫ "ሐማስ ለዩናይትድ ስቴትስ የላከውን ምላሽ ተቀብያለሁ። በፍፁም ተቀባይነት የሌለውና ወደኋላ የሚጎትተን ነው። ሐማስ እኛ ያቀረብነውን ረቂቅ ተቀብሎ በያዝነው ሳምንት ንግግር መጀመር እንችላለን" ብለዋል።
"በሚቀጥሉት ቀናት የ60 ቀናት የተኩስ አቁም ልንደርስ የምንችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው።"
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ቢሮ በለቀቀው መግለጫ ደግሞ "እስራኤል ዊትኮፍ ያቀረቡትን ሐሳብ ብትቀበልም ሐማስ አሁንም እንደማይቀበለው እያስታወቀ ነው" ብሏል።
በዩናይትድ ስቴትስ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አውሮፓ ኅብረት ሽብርተኛ ቡድን ተብሎ የተፈረጀው ሐማስ "እስራኤል ሙሉ በሙሉ ከጋዛ እንድትወጣና ቋሚ የተኩስ አቁም እንዲደረግ" ይጠይቃል።
ቡድኑ አክሎ እርዳታ ወደ ጋዛ ሰርጥ ያለምንም እንቅፋት እንዲገባ ጠይቆ 10 በሕይወት ያሉ እና 18 የሞቱ ታጋቾችን እንደሚለቅ በምትኩ "በስምምነት" የፍልስጤም እስረኞችን እንደሚቀበል አስታውቋል።
2.2 ሚሊዮን ገደማ ፍልስጤማዊያን በጣም ከባድ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። ሐማስ አሜሪካ ያቀረበችውን ሐሳብ የማይቀበል ከሆነ የሚደርስበት ጫና እንደሚጠነክር ይጠበቃል።
ባለፈው መጋቢት የሐማስ ነባር አመራር እና ዋና ተደራዳሪ የሆኑት ኻሊል አል-ሀያ ሙሉ በሙሉ የተኩስ አቁም የማይደረግ ከሆነ ከፊል ስምምነት እንደማይቀበል አስታውቀው ነበር።
ሐማስ አሁን በአሜሪካ የቀረበውን ረቂቅ ስምምነት የማይቀበል ከሆነ እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ወታደራዊ እርምጃ አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቃለች።
ቡድኑ አሁን ባለበት ሁኔታ የእስራኤልን ጥቃት መቋቋም እንደሚሳነው እየተነገረ ነው።
አሜሪካ ያቀረበችው ሐሳብ የ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት፣ በመጀመሪያው ሳምንት 28 ታጋቾች በሕይወት ያሉም ሆኑ እንዲለቀቁ እንዲሁም 30 ተጨማሪ ታጋቾች ደግሞ በሚቀጥሉት ሳምንታት እንዲለቀቁ ያትታል።
በተጨማሪም 1,236 ፍልስጤማዊያን እስረኞች እንዲለቀቁ እና የ180 ሟች ፍልስጤማዊያን ሬሳ እንዲመለስ ይጠይቃል።
አክሎም ሰብዓዊ እርዳታ በተባበሩት መንግሥታትና በሌሎች ድርጅቶች አማካይነት ወደ ጋዛ እንዲገባ ሐሳብ ያቀርባል።
ዋሺንግተን ረቂቅ የስምምነቱን ሐሳብ ወደ ሐማስ ከመላኩ በፊት እስራኤል እንደምትቀበለው እንደሚያረጋግጥ አስታውቆ ነበር።
ሐማስ ያቀረበውን የማሻሻያ ሐሳብ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ እንደማይቀበሉት ተንታኞች ይገምታሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐማስ ያገታቸውን እስራኤላዊያን እንዲያስለቅቁ ጫና እየበረተባቸው ይገኛል።















