ታሊባን የአፍጋኒስታን ሴቶች ፓርኮችን እንዳይጎበኙ ከለከለ

የታሊባን ፓርኮች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ፓርኮች
ታትሟል

ታሊባን ሴቶችን ከአፍጋኒስታን ሕይወት ይበልጥ በማግለል በካቡል የሚገኙትን መናፈሻ ቦታዎች እንዳይጎበኙ ከልክሏል።

የበጎ አድራጎት ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በመዲናዋ የሚገኙ ፓርኮች አስተዳዳሪዎች ሴቶችን ወደ ፓርኮቹ እንዳያስገቡ ተነግሯቸዋል።

ቡድኑ በእነዚህ መናፈሻ ቦታዎች የእስልምና ሕጎች እየተጠበቁ አይደለም ብሏል።

እአአ ነሐሴ 2021 ታጣቂዎቹ ሥልጣናኑን ከተቆጣጠሩ በኋላ የሴቶች መብት እና ነጻነት በእጅጉ ተገድቧል።

በታሊባን ሕግ መሠረት ሰዎችን በጾታ በመለየት ሴቶች በየሳምንቱ በሦስት ቀናት (እሑድ፣ ሰኞ እና ማክሰኞ) ፓርኮችን እንዲጎበኙ ተፈቅዶላቸው ነበር።

በቀሪዎቹ አራት ቀናት ወንዶች ይጎበኛሉ።

አሁን ደግሞ ሴቶች በወንድ ዘመዳቸው ቢታጀቡም ለመግባት አይፈቀድላቸውም።

“ይህንን ያደረግንበት ምክንያት ባለፉት 15 ወራት ጥረት ብናደርግም ሰዎች ወደ ፓርኩ እየሄዱ የሸሪዓን ሕግ ባለማክበራቸው ነው” ሲሉ የበጎ አድራጎት ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መሐመድ አኪፍ ለቢቢሲ ተናግረዋል። .

"እገዳው ከማህራም (የወንድ አጃቢ) ጋር የሆኑትንም ያልሆኑትንም ሁሉንም ሴቶች የሚመለከት ነው።"

በሴቶች ላይ የተጣለው እገዳ የመጫወቻ ስፍራ ያላቸውን እና ቤተሰቦች ከልጆቻቸው ጋር አብረው የሚጎበኟቸው የመዝናኛ ፓርኮችን ያካትታል።

እገዳው በአሁኑ ጊዜ በዋና ከተማው ውስጥ ብቻ በሥራ ላይ የሚውል ቢመስልም ነገር ግን ቀደም ባሉት ጊዜያት እንዲህ ዓይነቶቹ ደንቦች በመላው ሃገሪቱ ተግባራዊ ይሆናሉ።

ሮይተርስ የዜና ወኪል በካቡል መናፈሻ መግቢያ በር ላይ ያገኛት አንዲት ሴት እንዳትገባ በመከልከሏ ቅር መሰኘቷን አስታውቃለች።

ለደኅንነት ሲባል የመጀመሪያ ስሟን ብቻ የገለፀችው ማሶማ "እናት ከልጆቿ ጋር ስትመጣ ወደ መናፈሻው እንድትገባ መፍቀድ አለባቸው። ምክንያቱም እነዚህ ልጆች ምንም ጥሩ ነገር አላዩም ...፤ ልጆቻቸው መጫወት እና እነሱን ማዝናናት አለባቸው" ስትል ገልጻለች።  

የካቡል ፓርኮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የካቡል ፓርኮች

በታሊባን አስተዳደር ሥር የሚገኙ የአፍጋኒስታን ሴቶች ነጻነታቸውን የሚገድብ ተከታታይ እገዳዎች ተጥሎባቸዋል።

መብታቸውን የጠየቁ በርካታ ሴቶች ተደብድበዋል ።

ሴቶች ያለ ወንድ አጋር ረዥም ርቀት እንዳይጓዙ ተከልክለዋል።

ታሊባን ትምህርት ለሴቶችም ለወንዶችም የሚፈቅድ ቃል ቢገባም ልጃገረዶች አሁንም በአብዛኛዎቹ የሃገሪቱ ክፍሎች ወደ ትምህርት ቤት አልተመለሱም።

በጤና እና ትምህርት ዘርፎች ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ሴቶች ታሊባን እንደገና ወደ ሥልጣን ከተመለሰ በኋላ አብዛኞቹ ወደ ሥራ እንዳይሄዱ ተነግሯቸዋል።

በግንቦት ወር ሴቶች በአደባባይ ኢስላማዊ የፊት መሸፈኛን እንዲለብሱ ትዕዛዝ ቢተላለፍም በአንዳንድ ከተሞች አሁንም ተግባራዊ የማያደርጉ ይታያሉ።

ታሊባን እአአ በ1990ዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ እንደነበረው በሴቶች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ጭቆና አመራር እንደማይኖር ቃል ገብቷል።

በሸሪዓ ሕግ መሠረት የሴቶችን መብት እናከብራለን እንጂ የሴቶችን መማርም መሥራት አንቃወምም ይላል።

ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች በበኩላቸው በከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ላለችው ሃገር የልማት ፈንድ እንደገና ለማስጀመር በሴቶች አያያዝ ላይ መሻሻል ሊኖር እንደሚገባ ለታሊባን ጠቁመዋል።