በሕንድ የእግረኛ መሻገሪያ ደልድይ ተደርምሶ ቢያንስ 141 ሰዎች ሞቱ

ታትሟል

በሕንድ ምዕራባዊ ክፍል በምትገኘው ጉጃራት ግዛት ትላንት ዕሁድ የእግረኛ መሻገሪያ ድልድይ ተደርምሶ ቢያንስ 141 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ደግሞ ለጉዳት መዳረጋቸው ተሰምቷል።

ማቹቹ የተሰኘውን ወንዝ ለማቋረጥ እግረኞች የሚጠቀሙበት ድልድይ ከመደርመሱ በፊት በመቶች የሚቆጠሩ ሰዎች ቆመውበት ነበር።

ከሟቾቹ መካከል አብዛኛዎቹ ህጻናት፣ ሴቶች እና አረጋውያን እንደሆኑ ባለስልጣናት ገልጸዋል። የነፍስ አድን ስራው እስካሁን የቀጠለ ሲሆን የጉጅራት ባለስልጣናት የአደጋውን መነሻ ለማጠራት ምርመራ ጀምረዋል።

የተደረመሰው ድልድይ ከአንድ ክፈለ ዘመን በላይ የቆየ ሲሆን ባለፈው ዓመት ለእድሳት በሚል ዝግ መደረጉ የከተማው ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ ሳንዲፕ ጃሃላ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ኃላፊው ከጥገናው በኃላ ከቀናት በፊት መልሶ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉንም አስታውሰዋል።

ሆኖም እድሳት ከተደረገለት በኃላ “የጥራት ማረጋገጫ አልተሰጠውም” ነበር ብለዋል።

አክለውም ድልድዩ እንዴት እንደፈረሰ፥ የመያዝ አቅሙ፥ ጥቅም ላይ የዋለው ግብዓት በተመለከተ ማዘጋጃ ቤቱ መረጃ እንደሌለው ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ናንድራ ሞዲ አደጋው እጅግ የሚያም ነው ያሉ ሲሆን ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በአደጋው ለሞቱ ሰዎች መንግሥታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።

እስካሁን በቀጠለው የነፍስ አድን ስራ ቢያንስ 177 ሰዎችን መታደግ መቻሉን እና በምሽት ለዕይታ አስቸጋሪ መሆኑ የነፍስ አድን ስራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ባለስልጠናት ተናግረዋል።

በሞርቢ ወንዝ ላይ መሰል አደጋ ሲደር ይህ የመጀመሪያ አይደለም።

እንደ አውሮፓውያኑ በ1997 ከተገነባ አንደ ዓመት ያስቆጠረ እና በወንዙ ላይ የተገነባ ግድብ ያለማቋረጠ በዘነበ ከባድ ዝናብ ምክንያት ተደርምሶ ባስከተለው ከባድ ጎርፍ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ተዘግቧል።