ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጋና በታዳጊ ተጫዋቾች እድሜ ማጭበርበር እግድ ተጣለባት
ጋና ከ17 ዓመት በታች የዕግር ኳስ ተጫዋቾችን ዕድሜ በማጭበርበር የውድድር እገዳ እና የ100 ሺህ ዶላር ቅጣት ተጣለባት።
ጋና ከ17 ዓመት በታች የሴቶች እግር ኳስ ተጫዋቾቿን ዕድሜ ማጭበርበሯ ተረጋግጧል። በዚህ ምክንያትም የውድድር እገዳ እና የ100 ሺህ ዶላር ቅጣት ተጥሎባታል።
ቅጣቱን ውድቅ ለማስደረግ ጋና ይግባኝ ለማለት እየተሰናዳች ነው።
ባለፈው የሴቶች ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ጋና ከሞሮኮ ባደረገችው ጨዋታ በመለያ ምት ተሸንፋ ነበር።
ከጨዋታው በኋላ አሸናፊው የሞሮኮ ቡድን በጋና ስብስብ ላይ የዕድሜ ጥያቄ በማቅረብ ክስ መስርተው ነበር።
ሞርኮ ቢያንስ ሁለት ተጫዋቾች ከዕድሜው ገደብ በላይ መሆናቸውን ባቀረበችው ክስ ጠቁማለች።
ክሱን የተመለከተው ካፍ ጋና ጥፋተኛ መሆኗን አረጋግጫለሁ ብሏል። በመሆኑም ጋና በቀጣዮቹ ሁለት የማጣሪያ ውድድሮች እንዳትሳተፍ እና የ100 ሺህ ዶላር ቅጣት እንድትከፍል ካፍ በይኖባታል።
የጋና ስፖርት ፌደሬሽን ጉዳዩን አስመልክቶ ይግባኝ እንደሚጠይቅ አስታውቋል።
አንድ ከፍተኛ የጋና የስፖርት ኮሚሽን ባለስልጣን ለቢቢሲ አፍሪካ ስፖርት “ክሱ ሲጀመር የመከላከያ ደብዳቤ ጽፈናል” ብለዋል።
“እኛ ካፍ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔውን እንደሚቀለብስ እርግጠኞች ነን” ብለዋል ባለስልጣኑ።
ጋና የወጣት ተጫዋቾችን ዕድሜ በማጭበርበር ስትከሰስ ይህ የመጀመሪያ አይደለም።
እአአ 2014 ጋና ከካሜሮን ጋር ባደረገችው የወንዶች ከ17 ዓመት በታች ጨዋታ ዕድሜ ማጭበርበሯ በመረጋገጡ ከ2015ቱ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ታግዳለች።
በዚህም ምክንያት ኒጀር ላይ በተካሄደው ዝግጅት ጋናን በመተካት ማዕከላዊ አፍሪካ እንድትሳተፍ ተደርጓል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የካሜሮን እግር ኳስ ፌደሬሽን በ44 ተጫዋቾች ላይ የቀረበውን ክስ እየመረመረ ነው። ተጨዋቾቹ የቀረበባቸው ክስ ዕድሜያቸውን እና ማንነታቸውን ደብቀዋል በሚል ነው።
በታዳጊዎች እና በዋናው ፕሪሚየር ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋች ክስ የቀረበባቸው ሲሆን በርካታ የክለብ ፕሬዝዳንቶችም ማጭበርበሩ ውስጥ አሉበት በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
አንድ የካሜሮን እግር ኳስ ፌደሬሽን ባለስልጣን እንዳሉት የዕድሜ ማጭበርበር ክስ ውሳኔ እስከ አርብ የሚጠናቀቅ ሲሆን ጥፋተኛ የተባሉት እስከ 6 ወር እገዳ ይጣልባቸዋል።
የዕድሜ ማጭበርበር እና ማንነትን መደበቅ በተለይም በታችኛው ዕድሜ ለሚጫወቱ ተጫዋቾች በአፍሪካ ትልቅ ችግር ሆኖ ቢቆይም አቤቱታ መስማቱ የተለመደ አልነበረም።
የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማሕበራት ፌደሬሽን ፊፋ ከ17 ዓመት በታች ተጫዋቾችን ትክክለኛ ዕድሜ ለማስላት በ2017 ናይጄሪያ ውስጥ የኤምአርአይ ምርመራ ጀምሯል።