በጋዛ እርዳታ ከአየር ላይ ሲጥል በነበረ የፓራሹት ችግር ምክንያት አምስት ሰዎች ተገደሉ

እርዳታ ከአየር ላይ ሲጣል

የፎቶው ባለመብት, Instagram / ismail_gh2

ታትሟል

በጋዛ እርዳታ ከአየር ላይ ሲጥል በነበረ የፓራሹት ችግር ምክንያት አርብ ዕለት የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ዘገባዎች አመለከቱ።

አምስቱ ሰዎች የተገደሉት ቢያንስ አንድ ፓራሹት እርዳታውን በትክክል ማድረስ ባለመቻሉ እና የእርዳታ እሽጎች በላያቸው ላይ ወድቆ እንደሆነ አንድ የዐይን እማኝ እና የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ማስታወቁን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ዘግቧል።

አንድ በጋዛ የሚገኝ ዶክተርን ዋቢ አድርጎ ኤፍፒ እንደዘገበው አምስት ሰዎች በክስተቱ ተገድለዋል።

ቢቢሲ ይህንን በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻለም።

በዚህ አደጋ ውስጥ የትኛው የእርዳታ ፓራሹት እንደተሳተፈ ግልጽ አይደለም።

በእስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ያለችው ጋዛ ላይ የረሃብ ስጋት ማንዣበቡን ተከትሎ የተለያዩ አገራት ከአየር ላይ በፓራሹት እርዳታ እያደረሱ ይገኛሉ።

ከእነዚህም ውስጥ አሜሪካ፣ ዮርዳኖስ፣ ግብፅ፣ ፈረንሳይ፣ ኔዘርላንድስ እና ቤልጂየም ይገኙበታል።

የዮርዳኖስ ቴሌቪዥን ምንጩን ጠቅሶ እንደዘገበው የዮርዳኖስ አውሮፕላን የሰዎችን ሕይወት በቀጠፈው አደጋ የለበትም ብሏል።

ሲቢኤስ ኒውስ እንደዘገበው ክስተቱ የተፈጠረው አርብ ዕለት በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከረፋዱ 5፡30 አካባቢ ነው።

የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በበኩሉ ከዮርዳኖስ የሮያል አየር ኃይል ጋር በመጣመር በአየር ላይ በፓራሹት እርዳታ የጣሉት ከቀኑ 7፡30 አካበቢ ነው ብሏል።

የማዕከላዊ ዕዙ ጄኔራል ፓትሪክ ራይደር የእርዳታ ፓራሹታቸው በዚህ ክስተት እንዳልተሳተፈ ገልጸው፣ “ሁሉም የእርዳታ ጥቅሎቻችን በሰላም መሬት ላይ እንዳረፉ አረጋግጠናል” ብለዋል።

በቅርቡ ህጻናት በረሃብ እየሞቱ እንደሆነ እና ከጋዛ 2.3 ሚሊዮን ሕዝብ ሩቡ በምግብ እጦት እየተሰቃየ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

አርብ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋራው እና ቢቢሲ ትክክለኛነቱን ባረጋገጠው ቪዲዮ በጋዛ ሰሜናዊ ግዛት በምትገኘው አል ሻቲ ላይ ሲ-17 ከተሰኘ የጭነት አውሮፕላን በፓራሹት አማካኝት ከአየር ላይ እርዳታ ሲቀርብ ይታያል። ይህ አካባቢ ላለፉት ወራት እርዳታ ሙሉ በሙሉ የተቋረጠበት አካባቢ ነው።

አብዛኛዎቹ ትላልቅ የእርዳታ ጥቅሎች በፓራሹት አማካኝነት ሲወርዱ የሚታይ ቢሆንም አንደኛው ፓራሹት ባለመከፈቱ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ ሲወድቅ ይታያል።

በቪዲዮው ላይ ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ አዳጋች ሲሆን፣ አምስቱ ሰዎች የተገደሉበት ክስተት እንደሆነም ማወቅ አልተቻለም።

እርዳታ ከአየር ላይ በፓራሹት የማድረሱን ሂደት የረድኤት ድርጅቶች የሚተቹት ሲሆን፣ ይህ የመጨረሻ አማራጭ መሆን እንዳለት በመግለጽ እና በጋዛ ያለውን ችግርም የሚቀርፍ አይደለም ይላሉ።