አፍሪካ በሩሲያ ጦርነት ታግታለች- ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ

የስንዴ ምርት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ለአፍሪካ ህብረት ሰኞ እለት ባደረጉት ንግግር አፍሪካ በሩሲያ ጦርነት ታግታለች ብለዋል።

ሩስያ ባደረገችው ወረራ እንዲሁም የዩክሬንን እህል ወጪ ንግድ ማገዷ የእህል እና የማዳበሪያ እጥረት አስከትሏል እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ለረሃብ አደጋ አጋልጧል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር በበኩላቸው የአለም መረጋጋትን ወደነበረበት ለመመለስ "አስቸኳይ ውይይት ያስፈልጋል" ብለዋል።

ምዕራባውያን አገሮች ሩሲያ በዩክሬን ሰፊ የእህል ማከማቻ ላይ የጣለችውን እገዳ እንድታነሳ አሳስበዋል።

እገዳው የምግብ ዋጋን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲንር አድርጎታል።

"አፍሪካ በእውነቱ በግዛታችን ላይ ጦርነት በከፈቱት ታግታለች" ብለዋል ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ

በዩክሬን ጥቁር ባህር ወደቦች መተላለፊያ ያጣውን የእህል ክምችት ለማስለቀቅ መንግሥታቸው "ውስብስብ ድርድር" እያደረገ ነው ብለዋል።

“ጦርነቱ ለናንተም ሆነ ለአገሮቻችሁ ሩቅ ቦታ የሚከናወን ሊመስል ይችላል” ሲሉም ለአፍሪካ ህብረት ተናግረዋል ፕሬዚዳንቱ።

“ነገር ግን በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ያለው የምግብ ዋጋ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ አፍሪካውያን ቤተሰቦች ጦርነቱን ወደቀያቸው አምጥቶታል” ብለዋል።

የፕሬዚዳንት ዜለንስኪ የአፍሪካ ህብረት ንግግር ለአህጉሪዊው አካል ንግግር ለማድረግ ከጠየቁ ከአስር ሳምንታት በኋላ የመጀመሪያው ነው።

ቢቢሲ እንደተረዳው 55 የሀገር መሪዎች በበይነ መረብ ለነበረው ጉባኤ ቢጋበዙም የተገኙት አራት ብቻ ናቸው። የተቀሩት አገሮች ተወካዮቻቸው እንዲሳተፉ አድርገዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ለጀመረችው ጦርነት የአፍሪካ ሃገራት የሰጡት ምላሽ የተከፋፈለ ነው።

 በመጋቢት ወር 17 የአፍሪካ ሀገራት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወረራውን በማውገዝ ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል።

ነገር ግን ሰኞ እለት የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ማኪ ሳል ፕሬዚዳንት ዜለንስኩኪን ለህብረቱ ንግግር ስላደረጉ አመስግነዋል።

“አፍሪካ የአለም አቀፍ ህግ ደንቦችን ታከብራለች። ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን እና የንግድ ነፃነትን በማክበር ረገዱ ያላት ቁርጠኝነት ይቀጥላል” ሲሉ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።

መጀመሪያ ላይ የአፍሪካ ኅብረት ከፕሬዚዳንት ዜለንስኪ ጋር ውይይት አለመፈለጉን እንዲሁም ከሚሏቸው ጉዳዮች ጋር ሙሉ በሙሉ የአለመስማማት ሁኔታም ታይቶ ነበር።

ከሳምንታት በፊት ሊቀመንበር ማኪ ሳል ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋርም ተወያይተዋል። የአፍሪካ ሀገራት በዩክሬን ጦርነት ንፁሀን ሰለባ መሆናቸውን እና ሩሲያ ስቃያቸውን በማቃለሉ ረገድ ልትረዳ እንደሚገባ ለፑቲን ተናግረዋል።