የራያ አካባቢ የ12ተኛ ክፍል ተፈታኞች በወልድያ ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን እንዲጨርሱ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, woldia university
የትግራይን ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል ስር በተጠቃለሉት የራያ አካባቢዎች ባለው አለመረጋጋት ምክንያት ትምህርት የተቋረጠባቸው ከ800 በላይ የዘንድሮ 12ተኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች፤ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ እና ማጠናከሪያ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን የሰሜን ወሎ ዞን እና የአላማጣ ከተማ አስተዳደሮች ገለጹ።
ከራያ አካባቢዎች የተውጣጡት ተማሪዎች ከትናንት ሐሙስ ግንቦት 9፤ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ወልዲያ ዩኒቨርስቲ መግባት መጀመራቸውን የዩኒቨርስቲው ምንጭ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ከሚያዝያ መጀመሪያ በራያ አካባቢዎች በሚገኙ የአማራ እና የትግራይ ክልል ታጣቂዎች መካከል የተካሄደውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ ከትግራይ ጦርነት በኋላ በአማራ ክልል ስር በተጠቀለሉት የራያ ወረዳ እና የከተማ አስተዳደሮች የመንግስት አገልግሎት ቆሟል።
የአላማጣ ከንቲባን ጨምሮ በሌሎቹ የራያ አካባቢዎች ትምህርት ከተቋረጠ ከአንድ ወር በላይ እንደሆነ በአማራ ክልል የተሾሙት የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት ዘንድሮ ለ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚቀመጡ የአካባቢዎቹ ተማሪዎች “ከዚህ በኋላ ለፈተናው ተዘጋጅቶ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል ሁኔታ ላይ እንዳልሆኑ” ከንቲባው ጠቅሰዋል።
ተመሳሳይ ሀሳብ የሚያነሱት የሰሜን ወሎ ዞን የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰጠ ታደሰ፤ “ከዚያው አካባቢ ሆነው የማጠናከሪያ ትምህርትም የቀራቸውን [የትምህርት] ይዘቶች መሸፈን ስለማይቻል ወደዚህ ቀረብ ብለው ይሸፍኑ የማጠናከሪያ ትምህርት ይሰጣቸው የሚለውን አላማ ያደረገ ነው” ሲሉ ተማሪዎቹ ወደ ወልዲያ ዩኒቨርስቲ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል።
የአላማጣ ከንቲባ አቶ ኃይሉ እንደሚናገሩት ተማሪዎቹ ይህንን እድል እንዲያገኙ የተደረገው በአካባቢው ባለው ሁኔታ ወደ ቆቦ ከተማ ሸሽተው የነበሩት እና በአሁኑ ሰዓት ወደ አላማጣ ከተማ የተመለሱት ባለስልጣናት፣ የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር እንዲሁም የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ከተነጋገሩ በኋላ ነው።
ተማሪዎቹ እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ በሚኖራቸው ቆይታ በዩኒቨርሲቲው መምህራን የማካካሻ ትምህርት እንደሚያገኙም አክለዋል።
ወልዲያ ዩኒቨርስቲ ከዚህ ቀደምም 100 መምህራንን በመመደብ በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ለ12ተኛ ክፍል ተፈታኞች የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጥ እንደነበር የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊው አቶ ሰጠ አስታውሰዋል።
ኃላፊው፤ “የዞኑ ትምህርት ቤቶች በአቅራቢያቸው ባለው ትምህርት ቤት የአዳር ፕሮግራምም እየተመቻቸላቸው እያጠኑ ያሉ አካባቢዎች አሉ። እነዚህኞቹ [የራያ አካባቢ ተማሪዎች] ደግሞ ወደዚያ ተንቀሳቅሶ ሄዶ የማጠናክሪያ ትምህርትን ለመስጠት አስቻይ ሁኔታ ስለሌለ ወደዚህ መጥተው የቲቶሪያል ፕሮግራም እንዲያገኙ [እየተደረገ ነው]” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, alamata city administration
በዚህ አይነት መንገድ ከትናንት ጀምሮ ወደ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ እየገቡ ያሉት ከአላማጣ ከተማ፣ ራያ አላማጣ ወረዳ እና ባላ ወረዳ የተወጣጡ 850 ገደማ የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎች መሆናቸውን የአላማጣ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥ 572 ያህሉ የአላማጣ ከተማ ተማሪዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ተማሪዎቹ በመጪው እሁድ በዩኒቨርስቲው ገለጻ ተደርጎላቸው ሰኞ ዕለት ትምህርት እንደሚጀምሩም አቶ ኃይሉ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ምንጭ ከራያ አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎች ከትናንት ግንቦት 8/ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ዩኒቨርስቲው እየገቡ መሆኑን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ምንጩ፤ “[በራያ አካባቢዎች] በተፈጠረው ችግር የ12ተኛ ክፍል ትምህርት ስለተስተጓጎለ [ዩኒቨርስቲው] ከዞኑ የትምህርት መምሪያ ጋር ተነጋግሮ ተማሪዎች [ወደ ዩኒቨርሰቲው] እየገቡ እንደሆነ መረጃ አለኝ” ብለዋል።
ይሁንና ከዞኑ ጋር የተደረገው ስምምነትም ሆነ የተማሪዎቹ በዩኒቨርስቲው ሲቆዩ የምግብ ወጪያቸው በማን እንደሚሸፈን እስካሁን ድረስ በይፋ እንዳልተገለጸ አስረድተዋል።
ቢቢሲ ስለጉዳዩ ጥያቄ ያቀረበላቸው የወልድያ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አበበ ግርማ፤ “የአካባቢው [ባለስልጣናት] መግለጫ ሰጥተዋል” በማለት ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ተማሪዎቹ የመኝታ እና የምግብ አገልግሎት በዩኒቨርስቲው ውስጥ እንደሚያገኙ የሚናገሩት የአላማጣ ከንቲባ አቶ ኃይሉ፤ ተማሪዎቹ ለሚያገኙት የምግብ አቅርቦት ከአምስት እስከ ስድስት ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።
ይህ ወጪ ዩኒቨርስቲው ያለውን በጀት “የሚያዛባ” በመሆኑን የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለመሸፈን የተለያዩ መንገዶች በአማራጭነት መያዛቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ፈንድ ማጠያየቅ እንዲሁም ከአካባቢው ማህበረሰብ ገንዘብ ማሰባሰብ የመጀመሪያዎቹ ሁለት አማራጮች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰጠም፤ “ሊያግዘን የሚችል ሰው ከተገኘ በድጋፍ መልክ እየጠየቅን ነው” ሲሉ የከንቲባውን ሀሳብ አጠናክረዋል።
እነዚህ አማራጮች የማይሳኩ ከሆነ ተማሪዎቹ የመጡባቸው የራያ አካባቢ አስተዳደሮች ወጪውን ለመሸፈን መታቀዱን ከንቲባው አቶ ኃይሉ አስረድተዋል።
“[ከዚህ ቀደም] ትንሽ ከሰበሰብነው ገቢ ቅድሚያ እንሰጣለን። [የተሰበሰበው ገቢ] ዝግ [አካውንት] ላይ ነው ያለው። ከክልሉ ጋር ተነጋግረን አስከፍተን እንከፍላለን” ሲሉ በመጨረሻ አማራጭነት የተያዘውን እቅድ ገልጸዋል።












