የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የምዕራብ ዳርፉር አስተዳዳሪን መግደሉ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሱዳን ባለስልጣናት የምዕራብ ዳርፉር ግዛት አስተዳዳሪ በፈጥኖ ደራሽ ኃይል መገደላቸውን ተናገሩ።
አስተዳዳሪው ካሚስ አባካር የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና አጋር ሚሊሻዎችን በዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ አቅርበውባቸው ነበር።
ከመገደላቸው ከሰዓታት በፊት ነው በማሳሊት ብሔር ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን ፈጽመዋል ሲሉ አስተዳዳሪው የከሰሷቸው።
አል ጀኒና በተሰኘች ግዛት የተገደሉት አስተዳዳሪው ጥቃቱ በከተማው በተንሰራፋ ሁኔታ መስፋፋቱን አስጠንቀቅቀው ነበር።
በተጨማሪም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ እንዲገባም ጠይቀው ነበር ተብሏል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ለቀረበበት የግድያ ክስ ምላሽ አልሰጠም።
በኒያላ እና ዛሊንጌ ተመሳሳይ ግጭቶች መፈጠራቸው ተዘግቧል።
በሱዳን በተቀሰቀሰው ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የተገደሉ ሲሆን ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን አፈናቅሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በዳርፉር በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ብሄርን ልየታ ያደረገ ጥቃት እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ ጾታዊ ጥቃቶችና መደፈሮች ተባብሰው መቀጠላቸው እንዳሳዘናቸውም ዋና ጸሓፊው ገልጸዋል።
የዳርፉር ግዛት ከአውሮፓውያኑ 2000 ጀምሮ የአረብ ሚሊሻዎች አረብ ያልሆኑ አማጺያንን ለመዋጋት መሰማራታቸውን ተከትሎ ተደጋጋሚ ጦርነት የተስተናገዱበት ስፍራ ነው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ከታዩ ፍጅቶች አንዱ በሆነው የዳርፉር እልቂት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተገድለዋል እንዲሁም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቀያቸውን ለቀው ተፈናቅለዋል።
በሱዳን ጦር መሪ መሪ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መሪ ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ መካከል ጦርነቱ የተቀሰቀሰው ሚያዝያ 7/ 2015 ዓ.ም ነበር።
የሚሊዮኖች ህይወት ስጋት ውስጥ በገባበት በዚህ ግጭት መሃል ሁለት ጄኔራሎች በባላንጣነት በጽንፍ ስፍራ ተቀምጠዋል።












