ፕሬዝዳንት ፑቲን የሩሲያ ጦር ግስጋሴውን እንደሚያጠናክር ተናገሩ

ታትሟል

የሩሲያ ወታደሮች ሊሲቻንስክ ከተማን ከተቆጣጠሩ በኋላ ፕሬዝዳንት ፑቲን የመከላከያ ሚንስትራቸውን ጦርነቱን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት በሩሲያ ቴሌቪዥን ቀርበው ነው። የሊሲቻንስክ መያዝ ማለት ሙሉ የሉሃንስክ ክልል በሩሲያ እጅ መውደቅ ማለት ነው።

የከተማዋ አስተዳዳሪ ቀደም ብለው አካባቢውን ለቅቀን ስለወጣን ሩሲያውያን አካባቢውን ከርቀት ማውደም አይጠበቅባቸውም ብሎ ነበር።

 አንድ የዩክሬን ባለስልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት “አሁን ኃይላችን በሌላ ግንባር ተሰልፏል። ሉሃንስክን ለሩሲያ ማስረከብ በጣም የሚያም ነው። ግን ደግሞ ይህ የአንድ ግንባር ጉዳይ እንጅ አጠቃላይ የጦርነቱን ፍጻሜ አያሳይም” ብለዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ እንዳሉት ደግሞ ከምዕራባውያን የሚቀርብ ዘመናዊ መሣሪያ በመኖሩ የዩክሬን ጦር ድጋሚ ሉሃንስክን እንደሚቆጣጠር አረጋግጠዋል።

ሩሲያ አሁን ከሉሃንስክ ቀጥሎ ባለችው የዶኔስክ ግዛት ከተሞችን መደብደቡን አጧጡፋዋለች። ዩክሬናውያን ወታደሮች እንደሚሉት በተለይ በሊሲቻንስክ እና ባክሙት መካከል ያለችው ስሎቭያንስክ ከተማ ዋነኛዋ ኢላማ ነች። 

ሁለቱ ዶኔስክ እና ዶንባስ ክልሎች ተጣምረው ነው በኢንዱስትሪ የበለጸገችውን የዶንባስ ግዛትን የሚፈጥሩት። ፕሬዝዳንት ፑቲን ለመከላከያ ሚንስትሩ ሰርጊ ሾይጉ “ሉሃንስክን የተቆጣጠሩት ወታደሮች ዕረፍት አድርገው ለላቀ ድል መዘጋጀት አለባቸው” ብለዋል።

“ሌሎቹ የምዕራብ እና የምሥራቅ የወታደራዊ ክንፎች ከአሁን በፊት በተሳኩት እቅዶች ልክ ጥቃታቸውን መፈጸም ይኖርባቸዋል” ብለዋል ፕሬዝዳንት ፑቲን። 

በእነዚህ አካባቢዎችም በሉሃንስክ ያገኙትን ድል እንደሚደግሙት ፕሬዝዳንቱ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል። ይፋዊው ጦርነት በየካቲት 24 ከመታወጁ በፊት ሉሃንስክ እና ዶኔስክ ራሳቸውን የቻሉ ነጻ ግዛት መሆናቸውን እውቅና ሰጥተው ነበር።

ሩሲያ ክሪሚያን ከተቆጣጠረችበት 2014 ጀምሮ በሩሲያ የሚደገፉ የአካባቢው ኃይሎችም ከዩክሬን ጋር ሲዋጉ ቆይተዋል። ከሳምንት በፊት የሩሲያ ወታደሮች በከባድ ድብደባ ወደ ፍርስራሽነት የቀየሯትን ሴቨሮዶኔስክ ከተማን ተቆጣጥረዋል።

በዩክሬኗ ዶንባስ ግዛት ሲዋጉ የነበሩ ሦስት የዩክሬን ወታደሮች እንደሚሉት በአካባቢው የሚካሄደው ጦርነት እጅግ አውዳሚ ነው።

“በአካባቢው የዩክሬን ጦርም ይኑር ንጹሃን ሩሲያውያን ምንም ልዩነት ሳያደርጉ ከተማንና መንደርን ያወድማሉ፤ ምንም ግድ አይሰጣቸውም” ብሏል ከበጎ ፈቃደኝነት ዘማች የተመለሰው ማርክ።

ምንም እንኳን ስለዝርዝሩ ማውራት ባይፈልጉም የደረሰውን ጉዳት ግን “እጅግ ትልቅ ጉዳት” በማለት ይገልጹታል። “አብረናቸው የተማርነው፣ አብረናቸው ምግብ የተጋራናቸው፣

እንደእኛ ያሉ ወዶ ዘማቾች፣ እና ሌሎች ብዙዎች አልቀዋል” ብለዋል የአይን ምስክሮቹ። ስለሊሲቻንስክ መያዝ የተናገሩት ሃይዳይ “ጦራችን ለረጅም ጊዜ ከተማዋን ይዞ ቆይቷል።

አሁን ግን ሩሲያ በከባድ መሣሪያ እና ተተኳሽ የበላይነት አላት። በቀላሉ ከርቀት ሆነው የማውደም ዕድሉ ስላላቸው እዚያ መቆየቱ ትርጉም የለውም” ብለዋል።

ወታደሩ ወደ ዶንባስ ክልል ቢያመራም አሁንም 10 ሺህ በላይ ሰዎች እዚያው ከተማው ውስጥ ቀርተዋል።

ዩክሬን የወደሙባትን መሰረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት 750 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋት ለእዚህም የሩሲያ ቱጃሮች ማዋጣት እንዳለባቸው የዩክሬን ጠቅላይ ሚንስትር ዴኒስ ሺሚሃል ተናግረዋል።

የአውሮፓ ሕብረት ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ዴር ሌየን “ሩሲያ ዩክሬንን አውድማ ምድረ በዳ ማድረግ ትፈልጋለች። በእዚህ ጦርነት ግን ጠንካራ እና ዘመናዊ አገር ትሆናለች” ብለዋል።