ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሜክሲኮ ከቴክሳስ ተጠርዘው የሚላኩ ስደተኞችን ፈጽሞ አልቀበልም አለች
ሜክሲኮ፣ የአሜሪካዋ ግዛት ባጸደቀችው ጠንካራ የስደተኛ ሕግ ምክንያት ከቴክሳስ ተጠርዘው የሚመለሱ ስደተኞችን አልቀበልም አለች።
የአገሪቱ መንግሥት “ሜክሲኮ ከቴክሳስ የሚመለሱ ማንኛውንም ስደተኞች በምንም ሁኔታ አትቀበልም” ብሏል።
ሜክሲኮ ይህንን መግለጫ ያወጣችው የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕጉ ተግባራዊ እንዲሆን መፍቀዱን ተከትሎ ነው።
ይህ ኤስቢ4 የተባለው ሕግ የቴክሳስ ፖሊስ የአሜሪካ - ሜክሲኮን ድንበር በሕገ ወጥ መንገድ አቋርጧል ተብሎ የተጠረጠረን ስደተኛ እንዲያስር ይፈቅዳል።
ከዚህም በተጨማሪ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ቴክሳስ የሚገቡ ስደተኞች እስከ 20 ዓመት የሚደርስ እስራት እንዲቀጡ ያዛል።
የባይደን አስተዳደር ሕጉን “ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ” ሲሉ ተቃውመውታል።
የሜክሲኮ ባለሥልጣናትም ሕጉን 'ፀረ ስደተኛ' ሲሉ የተቹት ሲሆን ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት ሊያወሳስበው እንደሚችልም አስጠንቅቀው ነበር። ይህ ስጋታቸው በአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤትም ተስተጋብቷል።
ቀደም ብሎ ፍርድ ቤቶች የአገሪቷን የኢምግሬሽን ሕግ ማስፈፀም የሚችሉት ግዛቶች ሳይሆኑ የፌደራል መንግሥቱ ብቻ ነው ብለው ነበር።
የአሜሪካን ድንበር በሕገ ወጥ መንገድ ማቋረጥ ወንጀል ቢሆንም እነዚህ ጥሰቶች የሲቪል ጉዳይ ተደርገው የሚታዩትም በኢሚግሬሽን የፍርድ ቤት ሥርዓት ነው።
የሜክሲኮ የፍትሕ ሚኒስቴር ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ እንዳለው ግዛቶች አሊያም የአካባቢ ባለሥልጣናት ስደተኞችን እንዲቆጣጠሩ፣ ዜጎችና የውጭ ዜጎችን ማሰር እና መመለስ የሚፈቅደውን ሕግ ሜክሲኮ አትቀበለውም።
መግለጫው ጨምሮም ሕጉ በቴክሳስ የሚኖሩ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ሜክሲኮውያን ሰብዓዊ መብት ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር አትቷል።
የሜክሲኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ኤስቢ4 ስደተኛ ማኅበረሰቦችን ለጥላቻ ንግግርና ለአድልዎ በማጋለጥ አስከፊ ሁኔታን ይፈጥራል ብሏል።
ሚኒስቴሩ ኤስቢ4 ሕግን ለማስቆም በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሚደረገውን ሕጋዊ ጥረት እንደሚቀላቀልም አስታውቋል።
ዋይት ሃውስ የፌደራል የታችኛው ፍርድ ቤቱ ስለ ሕጉ ሕጋዊነት ላይ ጥያቄ ባነሳበት ሁኔታ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ማስተላለፉን ተችቷል።
የዋይት ሃውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሪን ጂን ፔሪ በሰጡት መግለጫ “ኤስቢ4 በቴክሳስ ያሉ ማኅበረሰቦችን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ብቻ ሳይሆን በሕግ አፈጻፀም ላይ ጫና ያሳድራል። ከዚህም ባሻገር በደቡባዊ ድንበር ላይ ትርምስ እና ግርታን ይፈጥራል” ብለዋል።
ሆኖም ሪፖብሊካኑ የቴክሳስ ገዥ ግሬግ አቦት፣ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አዎንታዊ ለውጥ በማለት አወድሰውታል።
ምክትላቸው ዳን ፓትሪክም “ ሕገ ወጥ ስደተኞችን ማሰር እና ወደ ሜክሲኮ ጠርዞ መላክ አሊያም ወደ እስር ቤት መወርወር እንጀምራለን” ሲሉ ማክሰኞ ዕለት ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።
ኤስቢ4 ሕግ የተፈረመው ታኅሳስ ወር ላይ ሲሆን ከመታገዱ በፊት ሚያዝያ 5 ላይ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ነበር።
አሁንም ጉዳዩ ኒው ኦርሊያንስ ወደሚገኘው የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ይመለሳል። የቃል ክርክሩም ለረቡዕ ቀጠሮ ተይዞለታል።
በክርክሩ ማንም ቢያሸንፍም ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መልሶ የመውሰድም አማራጭ አለ።
ሪፐብሊካኖች ብዙውን ጊዜ የዲሞክራቱን ባይደን አስተዳደር የአሜሪካ-ሜክሲኮን ድንበር በሚይዝበት አግባብ ይወቅሳሉ። ኅዳር ላይ ከሚካሄደው የዋይት ሐውስ ምርጫ በፊት ይህ የሕዝብ አስተያየት መኖሩም ለመራጮች ትልቅ ስጋት ነው።
የካቲት ወር ላይ በአሜሪካ ተቋም በተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት መሠረት አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት አሜሪካውያውያን ስደት፣ ኢኮኖሚ እና የዋጋ ንረት የአገሪቷ ትላልቅ ችግሮች እንደሆኑ ያምናሉ።