ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እንግሊዝ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ መገልገያዎችን ልታግድ ነው
በእንግሊዝ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ እንደ ቢላ፣ ሹካ፣ ማንኪያ፣ ሰሀን እና ትሪ የመሳሰሉ የፕላስቲክ መገልገያ እቃዎች ሊከለከሉ መሆኑን መንግሥት አስታወቀ።
ይሁን እንጂ ክልከላው ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን አልተገለጸም።
ውሳኔው የተላለፈው በስኮትላንድ እና ዌልስ የተወሰደውን ተመሳሳይ እርምጃ ተከትሎ ነው።
የአካባቢ ጥበቃ ኃላፊዋ ቴሬስ ኮፊይ እርምጃው ለመጪው ትውልድ አካባቢን ጠብቆ ለማቆየት ይረዳል ብለዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ተማጋቾች እርምጃውን በበጎ መልኩ የተቀበሉት ሲሆን፣ ከዚህ በበለጠ የፕላስቲክ ቁሳቁሶችን ለመቀነስ የሚረዳ ስትራቴጂ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የመንግሥት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በእንግሊዝ በየዓመቱ 1.1 ቢሊየን የሚሆኑ ለአንድ ጊዜ ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ ሰሃኖች እና ከ4 ቢሊየን የሚበልጡ የፕላስቲክ መመገቢያ ቁሳቁሶች አገልግሎት ላይ ይውላሉ።
አገልግሎት ላይ ከዋሉ በኋላ የሚወገዱ የፕላስቲክ ቁሳቁሶች ብዙውን ጊዜ የማይበሰብሱ ሲሆን፣ በአፈር ውስጥ ሆነው ለበርካታ ዓመታት መቆየት ይችላሉ።
እነዚህ ቁሳቁሶች ምንም እንኳን ምግብን በንጽህና ለመያዝ ጠቃሚ ቢሆኑም በሌላ በኩል ደግሞ ውሃንና አፈርን ሊበክሉ ይችላሉ።
የአካባቢ ጥበቃ፣ ምግብ እና የገጠር ጉዳዮች መሥሪያ ቤት ከብዙ ምክክር በኋላ ያጸደው ይህ እርምጃ በመጪው ቅዳሜ ታትሞ እንደሚወጣም ተገልጿል።
እንደ የአካባቢ ጥበቃ መሥሪያ ቤቱ ከሆነ በእንግሊዝ የሚኖር እያንዳንዱ ግለሰብ በዓመት ለአንድ ጊዜ ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ 18 የፕላስቲክ ሰሃኖችን እና 37 ለመመገቢያ የሚውሉ እንደ ቢላ፣ ማንኪያ እና ሹካ ያሉ የፕላስቲክ ምርቶችን ይጠቀማል።
ከእነዚህ መካከል መልሰው አገልግሎት የሚሰጡት 10 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው።
ኃላፊዋ እንዳሉት የሚታገዱት በዋናነት ከሬስቶራንት ምግብ እና መጠጥ ለመውሰድ የሚያገለግሉ ለአንድ ጊዜ ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ የፕላስቲክ ምርቶች ናቸው።
“ወደፊትም ይህንን ችግር ለማስወገድ እርምጃ ለመውሰድ ቆርጬ ተነስቻለሁ። በቅርብ ዓመታት ውስጥ ወሳኝ እርምጃዎችን ወስደናል፤ ግን የበለጠ መስራት እንዳለብን እናውቃለን። እናም በድጋሚ የሕዝቡን ጥያቄዎች አዳምጠናል” ብለዋል።
እርምጃውም በቢሊየን በሚቆጠሩ ፕላስቲኮች የሚፈጠር ብክለትን ለመከላከል እና ለመጪው ትውልድ ተፈጥሯዊ አካባቢን ጠብቆ ለማቆየት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ኃላፊዋ ተናግረዋል።
ስኮትላንድም ከዚህ በፊት ተመሳሳይ እርምጃዎችን ወስዳለች።
እንግሊዝ ለአንድ ጊዜ ብቻ አገልግሎት ላይ የሚውሉ እንደ የፈሳሽ መመገቢያ (ስትሮው)፣ ማማሰያዎች እና የኩክ ማውጫዎችን የመሳሰሉ የፕላስቲክ ምርቶችን የከለከለችው እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 ነበር።
ስኮትላንድ ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚውሉ የፕላስቲክ መገልገያ እቃዎችን በንግድ ተቋማት ላይ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አግዳለች።
በዌልስ ውስጥም ተመሳሳይ እገዳን የሚመለከቱ ሕጎች ታኅሣሥ ላይ የጸደቁ ሲሆን፣ በተያዘው 2023 ዓመት ተግባራዊ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
በእንግሊዝ አሁን ላይ የተወሰደው እርምጃ በገበያ ማዕከላት (ሱፐርማርኬቶች) ወይም በሱቆች ያሉ ቁሳቁሶችን የሚያጠቃልል ባይሆንም መንግሥት ይህንን በሌላ መልኩ እንደሚፈታው ገልጿል።
የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች የሆነው ግሪንፒስ ዩኬ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተሟጋቿ ሜጋን ራንድልስ፣ ድርጅታቸው መንግሥት የወሰደውን እርምጃ እንደተቀበለው ገልጻ ተጨማሪ እርምጃዎች እንደሚያስፈልጉ ተናግራለች።
“ከፕላስቲክ ጎርፍ ጋር እየታገልን ነው። እርምጃው ቧንቧውን ከመዝጋት ይልቅ የሚፈሰውን እንደ መጥረግ ነው” ብላለች።
በመሆኑም መንግሥት የፕላስቲክ አጠቃቀምን እንዴት መቀነስ እንደሚቻል የሚያሳይ እና እንደገና ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉበት ዘዴ ላይ “ትርጉም ያለው” ስትራቴጂ እንዲያወጣ ጠይቃለች።