በሄይቲ የተጠረጠሩ የወንበዴ ቡድን አባላት በደቦ ተቃጥለው ተገደሉ

ታትሟል

በሄይቲ በፖሊስ ሲፈለጉ የነበሩ 13 ተጠርጣሪ የወንበዴ ቡድን አባላት በደቦ ተገደሉ።

ተጠርጣሪዎቹ ሰኞ ዕለት በፖርት ኦ ፕሪንስ ተቃጥለው ከመገደላቸው በፊት የማኅበረሰቡ አባላት በጎማ ክፉኛ እንደደበደቧቸው ተገልጿል።

ፖሊስ እንዳስታወቀው ይህ ከመሆኑ በፊት ከተጠርጣሪዎቹ ላይ መሣሪያቸውን እንደወሰዱባቸው ነው።

የማኅበረሰቡ አባላት ተጠርጣሪዎቹን እንዴት ሊይዟቸው እንደቻሉ ግን ፖሊስ አላብራራም።

በሄይቲ እንደ አውሮፓውያኑ ሐምሌ 2021 ፕሬዚደንት ጆቨኔል ሞኢስ ከተገደሉ በኋላ ሕገ ወጥነት ተበራክቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ሰኞ እለት በወጣው ሪፖርት እንዳለው በዋና መዲናዋ ያለው የደኅንነት ችግር በጦርነት ውስጥ ካሉ አገራት ጋር ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ደርሷል።

የታጠቁ ወንበዴዎች የያዙትን ግዛት የማስፋፋት ፉክክሩ በመቀጠሉ ከፖሊስ ጋር እና ከተቀናቃኝ የወንበዴ ቡድኖች ጋር የሚፈጠር ግጭት ተደጋጋሚ በመሆኑ የበርካታ ሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉንም ሪፖርቱ አክሏል።

እንደ ተመድ ከሆነ ከአውሮፓውያኑ ሚያዚያ 14 እስከ 19 ባሉት አምስት ቀናት ብቻ 18 ሴቶች እና ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ ወደ 70 የሚጠጉ ሰዎች በወንበዴዎች በተፈጸመ ጥቃት ተገድለዋል።

በርካታ ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት የተዘጉ ሲሆን ጥቃቱ ሌሎች የማኅበረሰብ አገልግሎቶችንም አስተጓጉሏል።

“ የሄይቲ ሕዝቦች በአስርት ዓመታት ውስጥ አስከፊ በሆነው የሰብዓዊ መብት ቀውስ እና በአስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እጦት መሰቃየታቸውን ቀጥለዋል” ብሏል ሪፖርቱ።

ከፕሬዚደንት ሞኢስ ግድያ በኋላ የካሪቢያን አገሯ በጠቅላይ ሚኒስትር አሪል ሄንሪ እየተመራች ሲሆን አሁን ከዋና ከተማዋ 60 በመቶ የሚገመተውን አካባቢ የሚቆጣጠሩትን የወንበዴ ቡድኖች ግን መቆጣጠር ተስኗቸዋል።

ሄንሪ እና የተመድ ባለሥልጣናት ፖሊስ ከወንጀለኛ ቡድኖች ጋር የሚያደርገውን ፍልሚያ ለማገዝ በአካባቢው ዓለም አቀፍ ኃይል እንዲሰማራ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል።

ሆኖም እስካሁን ይህንን ኃላፊነት የተቀበለ አገር የለም። አሜሪካ፣ ካናዳ ኃላፊነቱን እንድትወስድ ለማግባባት ብትሞክርም ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ እስካሁን አልተቀበሉትም።

ሄንሪ ለረጅም ጊዜ የተራዘመው ምርጫ እንዲካሄድም የጸጥታ ሁኔታን ማረጋገጥ ቁልፍ ነው ብለዋል።