ተከላካዩን በቀይ ካርድ ያጣው አርሰናል የመጀመሪያ ሽንፈቱን ቀመሰ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ፈረንሳዊው ተከላካይ ዊሊያም ሳሊባ በቀይ የተሰናበተበት አርሰናል የወድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ሽንፈት ገጥሞታል።

ከሜዳው ውጪ ከቦርንመዝ ጋር የተጫወተው አርሰናል በቪታሊቲ ስታድየም 2 ለ 0 ከመሸነፉም በላይ ሳሊባን ለቀጣይ ጨዋታ ላያገኘው ይችላል።

በ30ኛው ደቂቃ ወደ አርሰናል ግብ እየገሰገሰ የነበረውን ኢቫኒልሰን ጠልፎ የጣለው ሳሊባ፣ መጀመሪያ ቢጫ ካርድ ነበር የተመለከተው።

ነገር ግን የመሐል ዳኛው በጆሮ ማዳመጫቸው ጨዋታውን በቪዲዮ ከሚከታተሉ (ቪኤአር) አጋሮቻቸው ጋር ከመከሩ በኋላ ከሜዳው ጥግ የሚገኘውን ‘ስክሪን’ ተመልክተው ቢጫውን በመሻር በቀይ ካርድ አሰናብተውታል።

የፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫውን ለማንሳት እየታገለ የሚገኘው አርሰናል በያዝነው የውድድር ዘመን ቀይ ካርድ በዝቶበታል።

አርሰናል ከዚህ ቀደም ከብራይተን እና ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በነበረው ጨዋታ ተጫዋቾቹ በቀይ ካርድ መሰናበታቸው የሚታወስ ነው።

ምንም እንኳ ሁለተኛውን አጋማሽ በ10 ተጫዋች የጀመረው አርሰናል በሩን ሳይስደፍር ቢቆይም በ70ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት መሬት ለመሬት የተሻገረችውን ኳስ የቦርንመዙ ክሪስቲ ወደ ጎል ቀይሯታል።

በ79ኛው ደቂቃ በክረምቱ የዝውውር መስኮት የክለቡን ክብረ ወሰን ሰብሮ በ40 ሚሊዮን ፓወንድ የፈረመው ኢቫኒልሰን በአርሰናሉ በረኛ ተጠልፎ መውደቁን ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ጀስቲን ክላይቨርት ወደ ግብ ቀይሯታል።

ባለፉት አራት ጨዋታዎች 13 ግቦች ተቆጥሮባቸው ሁለት ግብ ብቻ አስቆጥረው የተሸነፉት ቦርንመዝ አርሰናልን በመርታት በሊጉ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

አርሰናል ይህን ጨዋታ ቢያሸንፍ ዛሬ እሑድ አመሻሹን ሊቨርፑል ከቼልሲ ከመጫወታቸው በፊት የሊጉ መሪ መሆን ይችል ነበር።

ቦርንመዝ የአርሰናሉ ተከላካይ ዊሊያም ሳሊባ በቀይ ከመሰናበቱ በፊትም የመድፈኞቹን ተከላካይ መስመር እየፈተኑት ቆይተዋል።

ሚኬል አርቴታ የመድፈኞቹ አሠልጣኝ ሆነው ከተሾሙ በኋላ አርሰናል ከሌሎች የፕሪሚዬር ሊጉ ክለቦች የበለጠ ቀይ ካርድ ተመልክቷል።

በቀይ ካርድ የተሰናበተው ተከላካይ ሳሊባ አርሰናል በሚመጣው እሑድ በሜዳው ሊቨርፑልን ሲያስተናግድ የማይሰለፍ ይሆናል።

የቀኝ ክንፍ ተጫዋቹ ቡካዮ ሳካ ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን በሚጫወትበት ወቅት ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ከቦርንመዝ ጋር በነበረው ግጥሚያ አልሰተሰለፈም። አማካዩ ማርቲን ኦዴጋርድ ደግሞ ለረዥም ሳምንታት ካራቀው ጉዳት በማገገም ላይ ይገኛል።

አርሰናል በቀጣይ ሳምንታት በፕሪሚዬር ሊጉ ከሊቨርፑል፣ ከኒውካስል እና ከቼልሲ ይጫወታል።

በሌሎች የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች በሜዳው ኦልድ ትራፈርድ ብሬንትፈርድን ያስተናገደው ማንቸስተር ዩናይትድ ከኋላ ተነስቶ 2 ለ 1 ማሸነፍ ችሏል።

ለቀያይ ሰይጣኖቹ አሌሃንድሮ ጋርናቾ እና ራስመስ ሆይለንድ አስቆጥረዋል።

ቶተንሀም፣ ስተን ቪላ፣ ብራይተን፣ ሌስተር እና ኤቨርተን ድል ቀንቷቸዋል። እሑድ ከሰዓት ማንቸስተር ሲቲ ከሜዳው ውጪ ከዎልቭስ፤ ሊቨርፑል ደግሞ በሜዳው አንፊልድ ከቼልሲ ይጋጠማሉ።