ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሊቨርፑል ከቼልሲ - ማን ያሸንፋል? የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ግምት
ሊቨርፑልም ሆነ ቼልሲ የዘንድሮውን ውድድር ዘመን ጠንካራ ሆነው ነው የጀመሩት። ሁለቱም አዳዲስ አሠልጣኝ ሾመዋል። እሑድ በአንፊልድ ሲገናኙ ማን ድል ይቀዳጅ ይሆን?
“እርግጥ ነው ሊቨርፑል ሊጉን ይመራል ብዬ አልጠበቅሁም ነበር። ነገር ግን የቼልሲ ግስጋሴ የበለጠ አስገርሞኛል” ይላል የቢቢሲ ስፖርት ተንታኝ ክሪስ ሱተን።
“የቼልሲ ደጋፊዎች በቡድናቸው አቋም ደስተኛ እንደሆኑ አምናለሁ። ነገር ግን በአንፊልድ ትልቅ ፈተና ይገጥማቸዋል” ይላል ሱተን።
ሱተን የፕሪሚዬር ሊጉን ሁሉንም ጨዋታዎች ውጤት ገምቷል።
ቅዳሜ
ቶተንሃም ከዌስት ሃም
ዌስት ሃም ከኢፕስዊች ጋር በነበራቸው ጨዋታ አስፈላጊ የሚባል ሦስት ነጥብ አግኝተዋል። ቶተንሃም በተቃራኒው በብራይተን ተረትቷል።
ቶተንሃም ወደ ኦልድ ትራፈርድ አቅንቶ ማንቸስተርን መርታቱን ተከትሎ አሠልጣኝ አንጅ ፖስቴኮግሉ አድናቆት ዘንቦላቸው ነበር። ነገር ግን ከብራይተን ጋር በነበራቸው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ፈራርሰዋል።
ስፐርስ በዚህ ጨዋታ ወደ ድል ይመለሳል የሚል ግምት አለኝ። አምበሉ ሶን ሂዩንግ ሚን ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ይጠበቃል። ለዚህ ነው ከዌስት ሃም ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ ያሸንፋሉ የምለው።
ግምት፡ 3 - 1
ፉልሃም ከአስተን ቪላ
ፉልሃም በሜዳው ሲጫወት አስፈሪ ነው። በዚህ የውድድር ዘመን ከሜዳ ውጪም መልካም ብቃት እያሳዩ ይገኛሉ። ከሲቲ ጋር ኢቲሃድ ላይ በነበራቸው ጨዋታ ቢሸነፉም እስከ መጨረሻው ተጋድለዋል።
የዚህ ጨዋታ ውጤት የሚወሰነው በአስተን ቪላ ተጫዋቾች ጉዳት ላይ ነው። ኤዝሪ ኮንሳ እና አማዱ ኦናና መሰለፋቸው አጠራጣሪ ነው። አልፎም በሚመጣው ሳምንት አጋማሽ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ከቦሎኛ ይጫወታሉ።
እኔ ይህ ጨዋታ በአቻ ውጤት እንደሚጠናቀቅ ነው የምገምተው።
ግምት፡ 1 - 1
ኢፕስዊች ከኤቨርተን
ይህን ጨዋታ መገመት ከባድ ነው። ኢፕስዊች እስካሁን ድል አልቀናቸውም። ነገር ግን እያሳዩን ያለው አቋም የሚደነቅ ነው። በፕሪሚዬር ሊጉ የመቆየት አቅም እንዳላቸው ያስታውቃል።
ኤቨርተንም ቢሆን ወደ ድል ተመልሰዋል። ከኢፕስዊች በአንድ ነጥብ ከፍ ብለው ተቀምጠዋል። በሦስት ጨዋታዎች ሸንፈት አላስተናገዱም።
የዚህን ጨዋታ ውጤት መገመድ ከብዶኛል። ውስጤ የሚነግረኝ ምናልባት ኢፕስዊች የመጀመሪያውን ውጤት ያገኝ ይሆናል የሚለውን ነው።
ግምት፡ 2 - 1
ማንቸስተር ዩናይትድ ከብሬንትፈርድ
ባለፈው የውድድር ዘመን ብሬንትፈርድ ቀድሞ አግብቶ ሲመራ ስታድየም ተገኝቼ ታድሚያለሁ። ነገር ግን ስኮት ማክቶሚናይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ ለቡድኑ ድል አምጥቷል።
በዚህኛው ጨዋታስ ምን እናይ ይሆን? የዩናይትዱ አሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ውጤት ያስፈልጋቸዋል። ዩናይትድ 14ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። በሰባት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ብቻ ነው ያስቆጠሩት።
ንቦቹ ቀድሞው ግብ እንደሚያገቡ እገምታለሁ። ነገር ግን በስተመጨረሻ ውጤት የማንቸስተር ዩናይትድ እንደምትሆን እምነት አለኝ።
ግምት፡ 2 - 1
ኒውካስል ከብራይተን
አንዳንድ ሰዎች ኤዲ ሀው ኒውካስልን ለቀው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ እንደሚሆኑ ገምተው ነበር። ነገር ግን ይህ አልሆነም።
ይህ ጨዋታ አስደናቂ እንደሚሆን እገምታለሁ። ልክ እንደ ኤዲ ሀው የብራይተኑም አሠልጣኝ ወደፊት በመሄድ ያምናል። ስድስተኛ እና ሰባተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ቡድኖች ናቸው የሚፋለሙት።
አሌክሳንደር ኢሳክ ከጉዳት የሚመለስ ከሆነ ለኒውካስል ልዩነት ፈጣሪ ሊሆን እንደሚችል አምናለሁ።
ግምት፡ 2 - 1
ሳውዝአምፕተን ከሌስተር
ሁለቱም ቡድኖች ሦስት ነጥብ ያስፈልጋቸዋል። ሁለቱም በወራጅ ግርጌ ቀጣና ነው የሚገኙት። በተለይ የሳውዝአምፕተኑ አሠልጣኝ ረስል ማርቲን ውጤት በጣም ያስፈልጋቸዋል።
ምንም እንኳ ከታችኛቸው ሊግ ይዟቸው ቢመጣም ደጋፊዎች ውጤት ካጡ ፊታቸውን ማዞራቸው የሚቀር አይደለም። አሁን ያላቸው አንድ ነጥብ ብቻ ነው።
ሌስተር በተቃራኒው የመጀመሪያውን ድላቸውን አጣጥመዋል።
ጨዋታው በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል።
ግምት፡ 1 - 1
ቦርንመዝ አከርሰናል
ይህ ሌላ በጉጉት የምጠብቀው ጨዋታ ነው።
አርሰናል የተወሰኑ ተጫዋቾች ተጎድቶበታል። ቡካዮ ሳካ ለእንግሊዝ ሲጫወት ተጎድቶ ወጥቷል። ካይ ሀቨርትዝ እና ጋብርኤል ማርቲኔሊም መሰለፋቸው አጠራጣሪ ነው። ማርቲን ኦዴጋርድ ከጉዳቱ አልተመለሰም።
ነገር ግን የተከላካይ መስመራቸው ጠንካራ ነው። ምንም እንኳ ተጫዋቾች ቢጎዱባቸውም ውጤት ያመጣሉ የሚል እምነት አለኝ።
ቦርንመዝ የጎል ዕድል መፍጠር ይችላሉ። ነገር ግን የሚያገኟቸውን ኳሶች አለመጠቀማቸው ድክመታቸው ነው። ቦርንመዝ አርሰናል ላይ አስደናቂ ውጤት ቢያመጣ አይገርመኝም።
ግምት፡ 1 - 1
እሑድ
ዎልቭስ ከማን. ሲቲ
ዎልቭስ በሰባት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ማምጣት የቻሉት። የፕሪሚዬር ሊጉ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ ይገኛሉ። አሠልጣኙ ጋሪ ኦኒል በዚህ ሰዓት ከሲቲ ባይገጥሙ ደስ ይላቸዋል።
ባለፈው ጨዋታ በብሬንትፈርድ 5 ለ 3 ተሸንፈዋል። በዚህኛውም ጨዋታ የተወሰኑ ግቦች ማስተናገዳቸው አይቀሬ ነው።
ኧርሊንግ ሀላንድ በሁለት ጨዋታዎች ግብ አላስቆጠረም። ለሀላንድ ይህ ብዙ ነው። በዚህኛው ጨዋታ ጎል ባያስቆጥር ይገርመኛል።
ግምት፡ 1 - 6
ሊቨርፑል ከቼልሲ
ሊቨርፑል በቀጣይ ሳምንታት ጠንካራ የሚባል መርሐ ግብር ይጠበቀዋል። ከቼልሲ ቀጥሎ ወደ ኤሜሬትስ ስታድየም አቅንተው አርሰናልን ይገጥማሉ።
ሁለቱ ቡድኖች በተለይ ባለፈው አስር ዓመት ተቀናቃኝነታቸው እየጠነከረ መጥቷል። እሑድ ከሰዓት በሚደረገው ፍልሚያም ይህ ተቀናቃኝነታቸው በይፋ እንደሚታይ እምነት አለኝ።
ቼልሲ ወደ አንፊልድ ተጉዞ ሊቨርፑልን ይረታ ይሆን? እርግጠኛ አይደለሁም።
የአርን ስሎት አጨዋወት ለአጥቂው ሞሐመድ ሳላህ የተመቸ ይመስላል። እኔ ውጤቱ ወደ ሊቨርፑል የሚያጋድል ይመስለኛል።
ግምት፡ 2 - 1
ሰኞ
ኖቲንግሀም ከፓላስ
ክሪስታል ፓላስ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ አለበት። ባለፈው የውድድር ዘመን ጥሩ የሚባል አቋም ቢያሳዩንም ዘንድሮ ግን ይህ እየሆነ አይደለም።
ነገር ግን ኖቲንግሀም በሜዳቸው ከባድ ናቸው። እኔም ግምቴ ወደዚያ ያደላል።
ግምት፡ 1 - 0