ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሱዳን ጦር በዋና ከተማዋ አቅራቢያ የሚገኙ ቁልፍ ስፍራዎችን መቆጣጠሩ ተነገረ
የካርቱም ነዋሪዎች የሱዳን ጦር ኃይል ሰፊ የዋና ከተማውን ክፍል ከፈጥኖ ደራሹ ኃይል (አርኤስኤፍ) ታጣቂዎች አስለቅቆ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተናገሩ።
ይህም የጦር ኃይሉ በአንድ ዓመት ውስጥ ያስመዘገበው ትልቁ ድል መሆኑን ነዋሪዎች ጨምረው ገልጸዋል።
ስሙ ለደኅንነቱ ሲባል የተቀየረው ዶ/ር ሙስጠፋ ለቢቢሲ እንደተናገረው "በምኖርበት አካባቢ ተባራሪ ጥይቶች እና ተተኳሾች እየወደቁ ነው። በአሁኑ ወቅት ያለው ውጊያ ከባድ ነው" ብሏል።
በዚህ ሳምንት ገንዘብ የሚታተምባትን ሚንትን ጨምሮ ቁልፍ ቦታዎች በጄኔራል አልቡርሐን በሚመራው የአገሪቱ ጦር ቁጥጥር ስር ውለዋል።
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ፣ አርኤስኤፍ አሁንም አብዛኛውን የካርቱምን ክፍል ይቆጣጠራል።
የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ለዋና ከተማው አቅራቢያ ቁልፍ የሆኑ ስፍራዎችን ጨምሮ ኦምዱርማን እና ባህሪ የሚያዋስኑ አካባቢዎችን ይቆጣጠራል።
ጦሩ ወሳኙን የጀዚራ ግዛትን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠረ በኋላ፣ ዋና ከተማዋን ለመያዝ እና አማፂያኑ ለሁለት ዓመታት የተቆጣጠሩንት ለማስለቀቅ የሚያስችል አቅም እንዳለው ያምናል።
"በቅርቡ በካርቱም ምንም አማፂ አይኖርም" ሲሉ የጦሩ መሪ ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሐን ማክሰኞ ዕለት አስታውቀዋል።
ነገር ግን የዚህ ግጭት ማብቂያ እንዲህ በፍጥነት ሊመጣ አይችልም።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፉ ተመራማሪዎች እንዳሉት በካርቱም ብቻ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በረሃብ እየተሰቃዩ ነው።
የእርዳታ ሠራተኞች በጦርነቱ ምክንያት በመላ አገሪቱ ሰዎች በረሃብ እየተሰቃዩ መሆኑን ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።
የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በጄኔራል አል ቡርሐን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን በሚመሩት እና ምክትላቸው በነበሩት መሐመድ ሃምዳን "ሄሜቲ" ዳጋሎ መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ 12 ሚሊዮን ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል።
ሱዳን የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ መሆኗን የዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች በአንድ ድምጽ ይስማማሉ።
የአገሪቱ ጦር ሠራዊትም ሆነ አርኤስኤፍ በዳርፉር የዘር ማጥፋት ወንጀልን ጨምሮ በንፁሃን ዜጎች ላይ እጅግ የከፋ ግፍ እና በደል በመፈጸም ጥፋተኛ ናቸው ይላሉ።
ነገር ግን ሁለቱም ኃይሎች ክሱን ውድቅ አድርገዋል።
አርኤስኤፍ በካርቱም ሰላማዊ ዜጎችን በመግደል እና በመድፈር እንዲሁም ከተማዋን ለቀው የወጡትን የበርካታ ነዋሪዎችን ቤት በመዝረፍ ይወነጀላል።
ሠራዊቱ በቅርቡ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ሲደርስም በርካታ ነዋሪዎች ደስታቸውን ገልጸዋል።
የአገሪቱ መከላከያ ኃይል ቁልፍ ስፍራዎችን መቆጣጠሩን የሚገልጹ ዘገባዎችን አማፂያኑ "ውሸት እና አሉባልታ" በማለት አጣጥለዋል።
በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ለቅቀው በወጧቸው ከተሞች በሙሉ ተመሳሳይ ማስተባበያዎችን ሰጥተዋል።
ተንታኞች እንደሚሉት ሠራዊቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያስመዘገበው ድል ብዙ ተዋጊዎችን በመመልመሉ እና በርካታ የጦር መሳሪያዎችን በመግዛቱ የተገኙ ናቸው።
ሠራዊቱ በጥር ወር ከዋድ ማዳኒ አማፂያኑን ማስወጣቱን ተከትሎ ለታጣቂዎቹ መረጃ ያቀብላሉ ወይም ተባባሪዎች ናቸው ባላቸው ላይ የዘፈቀደ ግድያ በመፈጸም ክስ ቀርቦበታል።
ይህም በአንዳንድ የካርቱም ነዋሪዎች ላይ ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ይጠብቀናል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
ሙስጠፋ ለቢቢሲ እንደተናገረው "ማኅበራዊ ሚዲያ ስትከፍት እና የተፈጸሙ ግድያዎችን ስታይ የሠራኽው ነገር ካለ መጨነቅህ አይቀርም" ሲል ይናገራል።
"አንዳንዶች ተዋጊዎችን ወደ ሰዎች ቤት መርተዋል፣ ሌሎች ደግሞ [አርኤስኤፍን] ተቀላቅለው ንብረት ዘርፈዋል፣ ሰዎችን ያሸብራሉ፤ ሴቶችን ከፍላጎታቸው ውጪ [ የወሲብ ባሪያ አድርገው] ይይዙ ነበር። የሚመጣውን ፈርተው ነው? በእርግጥም እንደዚያ ነው። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ እንደ ተባባሪ በመታየት እና በጦርነት ውስጥ ሕይወትን ለማቆየት በሚደረግ ጥረት መካከል ቀጭን መስመር አለ።"
የካርቱም መንታ ከተማ በሆነችው ኦምዱርማን የሚኖረው አሚር "ለአክስቴ ልጅ ተጨንቄያለሁ" ይላል።
"ተባባሪ ወይም መረጃ አቀባይ አይደለም፤ እናቱን እና ልጆቹን ስለሚንከባከብ ብዙውን ጊዜ ከእነዚህ ሰዎች (አርኤስኤፍ) ጋር ይገናኛል። በሠራዊቱ ይገደላል ወይስ ይተርፋ?"
ለአሁኑ ሠራዊቱ ሲቃረብ እና የሱዳን የወደፊት ዕጣ ፈንታ መንታ መንገድ ላይ ሲወድቅ ሙስጠፋ እና አሚር ማድረግ የሚችሉት የሚሆነውን መጠበቅ ብቻ ነው።